ወደ የኦሮሚያ አካባቢ አንመለስም ያሉ ተፈናቃዮች የምግብ እርዳታ “ተከለከልን” አሉ…..

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጥቃቶችን በመሸሽ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው።

መንግሥት በሦስት ዙር ተፈናቃዮችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመመለስ ውጥን የያዘ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ዙር ተመላሾች ባለፈው የካቲት ወር ወደ የወለጋ ዞኖች እና ሌሎች አካባቢዎች መመለሳቸው ታውቋል።

ሆኖም የደኅንነት ስጋት አድሮባቸው ዳግም ወደ ደብረ ብርሃን የተመለሱ እና ቀድሞውኑም ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የምግብ እርዳታ እንዳይሰጣቸው መከልከሉን ተፈናቃዮች እና አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ሦስት [ባለፈው ዓመት ከስድስት ወደ ሦስት እንዲሰበሰቡ የተደረጉ] መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ አንዱ እና ሰፊው የሆነው ቻይና ካምፕ ከ12 ሺህ የሚበልጡ ተፈናቃቶችን ያስጠለለ ነው።

የመጀመሪያ ዙር ነው በተባለው ተፈናቃዮችን የመመለስ መርሃ ግብር ለመመለስ ዝግጁ ናቸው ተብሎ ከኦሮሚያ ክልል 1,800 በላይ ተፈናቃዮች ስም ዝርዝር እንደመጣ ቢቢሲ ከምንጮቹ ተረድቷል። ከእነዚህ ውስጥ 670 ያህሉ ወደ ቀድሞ መኖሪያ ወረዳቸው መመለሳቸው ታውቋል። 56 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ደግሞ በስጋት ምክንያት ወደ ካምፑ ተመልሰዋል ተብሏል።

የደኅንነት ስጋት አድሮባቸው ዳግም ወደ ደብረ ብርሃን የተመለሱ ተፈናቃዮችና ለመመለስ ፍላጎት ሳይኖራቸው የቀሩ ተፈናቃዮች ምግብ እርዳታ እንዳያገኙ የሚከለክል ደብዳቤ ባለፈው ሳምንት መላኩ ተነግሯል።

የካቲት 10/2016 ዓ.ም. ከተመለሱ ተፈናቃዮች አንዱ የሆኑትና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ተፈናቃይ በ15ተኛ ቀናቸው ወደ ደብረ ብርሃን መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ከባለቤታቸው እና ሁለት ልጆቻቸው ጋር ወደ ቀድሞ ቀያቸው ምሥራቅ ወለጋ ጎቡ ሰዮ ወረዳ ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደተመለሱ የሚናገሩት ተፈናቃዩ፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ በስጋት ምክንያት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

“ምንም የተቀየረ ነገር የለም። በፊትም በጦርነት ፍራቻ ነበር የወጣነው፤ አሁንም ተመልሶ ለሕይወታችን አስጊ ነው፤ ምንም የተቀየረ ነገር የለውም” ሲሉ ለመመለሳቸው ምክንያት ያቀርባሉ።

ሆኖም በተመለሱበት ደብረ ብርሃን የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ እርዳታ እንዳያገኙ ስለመከልከላቸው ተናግረዋል።

“በኮሚቴም ሆነ በምግብ ዋስትና ምንም አይነት እርዳታ እንደማይሰጠን ቁርጥ አድርገው ነግረውናል” የሚሉት ተፈናቃዩ፤ ከቤተሰባቸው ጋር “በረሃብ መሞት” ዕጣ ፈንታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ከምዕራብ ሸዋ ዳሎ ከሚባል ወረዳ እንደተፈናቀሉ የሚናገሩት የአምስት ልጆች እናት ወደ ቀደመ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ካልሆኑ በርካታ ተፈናቃዮች መሀል ናቸው።

“አገሩን የሚጠላ አልነበረም” ሲሉ አሁንም አካባቢያቸው ሰላም ባለመሆኑ መመለስ እንዳልፈቀዱ ገልጸው፤ በዚህ ውሳኔያቸው የምግብ ክልከላ እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።

“ሀሳብ ላይ ነው ያለነው። የምንቀምሰው የለን፤ ምን የለን” ሲሉ እርዳታ ከመጣ ወራት እንደተቆጠሩ ጠቁመው፤ በዚህ ላይ ገና ከሚመጣ እርዳታ መከልከላቸው ጭንቅ ላይ ነን ብለዋል።

“. . .ያልሄዱ ሰዎች በመንግሥት ድጋፍ መደገፍ አትችሉም፤ ለሌላው ስንዴ ሲሰጥ እናንተ ልትሰጡ አይገባም በሚል ነው የከለከሏቸው” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የመጠለያ ጣቢያ አስተባባሪ፤ ለዚህም የቀረበው ምክንያት የተፈናቃዮቹ ድርሻ (ኮታ) ወደ ኦሮሚያ ክልል ተልኳል የሚል ነው ብለዋል።

በቻይና ካምፕ ብቻ 1200 የሚሆኑ ተፈናቃዮች የምግብ እርዳታ እንዳይሰጣቸው መከልከላቸው ተነግሯል።

ለከተማ አስተዳደሩ አቤቱታ እንዳቀረቡ የተናገሩት ተፈናቃዮች “ትዕዛዙ ከላይ [ከፌደራል መንግሥት] ነው የመጣው” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

“ምግቡ የሚሰጠው ከፌደራል ነው፤ ትዕዛዙም የመጣው ከፌደራል ነው። ‘መመለስ ስላለባቸው ካልተመለሱ የምግብ ድጋፍ እዚህ አይሰጡም’ ስለተባለ እኛም ይኼ ነው የሚሆነው ዝም ብለን ነው ያልነው” ሲሉ አንድ አስተባባሪ ተናግረዋል።

የምግብ ክልከላው ተፈናቃዮችን “በግዴታ” ለመመለስ የሚደረግ እርምጃ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተፈናቃዮች እና አስተባባሪዎች እምነት ነው።

“የመንግሥትን አቋም ይዛችሁ ካልተራመዳችሁ የሚል ነው” ሲሉ ስለ እርምጃው የሚናገሩ አንድ ተፈናቃይ፤ ‘በሁለተኛው ዙር መሄድ ትችላላችሁ፤ ያለዚያ ካምፑን ለቃችሁ ትወጣላችሁ’ እየተባለ ነው” ብለዋል።

እኝሁ ተፈናቃይ “የሞት ሞት እዚሁ እንሞታለን” የሚል ውሳኔ ላይ ቤተሰባቸው እንደደረሰ ተናግረዋል።

“በግድ ያወጣናትን ነፍስ ተመለስን መልሰን እዚያው አንጥላትም። ይቺ ነፍስ ደግሞ ታጓጓለች፣ ታሳሳለች” በማለት እርዳታ ባያገኙም ደብረ ብርሃን እንደሚቆዩ ሌላ ተፈናቃይ ገልጸዋል።

“እንግዲህ ሰው የሚበላው ካጣ የግድ አማራጭ ሌላ ስለማይኖረው፤ ሞትም መጣ ስቃይም መጣ ያው ወደዚያ እየተመለሱ ሁሉን ነገር ከመጋፈጥ ውጭ ሌላ መፍትሄ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም [ሰው] ካልበላ መኖር ስለማይችል” በማለት ተፈናቃዮች በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ ስለመውደቃቸው አንድ አስተባባሪ ገልጸዋል።

የተመለሱ ሰዎችስ ምን ይላሉ?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በመጀመሪያ ዙር ወደ ምሥራቅ ወለጋ የተመለሱ ተፈናቃዮች የደኅንነት ስጋት አሁንም እንዳለ ጠቅሰው፤ በመንግሥት የተገባላቸውን ቃል እየጠበቁ መሆናቸውን ብለዋል።

ወይንሸት በተባለ መጠለያ ጣቢያ ሁለት ዓመት ቆይተው ወደ ምሥራቅ ወለጋ ባለፈው የካቲት ወር የተመለሱ አንድ ተፈናቃይ “የተሻለ” እርዳታ እያገኘን ነው ብለዋል።

የደኅንነት ስጋት ያደረባቸው “ጥቂት” ሰዎች ስለመመለሳቸው የሚያረጋግጡት ተፈናቃዩ፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከታጣቂዎች ይጠብቁናል የሚል ተስፋ በመሰነቅ፤ ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለሳቸው የተሻለ ምርጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2013 ዓ.ም. ተፈናቅለውበት ወደ ነበረው ጎቡ ሰዮ ወረዳ የተመለሱ ሌላ ተፈናቃይ “መንግሥት ዜጎቼ ናችሁ ካለን ዜጎቹ ነን” ሲሉ የተፈናቃዮችን መመለስ የሚደግፉ ቢሆንም፤ የተነገራቸው እና ያገኙት ግን ለየቅል ናቸው ይላሉ።

“ሁሉም ነገር ተሟልቷል፤ ሰላሙም ተስተካክሏል፤ ወደ ነበራችሁበት ቤት ገብታችሁ፤ ቤታችሁ ተሰርቶላችሁ፤ ቤታችሁ የፈረሰባችሁ ተክሳችሁ [ከሦስት ወር በኋላ] ወደ በፊቱ ሕይወታችሁ ትመለሳላችሁ” የሚል ቃል እንደተገባላቸው ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳደር “በአቅሙ” እየረዳን ነው ቢሉም፤ የአካባቢው የሰላም ሁኔታ ግን “አሳሳቢ” ነው ይላሉ።

“ዙሪያው ያለው የሰላም ሁኔታ፤ ወደ ቀያችን ገብተን የመሥራታችን ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ያለው።. . . በፊት ስንፈናቀል የነበረው የፀጥታ ሁኔታ አሁንም እንዳለ ነው። እኛ ከሄድን በኋላ [ከ10 ቀበሌዎች] ወደ ሦስት ቀበሌዎች በታጣቂዎች እጅ ነው ያሉት” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

ሆኖም “መንግሥት እንዳደረገ ያድርገን” በሚል ዕጣ ፈንታቸውን ለመንግሥት እንደሰጡ ተናግረዋል።

ከ22 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ባስጠለሉት የደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያዎች በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት ከበጎ አድራጊዎች የሚቀርበው ድጋፍ መቀነሱን አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ጠቁመዋል።

ከመንግሥት የሚቀርበው ሰብዓዊ እርዳታም ከጥር መጀመሪያ በኋላ እንዳልተሰጠ የተናገሩ ሲሆን፤ ተፈናቃዮች ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ የሰሜን ሸዋ አስተዳደርን እና የአማራ ክልልን የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(BBC)