አባ ገዳ ጎበና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል የሆነው ልጃቸው መገደሉን ከማኅበራዊ ሚዲያ መስማታቸውን ተናገሩ

የቱለማ አባ ገዳ የሆኑት አባ ገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል የሆነው ልጃቸው መገደሉን ከማኅበራዊ ሚዲያ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከአንድ ሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው ቡድን አባል ነው ያለው የአባ ገዳ ጎበና ልጅ “ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል ሲንቀሳቀስ እርምጃ ተወስዶበታል” ብሎ ነበር።

ይህን የዞኑ መግለጫን ተከትሎ በኦሮሞ ባሕላዊ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ስፍራ በሚሰጠው ገዳ ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸው የአባ ገዳ ጎበና ልጅ የመገደል ዜና ብዙዎችን ሲያነጋግር ቆይቷል።

የቱለማ አባገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ኅብረት ፀሐፊ የሆኑት አባ ገዳ ጎበና ሆላ፣ ፎሌ ጎበና የሚባለው ልጃቸውን መገደል የሰሙት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚሠራጨው ወሬ መሆኑን እና አስካሁን ምንም ማረጋገጫ እንዳላገኙ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋል።

የምዕራብ አርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ሚያዝያ 6/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ፤ “የኦሮሞ ልጆችን ሕይወት ሲቀጥፍ የነበረው የአባ ገዳ ጎበና ሆላ ልጅ ላይ እርምጃ ተወሰዷል” ብሎ ነበር።

የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጨምሮም፤ “ፎሌ ጎበና ሆላ የተባለው የአባ ገዳ ጎበና ሆላ ልጅ በምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ ውስጥ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ለመቅጠፍ ሲንቀሳቀስ” እንደነበረ እና በፀጥታ ኃይሎች “እርምጃ እንደተወሰደበት” አመልክቷል።

አባ ገዳ ጎበና የልጃቸውን ሞት ባያረጋግጡም በእርግጥ ልጃቸው መንግሥት ኦነግ-ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን አባል መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልጃቸው ፎሌ ዕድሜው ወደ 33 ዓመት እየተጠጋ መሆኑን እና ከልጃቸው ጋር ከተያዩ ስድስት ዓመታት ማለፋቸውን አባገዳው ገልጸዋል።

“ከስድስት ዓመታት በኋላ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ከቀናት በፊት ፎቶ ግራፉን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የተመለከትኩት።

“የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ውስጥ እንዳለ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ምንም ግንኙነት የለንም። የት እንዳለም አላውቅም። መገደሉን በተመለከተም ገድዬዋለሁ ያለውን መጠየቅ ነው የሚሻለሁ” ብለዋል።

የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ይህ የአባ ገዳው ጎበና ሆላ ልጅ በአካባቢው በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመዘዋወር ግድያዎችን ሲፈጽም ቆይቷል ሲል ከሶታል።

አባ ገዳ ጎበና ግን ልጃቸው ተገድሏል ከመባሉ በተጨማሪ መንግሥት ስለሚያቀርብበት ክስ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

“እኔ አባ ገዳ ነኝ አልዋሽም፤ ከልጄ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም። ስልክ አንደዋወልም። ከስድስት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ፎቶግራፉን እንኳ የተመለከትኩት።”

የአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል የሆነው እና የአባገዳው ሰባተኛ ልጃቸው የሆነው ፎሌ ጎበና ከቤት የወጣው የ26 ዓመት ወጣት ሳለ እንደነበረ አባቱ ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አባ ገዳ ጎበና ልጃቸው ወደ ትጥቅ እንቅስቃሴ መግባቱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ መኖሪያ ቤታቸው ላይ ብርበር ማድረጋቸውን ሲናገሩ ነበር።

ከጥቂት ወራት በፊት አባ ገዳ ጎበና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቤታቸው ላይ ብርበራ በተደረገበት ወቅት ከወላጅ አባታቸው የወረሱት የጦር መሳሪያ መወሰዱን እና ክስተቱን ተከትሎ በቤተሰብ አባላት ላይ ከፍተኛ መደናገጥ መፈጠሩን ተናግረው ነበር።

አባ ገዳ ጎበና ከቀድሞ የቱለማ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ መስከረም 20/2011 ዓ.ም. በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነውን ባሕላዊ ሥልጣንን መረከባቸው ይታወሳል።

በገዳ ሥርዓት መሠረት አባ ገዳ ጎበና የቱለማ አባ ገዳ ሆነው እስከ 2019 ዓ.ም. ድረስ በስልጣን ላይ ይቆያሉ።

በአሁኑ ጊዜ ታጣቂ ቡድኖች ከሚንቀሳቀሱባቸው ክልሎች አንዱ በሆነው የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የአባገዳው ልጅ አባል የሆነበት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋነኛው ነው።

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልፍሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው እና መንግሥት ‘ሸኔ’ በማለት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ይከሰሳል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )