ኢራን በእስራኤል ላይ በፈጸመችው ጥቃት ማን አተረፈ? ማንስ ከሰረ?

 “ለኢራን ባዘነበለ መልኩ ውጤቱ አቻ ተጠናቋል።” ይህ ኢራን እስራኤል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ለሰነዘረችው ጥቃት ተንታኞች የሰጡት ሃሳብ ነው።

እንደ እስራኤል ጦር ከሆነ ቴህራን ቅዳሜ ለሊት ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋለች።

የኢራን ጦር ጥቃቱ “ደማስቆ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ለተሰነዘረው ጥቃት ምላሽ” መሆኑን እና “ዓላማውን ማሳካቱን” አስታውቋል።

እስራኤል በሶሪያ መዲና ደማስቆ በሚገኘው በቆንስላዋ ላይ ለፈጸመችው የአየር ጥቃት ከባድ ምላሽ እንደምትሰጥ ኢራን ስትዝት ቆይታ ነበር።

የደማስቆው ጥቃት ሰባት የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባላትን እና የስድስት ሶሪያውያንን ሕይወት ነጥቋል።

እስራኤል ለጥቃቱ ኃላፊነት ባትወስድም ብዙዎች ግን ከጥቃቱ ጀርባ የቴል አቪቭ እጅ እንዳለበት ያምናሉ።

ኢራን እስራኤል ላይ የፈጸመችውን ጥቃት የተሳካ ነው ብላ አወድሳዋለች።

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የአረብ-ኢራን የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አሊ ኑሪ ዛዴህ ግን በጥቃቱ ኢራን ምንም ነጥብ አላስቆጠረችም።

እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ ዒላማውን መምታት ባለመቻሉ የኢራን መንግሥትን ደካማነት አጉልቷል ይላል።

ይህ አስተያየት ግን በኢራን ያሉ አንዳንድ ሰዎች መሳለቂያ አድርገውታል።

ዛዴህ “የሥነ ልቦና ጦርነት” ብሎ የሚጠራውን ጥቃት ኢራን አጠናክራ ብትቀጥል ከዚህ የበለጠ ውጤት ታገኝ ነበር ብሎ ያምናል።

በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የሞሼ ዳያን ማዕከል የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ተመራማሪ ዶክተር ኤሪክ ሩንድትስኪ በበኩላቸው እስራኤል ከፍ ያለ የማስጠንቀቂያ አዋጅ በማስተላለፏ ተሸንፋለች ይላሉ።

ይህም በእስራኤላውያን ዘንድ ጭንቀት እንዲፈጠረ እና ብዙዎችም ተመሳሳይ ዓይነት ጥቃቶች እንዳይደገሙ ሲሉ ፈርተዋል ብሏል።

ዛዴህ ደግሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አሁን የበለጠ ኃይለኛ እንደሆኑ ይሰማቸዋል ብሏል። ከቅዳሜ በፊት በርካታ ትችት ያስተናገዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጥቃቱ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከሌሎች ምዕራባውያን አገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ረድቷቸዋል።

እስራኤላዊው ተመራማሪ በጥቃቱ እስራኤል ያገኘቻቸው አንዳንድ ጥቅሞች ሊኖሩ ቢችሉም፣ በሌሎች መንገዶች ግን ሽንፈትን አስተናግዳለች ብሏል።

እስራኤል የመካከለኛው ምሥራቅ የኃይል አሰላለፍን አለመገንዘቧን እና ኢራን በድንበሮቿ ጥቃት እንዳታደርስ መከላከል አለመቻሏን ያሳያል ብሎም ያምናል።

እስራኤላዊው ተመራማሪ ኤሪክ ሩንድትስኪም የኢራን ጥቃት ለእስራኤል ትርፍ እንዳለው ያምናል። እስራኤል ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የምዕራባውያንን ድጋፍ እያገኘች ስለሆነ በፖለቲካው ረገድ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብሏል።

ውጥረቱ እስራኤል ወደ እነዚህ አገራት በተለይም ወደ አሜሪካ “እቅፍ” እንድትመለስ ሊያስችላት ይችላል ይላል።

በአንፃሩ ኢራናዊው ተመራማሪ አሊ ኑሪ ዛዴህ ደግሞ ቴህራን ከውስጥም ከውጭም በፖለቲካ ተሸንፋለች ብሎ ያምናል።

ኢራን የጎረቤት አገራትን ድጋፍ አጥታለች። ከየትኛውም አገር ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳልነበራትም ተናግሯል። ኢራንን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ወደ ቀጥተኛ ጦርነት ለመጎተት ከአንዳንድ ወገኖች ሙከራዎች መኖራቸውንም ጠቅሷል።

ሁለቱ ተመራማሪዎች በየአገራቱ ውስጣዊ ግፊት መኖሩን ያምናሉ።

በእስራኤል ውስጥ ትልቅ ስጋት እንዳለ ራንድስኪ ጠቁሟል። ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ እና በውስጣዊ የፖለቲካ ጉዳዮች የተነሳ ቁጣው እየተባባሰ መምጣቱን ገልጿል። በጋዛ ታግተው የነበሩ ዜጎችን ለማስለቀቅ የተደረገው ሙከራ ለውጥ ባለማሳየቱም ችግሩ ተባብሷል።

የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አሊ ካሜኒህ በጎዳና ላይ ብቻ ሳይሆን በአገዛዙ ውስጥ ካሉ ታዋቂ ሰዎችም ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው እንደሆነ ዛዴህ ያምናል።

“የአል-ቁድስ ብርጌድ ሰባት መሪዎች በእስራኤል ከተገደሉ በኋላ በኢራን አብዮታዊ ዘብ እና በኢራን ታጣቂ ኃይሎች የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት አለ።”

ጡረተኛው የሊባኖስ ጄኔራል ሂሻም ጃበር “የጥቃቱ አስገራሚው ነገር፤ አስገራሚ አለመሆኑ ነው” ሲል ለቢቢሲ ኒውስ አረቢክ ተናግሯል።

ምክንያት ያለው ደግሞ ለሁለት ሳምንታት የዘለቀው “የሥነ ልቦና ጦርነት” የአየር ድብደባውን በማስከተሉ እና እስራኤል “በችግር ጊዜ” ውስጥ በመሆኗ ነው ብሏል።

ይህም በርካታ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ በማድርጉ እና በርካታ እስራኤላውያን ዜጎች ቤታቸውን ለቀው በመውጣታቸው ምክንያት ሥነ ልቦናዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል ይላል።

የእስራኤልን ግዛት የማጥቃት ችሎታዋን ለማሳየት እና የእስራኤልን የአየር መከላከያ ዝግጁነት ለመፈተሽ የተደረገ “በእሳት የተላለፈ መልዕክት ነው” በማለት የኢራንን “ዘመቻ” ጃበር ገልጾታል።

“ስትራቴጂያዊ የትዕግስት ፖሊሲ” ብሎ የሰየመውን የኢራንን የቅርብ ዓመታት አካሄድ ተከትሎ ጥቃቱ በአንዳንድ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የጠፋውን ክብሯ እንድታገኝ አስችሏታል ብሎ ያምናል። ከወታደራዊ እና በስትራቴጂ ረገድም ተጠቃሚ አድርጓታል።

ኢራን የእስራኤልን የአየር መከላከያዎች ለማደናገር በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መጠቀሟን የሊባኖሱ ወታደራዊ ኤክስፐርት ያምናል።

የእስራኤል አይረን ዶም ብቻውን ሁሉንም ሚሳኤሎች ማክሸፍ አለመቻሉን እና በመካከለኛው ምሥራቅ በሰፈሩት የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም ኃይሎች ለመታገዝ መገደዷንም ጠቁመዋል።

“እስራኤል ወታደራዊ ምላሽ ከመረጠች በሚሳኤሎቿ ወደ ኢራን ድንበር መድረስ ብትችልም የሚከተለውን የኢራን ምላሽ በመፍራት በጥልቀት ገብታ አታጠቃም” ብሏል ጃበር።

“የእስራኤል አውሮፕላኖች ኢራንን ሊያጠቁ ይችላሉ። ይህንን ለማሳካት ግን በአረብ አገራት ላይ መብረር አለባቸው። ይህንን ደግሞ ኢራን አስጠንቅቃለች። ሌላው የቴል አቪቭ አማራጭ በአካባቢው ካሉ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በመነሳት ጥቃት መፈጸም ቢሆንም ዋሽንግተን ግን ይህን የምትፈቅድ አይመስለኝም” ብሏል።

በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ፋዋዝ ጌርገስ በበኩላቸው ከኢራን አንጻር እስራኤል ከእነዚህ ጥቃቶች የበለጠ ትርፍ አግኝታለች ብለው ይከራከራሉ።

የኢራን ጥቃት በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ወይም ውድመት አላደረሰም። ምዕራባውያን አገራትም እስራኤልን እየደገፉ መሆኑን ገልጸዋል። ምዕራባውያን ለእስራኤል የጦር መሳሪያ፣ የስለላ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ አሜሪካ እየሞከረች ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለእስራኤል ድጋፍ ለማሰባሰብ የቡድን ሰባት (ጂ7) አገራትን አስቸኳይ ጉባኤ በመጥራት አገሪቱን ተጎጂ ተደርጋ እንድትታይ ማድረጋቸውን ጌርገስ ተናግሯል።

“ኔታንያሁ ለጊዜውም ቢሆን በጋዛ ከተፈጠረው ሁኔታ የትኩረት አቅጣጫውን በማስቀየር በፖለቲካው ዘርፍ ያተርፋል” ብሏል።

ምዕራባውያን አገራት እስራኤልን በጋዛ ላይ በፈጸመችው “ግፍ” ላይ ከፍተኛ ትችት ሲሰነዝሩ መቆየታቸውን ተከትሎ ኔታንያሁ ከምዕራቡ ዓለም ጋር በተለይም ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደነበረበት መመለስ እንደሚጠቅማቸው ጠቁሟል።

ጌርጌስ የእስራኤልን ኪሳራም ተመልክቷል። የአገሪቱን ተጋላጭነት በማንሳት ይህ ስትራቴጂያዊ ኪሳራ ነው በማለት አጉልቶ አሳይቷል።

ኢራን በበኩሏ ከእስራኤል ጋር በቀጥታ ለመፋለም ያላትን ፍላጎት ለሕዝቦቿ፣ ለአጋሮቿ እና ለጠላቶቿ በማሳየት በፖለቲካው ዘርፍ ተጠቅማለች ብሏል።

አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ዮርዳኖስ በርካታ የኢራን ሚሳኤሎችን ማክሸፋቸውን በማንሳት እስራኤል በምዕራባውያን አጋሮቿ ድጋፍ ካልሆነ በቀር ራሷን ለብቻዋ መከላከል እንደማትችል ቴህራን አረጋግጣለች ብሎ ጌርገስ ያምናል።

እስራኤል ባለፉት ጊዜያት በኢራን ላይ ስታደርግ የነበረው ተደጋጋሚ ጥቃት ዋና አላማ ቴህራን ደካማ መሆኗን እና ግጭትን እንደምትፈራ ለማሳየት ነበር። ጥቃቶቹ ግን ይህንን አመለካከት ሰብረውታል ብሏል።

“አካባቢው አሁን በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል” ያለው ጌርገስ፤ ሁለቱም አገራት በዚህ እንደማያቆሙ እየዛቱ ነው።

አካባቢው በፖለቲካ፣ በወታደራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ቋፍ ላይ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(BBC)