ሐማስ የእስራኤልን አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚቀበል አሜሪካ ‘ተስፋ ሰንቃለች’…..

እስራኤል ያቀረበችውን እና አሜሪካ “በጣም ለጋስ” ስትል የጠራችውን የጋዛ ተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ሐማስ እንደሚቀበል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተስፋ ማድረጋቸውን ገለጹ።

አንቶኒ ብሊንከን ይህንን የገለጹት የሐማስ ልዑካን ቡድን በአዲሱ ሃሳብ ላይ ከግብጽ እና ከኳታር አሸማጋዮች ጋር በሚወያይበት ወቅት ነው።

ለውይይቱ ቅርብ የሆነ ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተስፋ አላቸው።

የቀረበው ሃሳብ ታጋቾችን መልቀቅን እና የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዲመለሱ እና የ40 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነትን ያካትታል።

የሐማስን የዘላቂ የተኩስ አቁም ጥያቄ እና ሠላሙን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ በማሰብም አዲስ ቃላትን ያካትታል ተብሏል።

የሐማስ ልዑካን ቡድን ካይሮንን ለቆ የወጣ ሲሆን ለቀረበለት ሃሳብ የጽሁፍ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ሲል የግብጽ መንግስት አጋር የሆነው አል ቃሄራ ቲቪ ተናግሯል።

የእስራኤል መንግሥት ከስምምነት እንዲደርስ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ እና ከታጋቾች ቤተሰቦች ጫና እየደረሰበት ነው።

ሐማስ መስከረም 26 በፈጸመው ጥቃት ከአንድ ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ገድሎ 253ቱን ደግሞ አግቶ መውሰዱን መውሰዱን ተከትሎ እስራኤል በተቀናጀ እና በማያባራ ሁኔታ ጋዛን እያጠቃች ትገኛለች።

በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ከ34 ሺህ 480 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በህዳር ወር በተደረሰ አንድ ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ሐማስ ከታጋቾቹ መካከል 105ቱን ሲለቅ 240 የሚያህሉ ፍልስጤማውያን አብዛኛቹ ህጻናት እስረኞች ደግሞ ከእስራኤል እስር ቤቶች እንዲፈቱ ተድርጓል።

ከግብጽ፣ ከኳታር እና ከአሜሪካ የተወከሉ አሸማጋዮች ጦርነቱ እንዲቆም እና እስራኤል በእስር ላይ ይገኛሉ ያለቻቸውን 133 ታጋቾች ለማስለቀቅ የሚያስችል አዲስ ስምምነት ለማድረግ ለሳምንታት ሲሞክሩ ቆይተዋል። ከታጋቾቹ መካከል 30 ያህሉ ህይወታቸው እንዳለፈ ይገመታል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለስድስት ሳምንታት በሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት 40 ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶች እንዲሁም ያመማቸው ታጋቾች ተለቀው በመቶዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞች እንዲፈቱ እስራኤል ያቀረበችውን ሃሳብ ሐማስ ውድቅ አደርጎታል።

ሐማስ በበኩሉ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ዘላቂ የተኩስ አቁም ጥያቄውን እንደሚቀጥልበት ተናግሯል።

በካይሮ ለሚደረገው ውይይት ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት ከሆነ በእስራኤል የቀረበው አዲስ ሃሳብ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በእጅጉ የተለየ ነው።

አክሲዮስ የዜና ድረ-ገጽ የእስራኤል ባለስልጣናትን ጠቅሶ ቅዳሜ ዕለት እንደዘገበው ከሆነ ነዋሪዎች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዲመለሱ እና የእስራኤል ወታደሮች ግዛቱን ከሚከፈለው እና የመዘዋወር ነፃነትን ከሚከለክለው ኮሪደር ለመውጣት ፈቃደኛ መሆንን ያካትታል ብሏል።

“የሁለተኛው ምዕራፍ አፈጻጸም አካል የሆነ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲኖር ለመወያየትም” ፍላጎቱን አካቷል ብለዋል ኃላፊዎቹ።

የእስራኤል ባለስልጣናት እና አንድ ዲፕሎማት ሰኞ ዕለት ለኒውዮርክ ታይምስ እና ለፋይናንሺያል ታይምስ እንደተናገሩት እስራኤል በመጀመሪያው ምዕራፍ እንዲለቀቁ ያቀረበችውን የታጋቾች ቁጥር ከ40 ወደ 33 ዝቅ ለማድረግ መዘጋጀቷንም ተናግረዋል።

አዲሱን የእስራኤልን ሃሳብ እየተመለከተው መሆኑን ሐማስ በይፋ ተናግሯል። ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ከሆነ “አዲስ የእስራኤል መሰናክሎች እስካልተፈጠሩ ድረስ ሁኔታው ጥሩ ይመስላል” ብለዋል።

“ሐማስ ያቀረበው ምልከታ እና ጥያቄ ይዘትን በተመለከተ ምንም አይነት ጉዳዮች የሉም” ሲሉም አክለዋል።

ብሊንከንም በርካታ የአውሮፓ እና የአረብ አቻዎቻቸው በተገኙበት የሪያዱ የዓለም ኢኮኖሚክ ጉባዔ ላይ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

“በእስራኤል በኩል ባልተለመደ መልኩ ለጋስ የሆነ ዕቅድ ሐማስ ፊት ተቀምጧል። በዚህ ወቅት በጋዛ ህዝብ እና በተኩስ አቁም ስምምነት መካከል ያለው መካከል ያለው ብቸኛው ነገር ሐማስ ነው” ብለዋል ።

“መወሰን አለባቸው። በፍጥነት መወሰን አለባቸው … እናም ትክክለኛውን ውሳኔ እንደሚወስኑ ተስፋ አደርጋለሁ።”

ከአሸማጋይ አገራት አንዷ የሆነችው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪም “ተስፋ አለኝ” ብለዋል።

“ሐሳቡ የሁለቱንም ወገኖች አቋም ከግምት ውስጥ ያስገባ እና አማካዩን ለመውሰድ ሞክሯል። በሁለቱም ወገኖች ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ቢኖሩም ግን ሁሉም ለኃላፊነቱ ላይ እንደሚነሱ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ያደረጉት የስልክ ጥሪ ትኩረቱን በድርድሩ ላይ ማድረጉ ታውቋል።

በቅርቡ በጋዛ እየደረሰ ያለው ዕርዳታ መጨመሩን እና ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ተፈናቃዮች በተጠለሉባት ደቡባዊ ራፋህ ከተማ ላይ ቴል አቪቭ ያቀደችውን ጥቃት ዋሸንግተን ተቃውማ መቀጠሏን የተገለጸበትም ነበር።

እስራኤል በራፋህ በሚገኙ ሦስት ቤቶች ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 22 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የህክምና ባለሙያዎች እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ተናግረዋል።

“መላው ዓለም ዘላቂ የተኩስ አቁም ጥሪ እንዲደረግ እንጠይቃለን። ይህ በቂ ነው” ሲል አቡ ታሃ የተባሉ ግለሰብ በአል-ናጃር ሆስፒታል ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

የእስራኤል ጦር ስለጉዳዩ ምንም አስተያየት አልሰጠም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ(BBC)