ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እንደሚያሳስበው ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ከስድስት ወራት በፊት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ አሳሳቢ ነው አሉ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያራዝመው ከሆነ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት ዛሬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ገደማ ያጻደቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማራዘም በሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ከተገለጸ በኋለ ነው።

ምክር ቤቱ ለዛሬ አርብ ጥር 24/2016 ዓ.ም. በጠራው ልዩ ስብሰባው አባላቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም በሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ውይይት በማድረግ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት ለማራዘም የሚቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የሕዝብ እንደራሴዎችን ድጋፍ ካገኘ ተፈጻሚነቱ ይረዘማል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚራዘም ከሆነ የግጭት ተጎጂ በሆኑ፣ በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ባሉ እና ለፍርድ ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜያት በእስር ላይ በሚቆዩ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተጽእኖ አሳሳቢ ብለዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በኤክስ ገጻቸው “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት፣ ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነትን በአግባቡ ማጤን ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲደነገግ ላስገደደው ችግር “ውይይት ቁልፍ” መፍትሄ ነው ሲሉ መክረዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል እየተባባሰ የሄደውን ግጭት ተከትሎ ክልሉ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ባቀረበው ጥሪ ነበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገው።

በአማራ ክልል ውስጥ እንዲሁም “እንዳስፈላጊነቱ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች” ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚቀጥለው ሳምንት የሚያበቃ በመሆኑ ነው ምክር ቤቱ ለማራዘም ስብሰባ የጠራው።

ኢሰመኮ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም. አውጥቶት በነበረው ሪፖርት ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገበት አማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።

ኮሚሽኑ በክልሉ ግድያ እና መድፈርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።

“የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው” ሲል ኮሚሽኑ ሁኔታውን ገልጾ ነበር።

እየተካሄዱ ካሉ ግጭቶች ጋር እና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ያለመከሰስ መብት ያላቸው የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከአማራ ክልል ባሻገር ባሉ አካባቢዎች ጭምር በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር ላይ ይገኛሉ።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ያወጣውን ሪፖርት “አስተማማኝ በሆነ መረጃ ላይ ያልተመሠረት እና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው” ሲል መንግሥት አጣጥሎት ነበር።

መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ስር የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መደበኛ ኑሯቸው መመልስ እንዲችሉ እና “መሠረታዊ መብታቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲጠበቅ” የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሰራ ይገልጻል።

በአማራ ክልል በፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተቀስቅሶ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ ምክንያት የሆነው ግጭት አሁንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የቀጠለ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትም ተሰማርቶ ይገኛል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnn

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )