የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ እርሻ ጥለው የወጡ ማላውያንን እስራኤል አባረረች……

የተሻለ ደመወዝ ለማግኘት ሲሉ ይሠሩበት የነበረውን ማሳ ጥለው የወጡ የማላዊ ዜጎችን እስራኤል አባረረች።

12ቱ ማላውያንን እስራኤልን ለቀው እንዲወጡ የተደረገው ከሌሎች 40 ስደተኞች ጋር ቴል አቪቭ በሚገኝ ዳቦ መጋገሪያ ውስጥ ሲሠሩ ከተገኙ በኋላ ነው።

በእስራኤል እና ማላዊ መካከል ሠራተኞችን ለመቀበል የተደረገ ስምምነትን ተከትሎ ነበር ወደ እስራኤል የተጓዙት።

ይሠሩበት በነበረው እርሻ ውስጥ በነበረው የሥራ ሁኔታ ደስተኛ ስላልነበሩ በዳቦ መጋገሪያ ውስጥ ሌላ ሥራ ይዘዋል።

በማላዊ የእስራኤል አምባሳደር ማይክል ሎተም “በየትኛውም አገር እንደሚደረገው የቪዛ ስምምነቱን የጣሰ ሰው ይባረረራል” ብለዋል ለቢቢሲ።

“ሌሎችም ባሉበት ሥራ እንዲቀጥሉ ያስተምራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ማንም አስገድዷቸው አልመጡም። ሊሠሩ የመጡትን ሥራ ማከናወን አለባቸው” ሲሉ አክለዋል።

በእስራኤል የሚሠራው የማላዊ ዜጋ ቤንዛኒ በእርሻው ላይ የሚከፈለው ደመወዝ በአገሪቱ ካለው ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ያነሰ እንደሆነ ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ገልጿል።

“በእስራኤል አነስተኛው ክፍያ 32 ሻክልስ (8.60 ዶላር) ነው። አንዳንዶቻችን ግን በሰዓት ከ18 እስከ 20 ሻክልስ ብቻ ነው እየተከፈለን ያለው” ብሏል።

አብዛኞቹ ወደ እስራኤል የሄዱት በወር 1500 ዶላር እንዲከፈላቸው ስምምነት አድርገው መሆኑንም ገልጿል።

ቢቢሲ ያነጋገረው ሠራተኛ ከእስራኤል እንዲወጡ ከተደረጉት መካከል ባይሆንም ያለውን ሁኔታ ገልጿል።

አምባሳደሩ እንዳሉት፣ የእርሻ ሥራቸውን ጥለው በመውጣት የቪዛ ስምምነታቸውን ከማፍረስ ይልቅ ቅሬታ ቢያስገቡ ይሻል ነበር።

“የሚገባኝን አላገኘሁም የሚል ሰው የሚደውልበት ስልክ ቁጥር አለ። ሕጉን ማፍረስ ግን መፍትሔ አይሆንም። የእስራኤል ፖሊስ ለሕገ ወጥ ድርጊት ትዕግስት የለውም” ብለዋል።

በእስራኤል ሐማስ ጥቃት ካደረሰ በኋላ የተፈጠረውን የሠራተኞች ቁጥር ክፍተት ለመሙላት በተደረገ ስምምነት ነበር 10 ሺህ ሠራተኞች ወደ እስራኤል የእርሻ ሥራ የተወሰዱት።

ወደ እስራኤል ከተጓዙት ሠራተኞች መካከል በብዛት ከታይላንድ የሄዱት ጦርነቱ ሲነሳ ጥለው ወጥተዋል።

ከማላዊ የሄዱት 200 ሠራተኞች ሲሆኑ ኬንያ ደግሞ 1500 ሠራተኞች ልካለች።

ኬንያ ውስጥ ውሳኔው ውዝግብ አስነስቷል። አንዳንዶች ለደኅንነታቸው ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አገራቱ ግን የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ስምምነቱ እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

ሌሎች 3000 ሠራተኞችን ከማላዊ ለመውሰድ ስምምነት መደረጉን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )