ፍቅረኛውን የገደለው አሜሪካዊ ታዳኝ ከኬንያ የፖሊስ ቁጥጥር ስር አመለጠ

ፍቅረኛውን ገድሎ ከአሜሪካ ሸሽቶ በኬንያ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ግለሰብ ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ከፖሊስ ይዞታ ማምለጡ ተነገረ።

የ41 ዓመቱ ኬልቪን ካንጌቴ በመዲናዋ ናይሮቢ ከሚገኝ አንድ የምሽት ክበብ ሲወጣም ነበር ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር የዋለው።

የኬንያ እና የአሜሪካ ፖሊሶችም በጥምረት ለወራትም ሲፈልጉት ከቆየም በኋላ ነው የተያዘው።

የኬንያ ፍርድ ቤት ግለሰቡ ለአሜሪካ ተላልፎ እስኪሰጥም ድረስ ለ30 ቀናት በቁጥጥር ስር እንዲቆይ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

ግለሰቡ ጥቅምት ወር ላይ የሴት ጓደኛውን ከገደለ በኋላ በቦስተን ሎጋን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኝ ስፍራ በመኪና ውስጥ አስከሬኗን ጥሏት እንደሸሸ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

ከዚያም ወደ ትውልድ አገሩ ኬንያም ሸሽቷል ተብሏል። ግለሰቡ በቀረበበት ክስ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።

ግለሰቡ ተይዞበት ከነበረው የናይሮቢ የፖሊስ ጣቢያ ወጥቶም በህዝብ ማመላለሻ ተሽካርካሪ ተሳፍሮ መሄዱን ፖሊስ ማሳወቁን ተከትሎ በርካቶችን ያስደነገጠ ዜና ሆኗል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ግለሰቡ ከማምለጡ በፊት አግኝተውታል የተባሉ በስራ ላይ የነበሩ አራት ፖሊሶች እንዲሁም ጠበቃው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የናይሮቢ የፖሊስ ኮማንደር አደምሰን ቡንጂ ለኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

እንዲህ ዓይነት የጸጥታ መላላት ለኬንያ ፖሊስ “አሳፋሪ ነው” ማለታቸውን የግል ጋዜጣ የሆነው ስታር ዘግቧል። ግለሰቡንም እንደ አዲስ መፈለግ ተጀምሯልም ሲሉ ተናግረዋል።

የግለሰቡ ፍቅረኛ የነበረችው ማርጋሬት ምቢቱ ቤተሰቦች ለአሜሪካ ሚዲያ እንደተናገሩት ከመገደሏ በፊት ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ እቅድ ነበራት ብለዋል።

የ30 ዓመቷ ግለሰብ ኬንያዊት አሜሪካዊት ስትሆን በማሳቹስተስ ግዛትም በነርስነት ታገለግል ነበር።

በህይወት ለመጨረሻ ጊዜ የታየችውም ከስራዋ ቦታ ስትወጣ ጥቅምት ወር ላይ ነበር።

መጥፋቷ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ከሁለት ቀናት በኋላ አስከሬኗ ተገኝቷል።

መጥፋቷ ሪፖርት በተደረገበት እና አስከሬኗ በተገኘበት ባሉት ቀናትም ግለሰቡ ጠፍቷል ብለው እንደሚያምኑም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል። አስከሬኗ ከተገኘበት ከአውሮፕላን ማረፊያው ከሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ለቆ ሲወጣም የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎም በግድያዋ እጁ እንዳለበት ተገልጿል።

ግለሰቡ ባለፈው ዓመት የአሜሪካ ዜግነቴን ትቻለሁ ማለቱን ተከትሎ በኬንያ ወይስ በአሜሪካ ይዳኝ በሚለው ላይ የኬንያ ፍርድ ቤት በቅርቡ ውሳኔም ሊያሳልፍ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn

ምንጭ (ቢቢሲ)