በናይሮቢ አቅራቢያ 50 ሰዎች በጎርፍ ተወሰዱ!!!!!

በኬንያ መዲና ናይሮቢ አቅራቢያ በምትገኝ ስፍራ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ 50 ሰዎች መወሰዳቸውን የቀይ መስቀል ባለስልጣን አስታወቁ።

ከናይሮቢ በ60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የማይማሂዩ መንደሮች ነዋሪዎችን ነው ጎርፍ ጠርጎ የወሰዳቸው።

ነዋሪዎቱ ተኝተው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተፈርቷል።

በጭቃ ውስጥ የተቀበሩ ነዋሪዎችን ለማውጣት የህይወት አድን ጥረቱ ቀጥሏል።

በኬንያ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ባስከተለው ጎርፍ ከ100 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።

በውሃ ተጠርጎ የተወሰደ ጭቃ፣ ተገነዳድሰው የወዳደቁ ዛፎች እና የፈራረሱ ቤቶች በማይ ማሂዩ አካባቢዎች ይታያሉ።

ሰኞ ሌሊት ከተከሰተው የከፋ ጎርፍ ነዋሪዎችን ለመታደግ እና ከጭቃው ለማውጣት እልህ አስጨራሽ ጥረቶች መደረጋቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የ60 ዓመቱ ዴደን ሙሪ በውሃ አንገታቸው ድረስ ከመስመጣቸው በፊት ነጎድጓድ የተሞላበት ድምጽ እና የመብረቅ ብልጭታ ለሰኮንዶች እንዳዩ ይናገራሉ።

ጎርፉ ባለቤታቸውን ጠርጎ ሲወስድ እና እሳቸውም ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ተወሰዱ።

ለመሞታቸው እርግጠኛ የነበሩት ዴደን ቤተሰባቸውን በውስጣቸው ተሰናበቱ።

ነገር ግን አትጥፊ ያላት ነፍስ ሆና ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ የዛፍ ቅርንጫፍ ይዘው ህይወታቸው ተረፈ።

ከሴት ልጆቻቸው አንዷ መዋኘት የምትችል ሲሆን ሁለት የልጅ ልጆቻቸውን ህይወት መታደግ ችለዋል።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች በአካባቢው በደረሱበት ወቅት በርካቶች ጉዳቱን ሲገመግሙ፣ ፍርስራሾችን እያዩ እና የደረሰው ጥፋት አስደንግጧቸው ባለበት ሁኔታ ነው።

የአካባቢው ነዋሪ ፒተር ሙንዩንጌ እንደ እድል ሆኖ ቤቱ ቢተርፍም የመንደሮቹ ቤቶች ተጠራርገው ተወስደዋል።

“ጎርፉ ትንንሽ ህጻናትን፣ አዛውንቶችን ወስዷል። ሰዎች እየጮሁ፣ እያለቀሱ ነበር። በርካቶች ህይወታቸው ሲነጠቅ ተመልክተዋል። የሚወዷቸውን አጥተዋል” ብሏል።

የኬንያ ቀይ መስቀል በፍለጋው እና በአድን ስራው የተሰማራ ሲሆን የተቋሙ ድንገተኛ አደጋ ምላሽ ኃላፊ አንቶኑ ሙቺሪ የሟቾች ቁጥር 50 መድረሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስ ከተገኙት አስከሬኖች 17ቱ የህጻናት መሆናቸውን የፖሊስ ኃላፊው ሲቴፈን ክሩይ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ድንገተኛው የጎርፍ ማዕበል የተፈጠረው የአካባቢው ግድብ በመፈንዳቱ ምክንያት እንደነበር የአካባቢው ባለስልጣናት ጠቅሰው ነበር።

ይሁን እንጂ የኬንያ የውሃ እና መስኖ ሚኒስቴር ሰኞ ማምሻውን እንዳስታወቀው ቶንጊ የተሰኘው ወንዝ የሚተላለፍበት በባቡር መንገድ ስር የሚገኘው መተላለፍያ በፍርስራሾች፣ ድንጋዮች፣ ዛፎች እና አፈር በመዘጋቱ ነው።

ይህም ውሃው ወደታች እንዳይወርድ በማድረጉ እና የባቡር መንገዱን ጠራርጎ ወደ አንድ መስመር መውሰዱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ(BBC)