ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የደረሰችው የቱርክ የጦር መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ ደረሰች

ከጥቂት ወራት በፊት በሶማሊያ እና በቱርክ መካከል የተደረሰውን የወታደራዊ ትብብር ስምምነትን ተከትሎ የቱርክ ባሕር ኃይል የጦር መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ ደረሰች።

ሁለቱ አገራት ባለፈው የካቲት 1/2016 ዓ.ም. በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች ትብብር ለማድረግ ስምምነት መፈራረማቸውን ይታወሳል።

የዚህ ስምምነት ዝርዝር ይፋ ባይሆንም ቱርክ የሶማሊያን ባሕር ኃይልን ለማሠልጣን እና ለማስታጠው እንዲሁም በአካባቢው ያለውን የባሕር ላይ ደኅንነት ለማስጠበቅ ተስማምታለች ተብሏል።

በአንጻሩ ቱርክ ከሶማሊያ የባሕር የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ እንደምትሆን ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ሶማሊያ እና ቱርክ ይህን የወታደራዊ ትብብር ስምምነት የተፈራረሙት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ አጠቃቀም ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ነው።

ይህ በኢትዮጵያ እና በሶኣመሊላንድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ሞቃዲሾን በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን፤ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ነው ስትል ተቃውሞዋን ስታሰማ ቆይታለች።

ሶማሊያ ይህንን ስምምነት ተከትሎ ከተለያዩ አገራት ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ የቆየች ሲሆን፣ ከቱርክ ጋርም ወታደራዊ ስምምነት ያደረገችው በዚህ ወቅት ነው።

የሶማሊያ እና የቱርክ መከላከያ ሚኒስትሮች አንካራ ላይ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ ስምምነቱ በሶማሊያ ፓርላማ ጸድቆ የቱርክ ባሕር ኃይል መርከብ በሶማሊያ የባሕር ክልል ውስጥ ይሰማራል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።

ማክሰኞ ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም. ዓይነቷ ያልተገለጸች ግዙፍ የቱርክ የጦር መርከብ ወደ ሞቃዲሾ ስትደርስ በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቱርክ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙነት “ከወዳጅነትም የበለጠ ነው” ብለዋል።

ለመርከቧ በተደረገው የአቀባብል ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ሐሰን ባደረጉት ንግግር፤ በቱርክ መንግሥት እና ሕዝብ ድጋፍ “ሶማሊያ የባሕር ግዛቷን በራሷ የባሕር ኃይል የምትቆጣጠርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም” ብለዋል።

“የሶማሊያ ሕዝብ በራሱ መንግሥት እና በወዳጅ አገር ቱርክ ላይ መተማመን አለው። . . . በአገራችን በሰብዓዊ እርዳታ ሥራ ላይ በስፋት የተሰማሩት ቱርኮች ናቸው።”

“. . . የሶማሊያ እና ቱርክ ግንኙነት በጣም ጥልቅ ነው። ወንድም ሕዝቦች ነን፣ ተመሳሳይ ሃይማኖት፣ አለመላከከት፣ ባሕል እና ታሪክ እንጋራለን” ሲሉ ፕሬዝዳንት ሐሰን ተናግረዋል።

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በሶማሊያ የቱርክ አምባሳደር አልፐር አክታስ የጦር መርከቧ ወደ ሶማሊያ የመጣችው ሁለቱ አገራት የተፈራረሙትን ወታደራዊ ትብብር ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ “ይህም ወዳጅነታችን ምን ያክል ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል” ካሉ በኋላ “የሶማሊያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የተቻለንን ሁሉ አድርገናል። ይህንም ማድረጋችንን እንቀጥላለን። የሶማሊያ ደኅንነት የቱርክ ደኅንነት ማለት ነው” ብለዋል።

የሶማሊያ መንግሥት በአልሻባብ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጸምበት ሲሆን፣ እስላማዊው ታጣቂ ቡድንም በርካታ የአገሪቱን ክፍሎች ተቆጣጥሮ ይገኛል።

የሶማሊያ መንግሥት ከአልሻባብ የተጋረጠበትን ስጋት ለመከላከል የኢትዮጵያ ሠራዊትን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ወታደሮች በአገሪቱ ውስጥ ተሰማርተው ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )