የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያውያን ላይ ጊዜያዊ የቪዛ ገደብ ጣለ…..

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት (ካውንስል) ኢትዮጵያውያን ላይ በጊዜያዊነት የቪዛ ገደብ ማሳለፉን አስታወቀ።

በአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ድረ ገጽ ላይ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ. ም. በወጣው መግለጫ መሠረት፣ በአውሮፓ ኅብረት ሕግ ሥር ያሉና ለኢትዮጵያውያን ቪዛ ለመስጠት ይውሉ የነበሩ አሠራሮች ላይ ገደብ ተደርጓል።

በዚህ ዕገዳ መሠረት፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ኢትዮጵያውያን በሚያቀርቧቸው ማስረጃዎች መሠረት ቪዛ ሲጠይቁ የሚያስፈልጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማንሳት (waiving requirements) አይችሉም።

ኢትዮጵያውያን ከአንድ ጊዜ በላይ ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ገብተው መውጣት የሚችሉበት ቪዛ (multiple entry) ማግኘት አይችሉም።

የዲፕሎማት እና አገልግሎት ፓስፖርት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ያለ ክፍያ ቪዛ እንዲሰጣቸው አይደረግም።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ቪዛ ለማግኘት የሚጠብቁት ጊዜ ከ15 የሥራ ቀናት ወደ 45 የሥራ ቀናት ከፍ እንዲል ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል።

መግለጫው እንደሚለው፣ ይህ ውሳኔ በኮሚሽኑ የተላለፈው “የኢትዮጵያ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ የአውሮፓ ኅብረት አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቹን መልሶ ለመቀበል ያሳየው ተባባሪነት አናሳ መሆኑን ካውንስሉ ባደረገው ግምገማ ስለተገነዘበ” ነው።

አክሎም “የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ዜጎችን መልሶ ለመውሰድ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም” በማለት መግለጫው ያብራራል።

የአስቸኳይ ጊዜ የጉዞ ሰነዶች በመስጠት እንዲሁም በፍቃድ እና ያለ ፈቃድም የሚደረግ ስደተኞችን የመመለስ ሂደትን በተመለከተም ኢትዮጵያ “በቂ ትብብር አላደረገችም” ሲልም መግለጫው የውሳኔውን ምክንያት ያስረዳል።

ስደተኞችን በመቀበል ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን “ትብብር” በድጋሚ እንደሚቃኝም ኮሚሽኑ አክሏል።

በአውሮፓ ኅብረት የቪዛ ሕግ መሠረት፣ ኮሚሽኑ አገራት ስደተኞችን መልሶ በመቀበል ረገድ ያላቸውን ተባባሪነት እንደሚገመግም በድረ ገጹ የወጣው መግለጫ ይገልጻል።

በኢትዮጵያ በኩል ስደተኞችን የመቀበል መጠኑ “አናሳ” እንደሆነ ጠቅሶ፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ለኢትዮጵያ ያቀረቡት ስደተኞችን የመመለስ ጥያቄ ያገኘው ምላሽ “እምብዛም አለመሆኑ” ያለውን ትብብር “ትንሽ” ነው ብሎ እንዲደመድም ምክንያት እንደሆነው ማብራሪያ ሰጥቷል።

ውሳኔው ጊዜያዊ ቢሆንም ቀነ ገደብ እንደሌለው የኮሚሽኑ መግለጫ ይጠቅሳል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ(BBC)