በዱባይ ለ26 ዓመታት የኢትዮጵያን የባህል ምግብ ያስተዋወቀው አል ሐበሻ ምግብ ቤት

ዱባይ የደረሰ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአገሩ ምግብ ቢናፍቀው ጎራ ብሎ ጉርስ የሚያደርግበት ነው፤ አል ሐበሻ ሬስቶራንት።

ምግብ ቤቱ በባሕረ ሰላጤዋ አገር ከ26 ዓመት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።

አል ሐበሻ እንደ ዛሬው በየቦታው ሳይስፋፋ በፊት አነስተኛ ምግብ ቤት የነበረው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን በተለያዩ የኤምሬትስ ግዛቶች ዘጠኝ ቅርንጫፎች አሉት።

በሁሉም ምግብ ቤቶች ከ40 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ተቀጥረው ይሠራሉ። አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በዚሁ የምግብ ቤት ሥራ በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ማፍራት የቻለችው ወ/ሮ ሳራ አራዲ፣ አሁን ያለችበት ደረጃ ለመድረስ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት አያሌ ውጣ ውረዶችን አልፋለች።

ሳራ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዱባይ ያመራችው በ1985 ዓ.ም. የ21 ዓመት ወጣት እያለች ነበር። በወቅቱም ከ500 የአሜሪካን ዶላር የማይበልጥ ገንዘብ እና ሠርቶ የመለወጥ ትልቅ ተስፋን ሰንቃ ነበር።

ሳራ ከልጅነቷ ጀምሮ ምግብ የማብሰል ተሰጥዖ እና ፍቅር አላት። ወደ ዱባይ እንድታመራ ያደረጋትም ይህ ሙያዋ ነው።

የልብ ጓደኛዋ ቀደም ብላ ወደ ዱባይ አምርታ ነበር። እንደ ጓደኛ ሲደዋወሉ “ወደ ዱባይ መጥተሽ የምግብ ቤት ሥራ ብትጀምሪ በአጭር ጊዜ ትለወጫለሽ” ትላት እንደነበር ሳራ ታስታውሳለች።

የምግብ ዝግጅት ሙያ እንዳላት ብታውቅም በማታውቀው አገር ሠርታ ለመለወጥ አስቸጋሪ ሊሆንባት እንደሚችል በመገመት የጓደኛዋን ምክር ብዙም ትኩረት አልሰጠችውም ነበር።

ነገር ግን ከጓደኛዋ የሚሰጣት ማበረታቻ እና ግፊት በጊዜ ሂደት ሃሳቧን አስቀየራት።

“ልሞክረውና ካልተሳካ ሌላ አማራጭ እፈልጋለሁ” በሚል ውሳኔ የጓደኛዋን ጥሪ ተቀብላ ወደ ዱባይ አቀናች።

ዱባይ እንደደረሰች ግን ነገሮች ባሰበችው ልክ አልሆኑላትም። ሥራ ለመጀመር ቦታ መርጣ ቤት ተከራየች። የሚከራየውን ቤት ያገናኟት ኢትዮጵያውያን ደላሎች ነበሩ።

የሁለት ወር የቤት ኪራይ ቅድመ ክፍያ እንድትፈጽም ነገሯት። ሥራውን ለመጀመር ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራት የተባለችውን ክፍያ ወዲያውኑ ፈጸመች። ነገር ግን ያ ገንዘብ (ወደ 10 ሺህ ድርሃም አካባቢ) ባለቤቶቹ ጋር አልደረሰም።

ደላሎቹ ይዘውት ተሰወሩ። ሳራ ገንዘቧን ለማስመለስ ብዙ ደከመች፤ አልተሳካላትም።

ድጋሚ ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ ከፍሎ ቤቱን መከራየት እና ሥራውን መቀጠል በሳራ አቅም የሚቻል አልሆነም። እናም ዱባይን ተሰናብታ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች።

ሳራ ወደ ኢትዮጵያ ብትመለስም ዱባይ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል ተረድታለች። ችግር የሆነው ለሥራ መጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘቱ ብቻ ነው።

የተለያዩ ሥራዎችን ብትሞክርም ልቧ ያለው ዱባይ ነው። በዚህም ምክንያት የተወሰነ ገንዘብ አጠራቅማ ድጋሚ ወደ ዱባይ ተመለሰች።

በ1991 ዓ.ም ዱባይ ውስጥ የመጀመሪያውን ‘አል ሐበሻ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት’ ከፈተች።

በወቅቱ በዱባይ የኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ ስለነበር ወደ ምግብ ቤት መጥቶ የሚስተናገድ ደንበኛ ውስን ነበር። ለአገሬው ሰው ደግሞ የኢትዮጵያን ምግብ ማስለመድ ከባድ ሆነባት። በዚህም ምክንያት ዋነኛ ሥራዋ የነበረው ምግብ አዘጋጅቶ ወደ ደንበኞች ቤት ማድረስ ነበር።

ምግብ መሥራት፣ የተሠራውን ወደ ደንበኞች ቤት ማድረስ፣ የምግብ ግብዓቶችን ገበያ ሂዶ መግዛት፣ ከኢትዮጵያ የሚታዘዙ ተጨማሪ ግብዓቶችን ከአየር መንገድ መቀበል የወቅቱ የሣራ የዕለት ከዕለት ሥራዎች ነበሩ።

ምግብ ቤቱ ተጨማሪ የሰው ኃይል የመቅጠር አቅም ስላልነበረው ሁሉንም ሥራዎች የምትሠራው ብቻዋን እንደነበር ታስታውሳለች።

“24 ሰዓት አንዳንዴም ከዚያ በላይ የሚሆን ጊዜ ያለእንቅልፍ አሳልፍ ነበር” ትላለች።

በእርግጥ የሥራ ውጥረት ቢኖርም አዲሱ ምግብ ቤቷ እየተወደደላት ነው። የደንበኞቿ ቁጥርም ጨምሯል። “ፈታኝ ጊዜ ገጥሞኝ ነበር” የምትለው ልጅ በወለደችበት ወቅት ነው።

“ምግብ ቤቱ እንዳይዘጋ እና ያስለመድኳቸው ደንበኞችም እንዳይበተኑ በሚል በወለድኩ በሦስት ወር ውስጥ ነው ወደ ሥራ የተመለስኩት።”

በወቅቱ የባለቤቷ እገዛ እና የሞራል ድጋፍ ያንን ፈታኝ ጊዜ ለማለፍ እንዳስቻላት ትገልጻለች።

“እኔ ወደ ሥራ ስሄድ ባለቤቴ ቤት ልጅ ይይዛል፣ ሥራችን እንዲቀላጠፍም ያበረታኛል” በማለት የባለቤቷን እገዛ ወሳን እንደነበር ታስረዳለች።

በተቃራኒው ሌሎች ጓደኞቿ “ነገ ጥለሽው ለምትሄጅው ነገር ይህንን ሁሉ መድከም አያስፈልግሽም ይሉኝ ነበር” የምትለው ሳራ፣ “የማልመውን ሕልም እውን ማድረግ እፈልጋለሁ፣ ያንን ሕልም ደግሞ እውን ማድረግ የምችለው እንደዚህ በመሥራት ነው” በማለት ለጓደኞቿ ትመልስላቸው ነበር።

ሳራ በዚያን ጊዜ ከምግብ ዝግጅት በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችንም ጎን ለጎን ትሠራ ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛ ኤሌክትሮኒክስ ቤት በመክፈት የሕንድ ፊልሞች የተጫኑባቸው ቪኤችኤስ ካሴቶችን ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች።

ብዙ ደንበኞች ካሴቶቹን በጉጉት ይጠብቁ የነበረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደርም ከደንበኞቿ መካከልም አንዱ ነበሩ።

በኋላም ሞባይል ስልኮችን እና ብራንድ መነጸሮችን በመላክ የንግድ ሥራዋን አጠናክራለች። የምግብ ቤት ሥራው እየተለመደ እና እየተወደደ ሲሄድ ግን ሙሉ ትኩረቷን አል ሐበሻ ሬስቶራንት ላይ አደረገች።

ሳራ የከፈተችው የመጀመሪያው ምግብ ቤት ‘ናይፍ’ ተብሎ በሚጠራው የዱባይ አካባቢ ነበር። ምግብ ቤቷ አነስተኛ ብትሆንም ደንበኞቿ ግን ከመላው ኤምሬትስ የሚመጡ ተስተናጋጆች ነበሩ።

ይህ ለሳራ ገበያ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ነበረው። የደንበኞች ቁጥር ሲጨምር እና ምግብ ቤቱ መወደድ ሲጀምር በዚያች ጠባብ ቤት ብቻ ደንበኞቿን ማስተናገድ አስቸጋሪ ሆነ።

ቅርንጫፍ መክፈት እንዳለባት አመነች። ወዲያውኑ ‘ፍሪጅ ሙራር’ በሚባለው የዱባይ ሰፈር ሁለተኛውን ቅርንጫፍ ከፈተች። ይህ ቅርንጫፍ ወሳኝ እንደነበር ሳራ ታስታውሳለች።

ከዚህ ቅርንጫፍ መከፈት በኋላ የራሷን ተሽከርካሪ እና ሌሎች የምግብ ቤቱ ግብዓቶች ማሟላት ቻለች። አጋዥ ሠራተኞችንም መቅጠር ጀመረች።

የምግብ ቤቱ ትርፍ እየጨመረ ሲሄድ ቀስ በቀስ ሳራ ከኩሽና በመውጣት ሌሎች ሙያተኞችን እየተካች እርሷ ወደ አስተዳደር ሥራው አተኮረች።

በሂደት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለበርካታ አገራት ዜጎች ለኑሮ ተመራጭ እና የቢዝነስ ማዕከል እየሆነች ስትሄድ በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም በተመሳሳይ እየጨመረ መጣ።

በሌላ በኩል የሳራ ምግብ ቤት በአገሬው ዘንድም ተወዳጅነትን አተረፈላት። በእነዚህ ምክንያቶች ሳራ ባሏት ሁለት ቅርንጫፎች ብቻ ዱባይ ላይ መወሰን አልፈለገችም።

ሌሎች የኤምሬትስ ግዛቶችንም አማተረች። አቡ ዳቢ፣ አጅማን፣ ሻርጃ እና ራሰ አልኬማ በተባሉት የተባበሩት ኤምሬትስ ግዛቶች ቅርንጫፎችን ከፈተች።

በአሁኑ ወቅት የሳራ አል ሐበሻ ሬስቶራንት 26 ዓመታትን አስቆጥሯል። ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በፊት ሬስቶራንቱ 11 ቅርንጫፎች ነበሩት።

ነገር ግን በዚያ ወቅት ተስተጓጉሎ በነበረው ትራንስፖርት እና በሌሎች ምክንያቶች ሠራተኞችን ከኢትዮጵያ ማምጣት ለሳራ ከባድ ነበር። በዚህም ምክንያት ሁለት ቅርንጫፎች መዘጋታቸውን ትናገራለች።

ዱባይ እንጀራ አይጋገርም። ሳራም ሆነች ሌሎች ኢትዮጵያውያን የምግብ ቤት ባለቤቶች በተደጋጋሚ ሞክረውት ያልተሳካላቸው ነገር ዱባይ ውስጥ እንጀራ መጋገር ነው።

እንጀራው ዱባይ ሲጋገር ይደርቃል፣ በፍጥነት ጣዕሙ እና ቀለሙ ይቀየራል፤ ከዚያም በላይ የተስተካከለ ቅርጽ ይዞ አይወጣም።

ምናልባት ችግሩ ከውሃው ነው በሚል እሳቤ ውሃ ከአዲስ አበባ ጭነው በመውሰድ ለመጋገር ተሞክሯል። ነገር ግን ያም ቢሆን ለውጥ አላመጣም።

በዚህም ምክንያት አል ሐበሻን ጨምሮ በአረብ ኤምሬትስ የሚገኙ ሁሉም የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች የሚጠቀሙት ከኢትዮጵያ ተጋግሮ የሚሄድ እንጀራን ነው።

ወ/ሮ ሳራ አዲስ አበባ ውስጥ የራሷ እንጀራ መጋገሪያ አላት። በዚህ መጋገሪያ ውስጥ 20 ሴቶች እንጀራ በመጋገር ተቀጥረው ይሠራሉ።

አዲስ አበባ የሚጋገረው እንጀራ በየቀኑ ወደ ዱባይ ይላካል። ከዱባይ ደግሞ ወደ ሌሎች የአረብ ኤምሬትስ ግዛቶች ይሠራጫል። ይህ የዕለት ተዕለት ተግባር ነው።

ከምግብ ቤት ሥራው በተጨማሪ ለሰዎች እና ለሌሎች ምግብ ቤቶችም እንጀራ ያከፋፍላሉ። “አሁን እንጀራ ከጤና አንጻር ጥሩ ነው ስለሚባል እና የአገሬው ሰውም ስለለመደው አረቦች ሁሉ እየመጡ ይወስዳሉ” ትላለች ሳራ።

የአል ሐበሻ ሬስቶራንት ከተከፈተ ጀምሮ በአማካይ ከስምንት መቶ እስከ አንድ ሺህ ኢትዮጵያውያን ሰዎች ተቀጥረው እንደሠሩ ሳራ ትገምታለች።

አሁንም ከብዙዎቹ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት የምትገልጸው ሳራ፣ “ወደ አገር ቤት ከተመለሱት መካከል ከ50 በላይ የሚሆኑት የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ትላለች።

ሳራ የኢትዮጵያን ባሕል በማስተዋወቅም ከፍተኛ ሚና መጫወቷን ታምናለች።

“እስከ ዛሬ ከተቀያየሩት አምባሳደሮች በላቀ አገሬን እንዳስተዋወቅኩ ይሰማኛል” የምትለው ሳራ፣ ከመላው ዓለም ለሚመጡ ደንበኞቿ ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያን ባሕል እንደምትገልጽላቸው ተናግራለች።

በአል ሐበሻ ሬስቶራንት ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የሌሎች አገራት ዜጎችም ተቀጥረው ይሠራሉ። አንዳንዶቹ አማርኛ አቀላጥፈው መናገር ችለዋል። ሌሎቹ ደግሞ እየተኮላተፉ አንዳንድ ቃላትን ይናገራሉ።

ባንግላዲሻዊው ዳዱ በአል ሐበሻ ሬስቶራንት ረጅም ጊዜ ከሚሠሩ የሌላ አገር ዜጎች መካከል አንዱ ነው።

በአል ሐበሻ ሬስቶራንት16 ዓመታትን ሠርቷል። ለረጅም ጊዜ ያሳለፈው በአስተናጋጅነት ነው። አሁን አሽከርካሪ ሆኗል።

ከኢትዮጵያ የሚላከውን እንጀራ ከዱባይ ወደ ሌሎች የኤምሬትስ ግዛቶች ከሚያሠራጩ አሽከርካሪዎች መካከል አንዱ ነው። አማርኛ አቀላጥፎ ይናገራል።

ከሕንድ የመጣው ሌላኛው ጓደኛውም በአል ሐበሻ 17 ዓመታት ሠርቷል። እርሱም አማርኛ ተናጋሪ ሆኗል። አገራቸው የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን የሚደጉሙት ከአል ሐበሽ በሚያገኘው ደሞዝ ነው።

ሳራ አራዲ ያኔ ከ30 ዓመት በፊት ታልመው የነበረውን ሕልሟን አሳክታለች። ጠንክራ መሥራቷ እና የባለቤቷ ድጋፍ የስኬቷ መሠረት እንደሆኑ ታምናለች።

የሥራ ቦታዋ ዱባይ መሆኑ ደግሞ የጨመረላት ነገር እንዳለ “የእዚህ አገር መንግሥት ባያበረታታኝ እና ባይደግፈኝ ኖሮ እዚህም ባልደረስኩ ነበር” ትመሰክራለች።

የአገሬው ሰው “ሠርተን ተለውጠን ሲያይ ‘እንኳን ፈጣሪ እረዳችሁ’ በማለት ያበረታናል እንጂ ተቃራኒውን አያስቡም” በማለት ለዱባይ መንግሥት እና ሕዝብ ያላትን አክብሮት ገልጻለች።

አብዛኛውን የሕይወት ዘመኗን ያሳለፈችባትን እና ሠርታ የተለወጠችባትን ዱባይን ትወዳታለች።

እንደ አገሯ ቆጥራ እየኖረችባት ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያን ደግሞ መርሳት አይቻላትም።

ለዚህም በየዓመቱ ስድስት የሚደርሱ የግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በመደገፍ በአገሯ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ትሳተፋለች።

የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ ቢሻሻል ሳራ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ከዚህም በበለጠ ሁኔታ ሰዎችን የማገዝ ፍላጎት አላት።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )