በጋዛ ሆስፒታሎች የጅምላ መቃብር መገኘቱን ‘አስደንጋጭ’ ሲል የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ!!!!!

በጋዛ ናስር እና አል-ሺፋ ሆስፒታሎች ላይ የደረሰው ውድመት እና ከእስራኤል ወረራ በኋላ በሆስፒታሎቹ “የጅምላ መቃብሮች” መገኘታቸው “አሰቃቂ” ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ገለጹ።

ቮልከር ቱርክ በሟቾች ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግም ጠይቋል።

የፍልስጤም ባለስልጣናት በናስር ሆስፒታል በጅምላ የተቀበሩ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎችን አስከሬን ማውጣታቸውን ተናግረዋል። ሰዎቹ እንዴት እንደሞቱ እና መቼ እንደተቀበሩ ግን ግልጽ አይደለም።

የእስራኤል ጦር አስከሬኖቹን ቀብሯል መባሉን “መሰረተ ቢስ” ሲል አጣጥሎታል።

ጦሩ በዃን ዮኒስ ከተማ በሚገኘው ሆስፒታል ለሁለት ሳምንታት በቆየ ዘመቻ ወቅት ታጋቾች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠርጠሩ በፍልስጤማውያን የተቀበሩ አስከሬኖችን “መመርመሩን” አስታውቋል።

ከእገታ ነጻ የወጡ 10 ታጋቾች በናስር ሆስፒታል ለረጅም ጊዜ ተይዘው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር በናስር ካደረገው ዘመቻ በፊት በአካባቢው በነበረው ጦርነት ምክንያት ወደ መቃብር ስፍራዎች መሄድ ባለመቻላቸው በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ አስከሬን ለመቅበር ተገድደው እንደነበረ የሆስፒታሉ ባልደረቦች ገልጸው ነበር።

የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚገኙ በርካታ ሆስፒታሎች ወረራ የፈጸመው የሐማስ ተዋጊዎች ስለሚንቀሳቀሱባቸው ነው ቢልም ታጣቂ ቡድኑ እና የህክምና ባለስልጣናት ይህን ያስተባብላሉ።

ጦርነቱ የተጀመረው የሐማስ ታጣቂዎች መስከረም 26 በደቡባዊ እስራኤል ድንበር ተሻግረው በፈጸሙት ጥቃት አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደሉ እና 253 ሰዎችን አግተው ወደ ጋዛ ከወሰዱ በኋላ ነበር።

ጦርነቱን ተከትሎ አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ34 ሺህ 180 በላይ ሰዎች በጋዛ መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ በአሁኑ ወቅት የፍልስጤም ባለስልጣናት 283 አስከሬኖች በናስር ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ መገኘታቸውን የሚያረጋግጡ ሪፖርቶችን ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ የ42 ሰዎች ማንነት ተለይቷል።

ራቪና ሻምዳሳኒ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ሟቾች በጥልቅ በተቆፈሩ ቦታዎች መቀበራቸውን እና ቆሻሻ እንዲለብሱ ተደርጓል” ብለዋል።

“ከሟቾቹ መካከል በዕድሜ የገፉ፣ ሴቶች፤ … ሌሎች ደግሞ እጃቸውን ታስረው ልብሳቸውን ተገፈው ተገኝተዋል” ብለዋል።

ቱርክ በሟቾቹ ዙሪያ ገለልተኛ፣ ውጤታማ እና ግልጽ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። “በአሁኑ ወቅት ካለው የጥፋተኝነት ሁኔታ አንጻር ዓለም አቀፍ መርማሪዎችን ማካተትም ይገባል” ሲሉ አክለዋል።

“ሆስፒታሎች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ልዩ ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው። በጦር ቀጠና ውስጥ በማይገኙ በሠላማዊ ሰዎች ላይ፣ እስረኞች እና ሌሎችም ላይ ሆን ተብሎ ግድያ መፈጸም የጦር ወንጀል ነው።”

ሐማስ ማስረጃ ሳያቀርብ አስከሬኖቹ በእስራኤል ወታደሮች “በግፍ የተገደሉ” ሰዎችን ያካትታል ሲል ከሷል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ማክሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ “ጦሩ የፍልስጤማዊያንን አስከሬን ቀበሯል የሚለው አባባል ያልተረጋገጠ እና መሠረተ ቢስ ነው” ብሏል።

“ዘመቻው የተካሄደው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እና ታግተው የተወሰዱ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በተጠረጠሩ ቦታዎች ላይ ብቻ ነው። ምርመራው የተካሄደው የሟቾችን ክብር በጠበቀ መልኩ ነው። የእስራኤል ታጋቾች ያልሆኑ አስከሬኖችም ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል” ብሏል።

“በሆስፒታል የነበሩ 200 የሚጠጉ አሸባሪዎችን” በቁጥጥር ስር ማዋሉን ጦሩ ገልጾ፤ ጥይቶችን እና ለእስራኤላውያን ታጋቾች የታሰቡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መድኃኒቶችን ማግኘቱን ገልጿል።

ዘመቻው የተፈፀመዉ በሆስፒታሉ፣ በህሙማንና በህክምና ባለሙያዎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ መሆኑንም ገልጿል።

በዘመቻው ወቅት ከታሰሩ በኋላ ለሰዓታት ተዋርደው፣ ድብደባ፣ ቀዝቃዛ ውሃ ሲፈስባቸው እና ለመንበርከክ መገደዳቸውን ሦስት የሕክምና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስራኤል ሆስፒታሉን ከተቆጣጠረች በኋላ በናስር ሆስፒታል የቆዩ የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ታማሚዎችን መንከባከብ እንዳልቻሉ እና 13 ሰዎች በውሃ፣ በኤሌትሪክ እና በሌሎች አቅርቦቶች እጦት ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ሐማስ በሆስፒታሉ መሰባሰቡን በመግለጽ ሌላ “ውጤታማ” ዘመቻ ማከናወኑን በመግለጽ እስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ካለው አል-ሺፋ ሆስፒታል ለቆ ወጥቷል።

በሆስፒታሉ ውስጥ እና በአካባቢው 200 “አሸባሪዎች” ተገድለዋል ሲል ጦሩ በወቅቱ ተናግሯል። ከ500 የሚበልጡ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የጦር መሳሪያዎች እና መረጃዎች “በሆስፒታሉ ውስጥ” ተገኝተዋል ሲልም አክሏል።

ከአምስት ቀናት በኋላ ቦታውን መጎብኘት የቻለው የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አል-ሺፋ “ባዶ ቀፎ” መሆኑን ገልጿል።

ከድንገተኛ ክፍል፣ ከአስተዳደር እና ከቀዶ ጥገና ህንጻዎች አጠገብ “ብዙ ጥልቀት የሌላቸው መቃብሮች ተቆፍረዋል፣ ብዙ አስከሬኖች በከፊል ብቻ ተቀብረዋል” ብሏል።

ጦሩ በአል-ሺፋ በታካሚዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረጉንም ገልጿል። የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የሆስፒታሉ ተጠባባቂ ዳይሬክተርን ጠቅሶ በዘመቻው ወቅት ህሙማን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ እና ቢያንስ 20 ታካሚዎች በእንክብካቤ እጥረት እና በነበረው የእንቅስቃሴ ውስንነት ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል ብሏል።

የጋዛ ሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ በአል-ሺፋ አካባቢ 381 አስከሬኖች መገኘታቸውን ነገር ግን ቁጥሩ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ የተቀበሩ ሰዎችን እንደማያካትት ለሲኤንኤን አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ባለፉት ጥቂት ቀናት እስራኤል በደቡባዊቷ ራፋህ ከተማ ላይ ያደረሰችውን ተከታታይ ጥቃት “ከጦርነት በላይ” ሲሉ ገልጸውታል።

ቅዳሜ ምሽት በተሰነዘረ አንድ ጥቃት ከባለቤቷ እና ከሴት ልጇ ጋር ከተገደለች ነፍሰ ጡር እናት ማህጸን ውስጥ ያለጊዜዋ የተወለደች ህፃን ለማዋለድ ተችሏል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(BBC)

 

 

Show Buttons
Hide Buttons