ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት የጀልባ አደጋ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በስደተኛው አንደበት………

ሰባ ሰባት ኢትዮጵያውያን የየመን እና የሳዑዲ ስደታቸው ተስፋቸውንም፣ የወጣትነት ዕድሜያቸውንም አላምጦ ተፍቶታል። እናም ወደ ቤተሰቦቻቸው ኢትዮጵያ ለመመለስ ወሰኑ።

ውሳኔያቸውን ለደላላ ሲያሳውቁ ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. ምሽት ወደ ጂቡቲ የምትሻገር ጀልባ ዝግጁ መሆኗ ተነገራቸው።

ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በቅድሚያ ጂቡቲን መርገጥ አለባቸው። ጂቡቲ ለመድረስ ደግሞ ቀይ ባሕርን በጀልባ ማቋረጥ ያስፈልጋል።

ይህንን ጉዞ ከዚህ በፊት ከውነውታል። ከኢትዮጵያ የመን ሲመጡም ተመሳሳይ መንገድ ተከትለው ነው።

ስለዚህ ደላሎቹ የጠየቁትን ከፍለው ሚያዝያ 14 ሰኞ ምሽት፣ አራ በምትባለው የየመን የወደብ ከተማ ደረሱ።

ቢቢሲ ያነጋገረው መሐመድ* [ስሙ የተቀየረ] ከ77ቱ ፍልሰተኞች መካከል ነው።

እርሱን እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን የጫነችው ጀልባ ስትገለበጥ በሕይወት መትረፍ ከቻሉት ውስጥ አንዱ ነው።

ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. ሰባ ሰባት ኢትዮጵያውያንን ይዛ ከየመን ወደ ጂቡቲ የባሕር ዳርቻ የተቃረበችው ጀልባ ተገልብጣ 24 ፍልሰተኞች መሞታቸውን በጂቡቲ የመንግሥታቱ ድርጅት ለቢቢሲ ገልጿል።

የጂቡቲ ባለስልጣናት በበኩላቸው የሟቾችን ቁጥር 33 አድርሰውታል።

ከሟቾቹ መካከል የሰባት ወር ጨቅላን ጨምሮ አምስት ሴቶች ይገኙበታል።

በእርግጥ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል። እስካሁን ቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ያልተገኙ 20 ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ተገልጿል።

ከአደጋው የተረፉ 33 ኢትዮጵያውያን በአሁን ሰዓት በጂቡቲ ኦቦክ የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

መሐመድ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የመን ከምትገኘው አራ ሲነሱ፣ ጀልባዋ ላይ የተሳፈሩት ሰዎች ብዙ መሆናቸውን ለደላሎቹ በመንገር ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

“50 ያህል እንሆን ነበር መጀመሪያ ላይ፤ 27ቱን አምጥተው ሲጨምሯቸው ቅሬታ አቅርበን ነበር።”

ያም ሆኖ ጎዶርያ የጅቡቲ የባሕር ዳርቻ የደረሱት በሰላም መሆኑን መሐመድ ያስታውሳል።

መሐመድ ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ ነው። የ22 ዓመት ወጣት ሳለ ለታናናሾቹ እንዲሁም ለእናት እና ለአባቱ ደጀን መሆን ፈለገ።

የአባቱን እርሻ፣ ያደገበትን ቀዬ ጥሎ ወደ የመን ወይም ሳዑዲ አረቢያ ሄዶ መሥራት ሻተ።

ይህ ምኞቱ ደግሞ ፈርጠም እንዲል እና ጉልበት እንዲያገኝ ያበረታቱት ደላሎች ናቸው።

ከኢትዮጵያ ጂቡቲ፣ ከዚያም ወደ የመን የተሻገረው የዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አካባቢ መሆኑን ያስታውሳል።

ለመሻገርም 17 ሺህ ብር ያህል ለደላሎች ከፍሏል።

መሐመድ ዕቅዱ የነበረው ወደ ሳዑዲ አረቢያ መሻገር ቢሆንም “አልተሳካም፤ ረብሻ ነበረ [የየመን ግጭት]፤ የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች ለመሻገር የሚሞክሩትን ተኩሰው ይመታሉ። በአጠቃላይ መሞት በዛ ስለዚህ መሻገር አልቻልኩም” ይላል።

ሳዑዲ አረቢያ ገብቶ የራሱን ሥራ ሠርቶ ቤተሰቡን መደገፍ፣ ሕይወቱን መለወጥ ያለመው መሐመድ “አልተሳካልኝም” ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ የሁለት ዓመት ከአንድ ወር የመን ቆይታው መሐመድን ብዙ አሳይቶታል።

በሰው አገር ሳይሰሩ፣ ለምጽዋት እጅን እየዘረጉ መኖሩ ምቾት አልሰጠውም። በሩቅ ወደሚያልማት ሳዑዲ አረቢያ መግባት ደግሞ የሚታሰብ አልሆነም።

ያኔ ደላሎች ወደ ጂቡቲ መመለስ የሚፈልጉትን እያስከፈሉ እንደሚያሻግሩ ሰማ።

ደላሎች ከሳዑዲ ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች 1ሺህ 500 ሪያድ ያስከፍላሉ ይላል መሐመድ።

የመን ደግሞ ለቆዩት 600 ሪያድ መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

“በየመን ያለው የስደተኛው ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም። አብዛኛው መመለስ ይፈልጋል” ይላል መሐመድ።

ነገር ግን አብዛኞቹ ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ የላቸውም። ቤተሰቦቻቸውም ቢሆኑ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ነው።

ስለዚህ እንዲሁ በየመን ሰማይ ስር ነገ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን እያሉ ሲንከላወሱ መዋል ነው።

በረመዳን የጾም ወር የመን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት የተወሰኑትን ወደ መጠለያ አስገብቶ ነበር ይላል መሐመድ።

ቀሪው ግን በረሃብ እና በእርዛት በየመን ጎዳናዎች ላይ ቀኑን ሲቆጥር ይውላል።

በየመን የሚገኙ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ያሉት ኤደን ከተማ ውስጥ ነው የሚለው መሐመድ፣ በዚያ ሕይወት ከባድ መሆኑን ያስታውሳል።

ለመሐመድም ሆነ ለሌሎች ፍልሰተኞች በስደት ጉዞ ውስጥ ሞት የማይታለፍ ዕጣ ፈንታ ነው። በየመን ሲኖርም ሞትን በቅርብ ርቀት፣ በግጭቶች መካከል፣ በሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች አፈሙዝ ጫፍ ተመልክቶታል።

የመን ያለ ሥራ ከሁለት ዓመት በላይ ይህንን ሲታዘብ የቆየው መሐመድ ወደ ቤተሰቦቹ ስልክ ደውሎ ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ ማስላኩን ለቢቢሲ ገልጿል።

“እንደምንም አገሬ ተመልሼ እዚያ መኖር አለብኝ ብዬ ነው ከየመን ለመውጣት የወሰንኩት” ይላል።

ልክ አንደሱ የየመን ስደት ኑሮ በቃኝ ያሉ 77 ስደተኞች ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል በጀልባ ተሳፍረው በቀይ ባሕር ወደ ጂቡቲ ጎዶሪያ ባሕር ዳርቻ መጡ።

በጀልባው ላይ ከተሳፈሩት መካከል ሴቶች የሚገኙ ሲሆን አንዷ የሰባት ወር ልጇን ታቅፋ ነበር በአደገኛው ባሕር ላይ ጉዞ የጀመሩት።

ፍልሰተኞቹን አሳፍራ ወደ ጂቡቲ የባሕር ዳርቻ ተቃርባ የነበረችው ጀልባ፣ ከስሯ ቋጥኝ እንደመታት መሐመድ ያስታውሳል።

ጀልባዋን በቅርብ ርቀት ዋዳለው የባሕር ዳርቻ በመውሰድ ተሳፋሪዎቹን ምቹ ቦታ ላይ ለማውረድ ባለመቻላቸው ገመዳቸውን ዘርግተው ለመቆም ተገደዱ።

ዙሪያቸውን በውሃ ተከበው መውጪያ የጠፋቸው ፍልሰተኞች በድንገት ማንነታቸውን እና ከየት እንደመጡ ያልለይዋቸው ታጣቂዎች መጡባቸው።

እነዚህ ታጣቂዎች ጀልባዋ ከቋጥኝ ጋር ተጋጭታ ጉዞዋን መቀጠል ተቸግራ ሲመለከቱ ተጠግተው ገመዷን በመቁረጥ ወደ ባሕሩ መሀል እንደገፏቸው መሐመድ ይናገራል።

ታጣቂዎቹ ወደ ባሕሩ ሲመልሷቸው እና ሊገለበጡ እንደሆነ ሲረዱ ሁሉም በየሃይማኖቱ ልመና እና ጸሎት እንደያዘ ያስታውሳል።

ሁሉም የእርዱን ጩኸቱን ማሰማት ጀመረ።

“እኛ በአላህ እንላለን፤ ክርስቲያኖቹ እግዚአብሔርን ፍሩ ሲሉ ታጣቂዎቹን ይለምናሉ” ይላል መሐመድ።

ታጣቂዎቹ ግን ጀልባዋ ወደ ባሕር ዳርቻው እንድትጠጋ አልፈለጉም። በዚህ መካከል ትርምስ ሆነ እና ጀልባዋ ተገለበጠች።

በባሕሩ ውስጥ የሰመጡት ስደተኞች ታጣቂዎቹ እንዲደርሱላቸው ቢጮሁም “ማንም ሊደርስልን አልፈለገም” ይላል።

አክሎም በሐዘን ስሜት “ስንት ወንድሞቻችን ሞቱ መሰለህ። ከአርባ በላይ ሰው ይሆናል የሞተው” ብሏል።

ጀልባዋ ስትገለበጥ የሰባት ወር ሕጻን ልጅ የያዘችው እናት ‘ልጄን አትርፉልኝ’ እያለች ትለምን እንደነበር የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ከተረፉት ሰዎች መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መጀመሪያ ላይ ቢቀበሏትም በኋላ ግን መልሰው ስለሰጧት እናትም ልጅም ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሞተዋል ሲሉ አክለዋል።

መሐመድ እንዴት እንደተረፈ ሲናገር “ዋና አልችልም፤ ቤንዝን መያዣ ጀሪካን ሳገኝ ወገቤ ላይ አስሬ እርሱ ላይ ሆኜ ውሃውን መግፋት ያዝኩኝ። አጠገቤ የነበሩ አንድ አምስት የሚሆኑ ሰዎች እኔን ይዘው ወደ ባሕር ዳርቻው ቀዘፍን” ይላል።

ከዚህ በኋላ በጂቡቲ ኦቦክ ከተማ የሚገኘው የመንግሥታቱ የስደተኞች ድርጅት ባለሙያዎች ደርሰው ሕይወታቸውን መታደጋቸውን መሐመድ ይናገራል።

በአሁን ሰዓት ጂቡቲ ኦቦክ በሚገኘው የአይኦኤም መጠለያ ጣብያ የሚገኘው መሐመድ “አሁን ፈጣሪ ሕይወቴን አትርፎኛል። ከአሁን በኋላ ወደ ሰው አገር እሻገራለሁ የሚል ሀሳብ የለኝም። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ አገሬን እና ራሴን ማገልገል እፈልጋለሁ” ይላል።

እነ መሐመድ ላይ ያጋጠመው የጀልባ መገልበጥ አደጋ ከመድረሱ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ፣ እንዲሁ ጂቡቲ ወደ የመን እየሄዱ የነበሩ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በተመሳሳይ ተገልብጣ 38 ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ይታወሳል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ(BBC)