ተከታዮቹ በረሀብ ተቀጥተው እንዲሞቱ አድርጓል የተባለው ኬንያዊ “ፓስተር” ጥፋተኛ አይደለሁም አለ……
ከ400 በላይ ተከታዮቹ በጠኔ እንዲሞቱ አበረታትቷል የተባለው ኬንያዊ የግለሰብ አምልኮ መሪ በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ለፍርድ ቤት ተናግሯል።
በሀገሪቱ ታሪክ በግለሰብ አምልኮ ምክንያት በርካታ ሰዎች ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ራሱን ፓስተር ብሎ የሚጠራው ፖል ማኬንዚ በባሕር ዳርቻዋ ከተማዋ ሞምባሳ በተሰየመ ችሎት ፊት ሰኞ ዕለት ቀርቧል።
ማኬንዚ ብቻ ሳይሆን ሌሎች 94 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው።
የሕፃናትን ጨምሮ የ429 ሰዎች ሬሳ ሻካሆላ ከተባለ የጅምላ መቃብር ሥፍራ መውጣቱን ተከትሎ ነው ፓስተሩ ባለፈው ሚያዚያ በቁጥጥር ሥር የዋለው።
ሻካሆላ የተባለው መንደር ከሌላኛዋ የባሕር ዳርቻ ከተማ ማሊንዲ በስተምዕራብ የሚገኝ ራቅ ያለ ቦታ ነው። አብዛኛዎቹ አስክሬኖች የረሀብ እና የድብደባ ምልክት ታይቶባቸዋል።
“እንዲህ ያለ የግድያ ወንጀል ኬንያ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም” ሲሉ አቃቤ ሕግ አሌክሳንደር ጃሚ ያሚና ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
አቃቤ ሕግ እንደሚለው በሚቀጥሉት አራት ቀናት ከ400 በላይ ምስክሮች ቃላቸውን ይሰጣሉ።
ጉዳዩ በኬንያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ያሉት ያሚና ተጠርጣሪዎቹ ቅጣት የሚደርስባቸው ራስን ከማጥፋት ጋር በሚያያዘው የሀገሪቱ ሕግ መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ ዜና ባለፈው ዓመት በመገናኛ ብዙኃን ሲነገር ኬንያዊያንን ያስደነገጠው ጉዳይ እንዴት ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ ተርበው ይሞታሉ የሚለው ነበር።
የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበው ጉዳይ “የሻካሆላ ጫካ የጅምላ ጭፍጨፋ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ማኬንዚ ተከታዮቹ ምግብ መመገብ ካቆሙ በፍጥነት ወደ ገነት ይገባሉ ሲሉ ተናግሯል ተብሎ ይጠረጠራል።
ግለሰቡ ሌሎች ሁለት ክሶች ያሉበት ሲሆን አንደኛው ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ፤ ሌላኛው ደግሞ ከሕፃናት ብዝበዛ ጋር የተገናኘ ነው።
ሕፃናትን ለስቃይ ዳርጓል፣ አካላዊ ጉዳት አድርሶባቸዋል፣ ጭካኔ አሳይቷል እንዲሁም ትምህርት ከማግኘት መብታቸው ገትቷቸዋል የሚሉ ክሶች ቢቀርቡበትም እሱ ግን ይክዳል።
ከሞት የተረፉ ሰዎች እንደሚሉት መጀመሪያ ራሳቸውን በረሀብ እንዲቀጡ የሚደረጉት ሕፃናት ናቸው፤ ይህም የሚሆነው ደግሞ ግለሰቡ ባወጣው ሕግ መሠረት ነው።
በመመሪያው መሠረት ከሕፃናት ቀጥሎ ያላገቡ፣ ከዚያ ሴቶች፣ ቀጥሎ ወንዶች ከሁሉም በኋላ ደግሞ የእምነት መሪዎች ራሳቸውን በረሀብ ይቀጣሉ።
ማኬንዚ፤ ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል የተባለውን ቸርች ያቋቋመው በአውሮፓውያኑ 2003 ቢሆንም በ2019 ዘግቼዋለሁ ይላል።
ተከታዮቹን ሻካሆላ ወደ ተባለው ጫካ ገብተው የዓለም ፍፃሜን እንዲጠባበቁ እና “እየሱስን ለማግኘት” እንዲዘጋጁ ሲያበረታታቸው ነበር።
ራሱን ፓስተር የሚለው ማኬንዚ ሻካሆላ ጫካ ውስጥ ከ300 በላይ ሄክታር መሬት እንዳለው የሚነገር ሲሆን ሥፍራው የሞባይል ኔትዎርክ የማይደርስበት ነው።
የማኬንዚ መሬት ተሸንሽኖ የተለያዩ ስሞች ተሰጥተውት ነበር። ከእነዚህ መካከል ይሁዳ፣ ቤተልሄም እና ናዝሬት ይገኙበታል።
ባለሥልጣናት ባለፈው መጋቢት የበርካታ ሬሳዎችን ዲኤንኤ መርምረው ለዘመድ አዝማድ አሳልፈው ሰጥተዋል። ከአስክሬኖቹ መካከል እስካሁን 34 ሰዎች ብቻ ናቸው ለቤተሰብ የተመለሱት።
ማኬንዚ ዓለማዊ ትምህርት ሰይጣናዊ እና ገንዘብ ለማጭበርበር የሚደረግ መንገድ ነው ብሎ ይሰብክ ነበር።
“ትምህርት በመፅሐፍ ቅዱስ ቦታ የለውም” የሚለው ማኬንዚ በ2017 እና 18 ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ በማበረታቱ በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።
አልፎም እናቶች በወሊድ ጊዜ የሕክምና እርዳታ እንዳይገኙ እና ልጆቻቸውን እንዳያስከትቡ እንደሚያበረታታ ይነገራል።
ግለሰቡ ባለፈው ኅዳር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የፊልም ስቱዲዮ በማንቀሳቀስ እና ከስብከቱ ጋር የተገናኙ ፊልሞችን በማሰራጨት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ አንድ ዓመት እንደተፈረደበት ይታወሳል።
ኬንያ ኃይማኖታዊ ሀገር ስትሆን ከ85 በመቶ በላይ የሀገሪቱ ነዋሪ የክርስትና እምነት ተከታይ ነው። አማኞች በግለሰብ አምልኮ አሊያ በሌሎች እምነታዊ ጉዳዮች ምክንያት ጉዳት ሲደርስባቸው ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)