ከራያ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እና አመራሮች ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ናቸው?

በአወዛጋቢዎቹ የራያ አካባቢዎች ያለውን ባለው አለመረጋጋት ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቆቦ፣ በሰቆጣ፣ በወልዲያ እና በሐሙሲት ከተማዎች መጠለላቸውን ተፈናቃዎች እና በአማራ ክልል የተሾሙት የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከትግራይ ኃይሎች በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች አለመረጋጋት ውስጥ የገቡት ስድስቱ የራያ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች፤ በአማራ ክልል መንግሥት ስር በተመሠረቱላቸው መዋቅሮች ስር መተዳደር ማቆማቸውን አራት የወረዳዎቹ አመራሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይሎች በተለይም የገጠር ቀበሌዎችን መቆጣጠራቸውን የዛታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን መኮንን እና የወፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ሞላ ገልፀዋል። ይህንን ተከትሎም የሁለቱ ወረዳዎች አመራሮች እና ነዋሪዎች ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የኮረም እና አላማጣ ከተማዎች ነዋሪዎች በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙት ቆቦ እና ወልዲያ ከተሞች እንዲሁም ሰቆጣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር በሚገኙት ሰቆጣ ከተማ እና ሐሙሲት ቀበሌ መጠለላቸውን ገልጸዋል።

ተፈናቃዎቹ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች መጠለላቸውን ተናግረው፤ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው 30 ሺህ ገደማ የራያ አካባቢ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል።

ቢቢሲ ስለተፈናቃዮች መረጃ ለማግኘት ወደ ተጠለሉባቸው ሁለት ዞኖች ኃላፊዎች ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አላገኙም።

የተፈናቃዮች ሁኔታ

ቢቢሲ ካነጋገራቸው ተፈናቃዮች እና የወረዳዎቹ ኃላፊዎች ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አብዛኞቹ የራያ አካባቢዎች ተፈናቃዮች የሚገኙት በሰሜን ወሎዋ ቆቦ ከተማ ነው። በተለይም ከራያ አላማጣ እና ራያ ባላ ወረዳዎች እንዲሁም አላማጣ እና ኮረም ከተሞች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቆቦ ውስጥ እንደሚገኙ የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ወደ ከተማዋ የመጡ ተፈናቃዎች ከቆቦ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኝ የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ በሚገኙ ሼዶች ውስጥ እንዲጠለሉ መደረጉን ተፈናቃዎቹ ተናግረዋል። ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ በዘመድ ቤት፣ በሆቴሎች እንዲሁም በረንዳዎች ላይ መጠለላቸውን አቶ ጥላሁን አኪያ የተባሉ ግለሰብ ገልፀዋል።

ወደ ከተማዋ በጎረፉት ተፈናቃዎች ምክንያት ቆቦ ከተማ መጨናነቋን የሚናገሩት አቶ ጥላሁን፤ “ከከተማዋ አቅም በላይ ሕዝብ ተጨምሮ በሄድክበት ሁሉ ወንበሮች ሙሉ ናቸው። ሁሉም ቦታ በሰውም፣ በባጃጅም ተጨናንቋል። የተፈናቃይ መምጣትን ተከትሎ እንደ ሻይ፣ ምግብ ቤት የሚከፈቱ አሉ። የማረፊያ ቦታ ታጥተው ወደ ሮቢት የሚሄዱም አሉ። አልጋ ጭራሹኑ አይገኝም” ሲሉ የከተማዋን ሁኔታ ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ ሰዎች ከተጠለሉባቸው ከተሞች አንዷ ሰቆጣ
የምስሉ መግለጫ, የተፈናቀሉ ሰዎች ከተጠለሉባቸው ከተሞች አንዷ ሰቆጣ

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በኢንዱስትሪ መንደር እና ከተማዋ ውስጥ የተጠለሉ ነዋሪዎች ከማኅበረሰቡ ከሚደረግላቸው ድጋፍ ውጪ እስካሁን ድረስ ከመንግሥት እርዳታ እንዳልቀረበላቸው አስረድተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የምግብ እርዳታ ያልቀረበላቸው በወልዲያ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች በአንጻሩ፤ የመጠለያ ጣቢያም አንዳልተዘጋጀላቸው አንድ ተፈናቃይ ለቢቢሲ ገልፀዋል። ከኮረም ከተማ እና ወፍላ ወረዳ ብቻ ወደ ወልዲያ የመጡ ተፈናቃዮች ብዛት ከ500 በላይ እንደሆነ የሚናገሩት ተፈናቃዩ፤ “የተወሰኑ ቤተሰብ፣ ጓደኛ ያላቸው የተጠጉ ይኖራሉ። በየአልጋ ቤት፤ አብዛኛው በረንዳ ላይ ነው ያለው ማለት እንችላለን። ምንም የተሰጠን ነገር የለም” ሲሉ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ አብራርተዋል።

“ተወካዮቻችን ዛሬ [አርብ] ጠዋት የዞን አስተዳዳሪዎች ጋር ሄደው ነበር። ‘ምንም የምናደርገው ነገር የለም፤ የሚመጡ አንዳንድ ድጋፎች ካሉ ቆቦ አካባቢ ወደ አንድ ማዕከል መሆን አለባችሁ’ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል” ሲሉም አክለዋል።

ከኮረም ከተማ እና ዛታ ወረዳ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሌላኛው አካባቢ በዋግ ኽምራ ውስጥ የሚገኘው ሐሙሲት ቀበሌ እንደሆነ ሁለት ተፈናቃዮች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ተፈናቃዮች ከኮረም ከተማ 45 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ሐሙሲት መሰባሰብ የጀመሩት ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ መሆኑን የዛታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

ወደ ሐሙሲት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በአቅራቢያው በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ወስጥ እንዲጠለሉ መደረጋቸውን አንድ ከኮረም ከተማ የተፈናቀለ ነዋሪ ገልጿል። “ምንም የተደረገልን እገዛ የለም። የአካባቢው ሰው የሚችለውን አንድም እንጀራ [እየሰጠ] እያገዘን ነው። እርስ በእርሳችም እየተጋገዝን ነው ያለው” ሲል ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ አስረድቷል።

የተፈናቀሉት የራያ ወረዳ አመራሮች

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ የማንነት ጥያቄ ይነሳባቸው የነበሩት የራያ አካባቢዎች በአማራ ክልል ስር መግባታቸው ይታወሳል። የክልሉ መንግሥት በእነዚህ አካባቢዎች መዋቅሩን ዘርግቶ፤ በሾማቸው አመራሮች ወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮቹ እንዲመሩ አድርጎ ቆይቷል።

ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ግን እነዚህ አመራሮች አካባቢዎቹን ለቅቀው ወጥተዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዛታ እና ወፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የአላማጣ እና ኮረም ከተማ ከንቲባዎች ከተፈናቃዮች ጋር አንድ ላይ መጠለላቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር አመራሮችም በተመሳሳይ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ተናግረዋል። በራያ አላማጣ ወረዳ እና አላማጣ ከተማ ከ60 በላይ የወረዳ እና ቀበሌ አመራሮች ኃላፊነት ላይ እንደነበሩ የሚናገሩት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ፤ ሁሉም አመራሮች ከአካባቢው ለቀው መውጣታቸውን አመልክተዋል።

የዛታ ወረዳም ካሉት 18 አመራሮች ውስጥ 16ቱ መውጣታቸውን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን ጠቅሰዋል። በወፍላ ወረዳ ውስጥ የነበሩት ከ40 በላይ አመራሮችም በተመሳሳይ አካባቢውን ለቅቀው ወደ ቆቦ፣ ሰቆጣ እና ወልዲያ አካባቢዎች መሄዳቸውን የወፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የተፈናቀሉት አመራሮች ከዞን መስተዳደር ጋር ንግግር እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፍሰሐ፤ “እነዚህን ውይይቶች እንደጨረስን በቀጣይ ቀናት ውስጥ አዲስ ነገር ይኖራል” ብለዋል።

ከዞን አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ያረጋገጡት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ በበኩላቸው፤ የመንግሥትን አቅጣጫ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የወሰን እና የማንነት ጥያቄ ሲነሳባቸው ከነበሩ ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነው የራያ አላማጣ አካባቢ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ በአመራ ክልል ስር ገብተው ቆይተዋል።

ለአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች መፍትሔ ለመስጠት በሚል የፌደራል መንግሥቱ በቦታዎቹ ላይ ያሉት መስተዳደሮች ፈርሰው፣ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ተመልሰው ሕዝቡ የራሱን አስተዳደር እንዲመሠርት እንደሚደረግ በተደጋጋሚ ገልጿል።

በራያ አላማጣ አካባቢ ባለፉት ጥቂት ወራት በትግራይ እና በአማራ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ሲካሄዱ የቆዩ ሲሆን፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ የሰው ሕይወት የጠፋበት ግጭት አጋጥሞ ነበር። የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎችም ወደ ከተማዋ መግባታቸውን፤ የትግራይ ኃይሎች ደግሞ ከከተማ ውጪ ባሉ አካባቢዎች መግባታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጄኔራል ታደሠ ወረደ፣ በአካባቢዎቹ በአማራ ክልል የተቋቋሙ አስተዳደሮችን ለማፍረስ በፌዴራል መንግሥቱ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ስምምነት መደረሱን ተናግረው ነበር።

የአማራ ክልል መንግሥት ደግሞ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ ላይ ወረራ ፈጽሟል ሲል መክሰሱ ይታወሳል።

ደም አፋሳሹ የእርስ በርስ ጦርነት ከቆመ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ አስካሁን ያለው ነገር የለም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(BBC)