ከመካ የሚመነጨው ቅዱሱ የዘምዘም ውሃ ምንድነው?

የዘምዘም ጉድጓዱ በሳዑዲ አረቢያዋ መካ በሚገኘው በታላቁ አል ሀራም መስጂድ ነው። ይህ የዓለማችን ትልቁ መስጂድ ሲሆን፣ የእስልምና ቅዱስ ስፍራ በሆነው ካዕባ ዙሪያ ይገኛል።

ከጉድጓድ የሚወጣው ውሃ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የዓለም ሙስሊሞች ዘንድ የተቀደሰ እና የመፈወስ ኃይል እንዳለው ይታመናል።

ለሃጅ ከሚጓዙ ሙስሊሞች አብዛኞቹ ከዚህ ጉድጓድ ውሃ ይዘው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ውሃው አደጋን፣ በሽታን እና ክፉን ነገሮችን ይከላከላል ተብሎ ስለሚታመን፤ ለቤተሰብ አባላት እና ለጓደኞች ያካፍላሉ። ውሃው የማያልቅ በመሆኑም ተአምር እንደሆነ ይታመናል።

በየዓመቱ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች መካ ይገባሉ ተብሎ ይታመናል።

ሁሉም ጎብኚዎች ስለማይመዘገቡ እና ብዙዎቹ የአካባቢው ተወላጆች ወይም ከጎረቤት አገራት በባሕር እና በየብስ የሚገቡ በመሆናቸው በሃጅ ላይ የሚሳተፉት ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በእጅጉ እንደሚበልጥም ይገመታል።

ዘምዘም ለሙስሊሞች ለምን አስፈላጊ ሆነ?

ይህ ውሃ በታሪክ እና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ምክንያት ለሙስሊሞች ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የእስልምና ሊቁ ኢማም ቡኻሪ አብደላህ ኢብኑ አባስ በ860 ሳሂህ አል ቡኻሪ በመባል የሚታወቁትን ስድስት የሐዲስ ጥራዞች አጠናቅረዋል።

ሐዲስ ከቁርአን ቀጥሎ የሃይማኖታዊ እና የሞራል መመሪያ ምንጭ ሆኖ ይቀመጣል። የነቢዩ ሙሐመድን ወጎች፣ ግላዊ የአምልኮ ሥርዓቶች እና አስተምህሮዎችን ያቀፈ ነው ተብሎ ይታመናል። የተዘጋጀውም በነብዩ የቅርብ ሰዎች ነው።

ሐዲስ የነብዩን ትምህርቶች እና መከተል የሚገቡ የሥነ ምግባር ሕግጋትን ይወክላል። የሐዲስ የተቀባይነት መጠን በሱኒ እና በሺዓ ሙስሊሞች መካከል እና በሁለቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የእምነት እሳቤዎች መካከልም ይለያያል።

ነብዩ ኢብራሂም ሚስቱን ሃጃርን እና ልጁን ምግብ እና ውሃ በሌለበት በረሃ ውስጥ ትቶ በሄደበት ወቅት ጸሎቷ እንዲመልስ ፈጣሪ የዘምዘም ጉድጓድን ከሺህ ዓመታት በፊት መፍጠሩን እስላማዊ ትውፊቶች ያስረዳሉ።

ይህ ክስተት በቁርአን ሱራ ኢብራሂም ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለያዩ የእስልምና ጽሑፎች ውስጥም በዝርዝር ተቀምጧል።

በሳሂህ አል ቡኻሪ ታሪኩ ሃጀር በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆና ውሃ ፍለጋ በሴፋ እና በማርዋ ኮረብታዎች መካከል መልአኩ ገብርኤል መሬቱን በተረከዙ መትቶ ውሃው እስኪፈልቅ ድረስ ሰባት ጊዜ እንዴት እንደተመላለሰች ይገልፃል።

ውሃው ሊያልቅ ይችላል በሚል ፍራቻም ሃጃር ‘ዘም ዘም’ (በአረብኛ ‘ውሃውን ማቆም’ እንደማለት ነው) የሚለውን ቃል ደጋግማ በመናገሯ ጉድጓዱ እና ውሃው ስያሜውን አግኝተዋል።

ከሐጅ ጋር እንዴት ይገናኛል?

የዘምዘም ውሃ እና የሐጅ ጉዞ ታሪካዊ እና ጥልቅ የሆነ ትስስር አላቸው። ሐጅ ለሙስሊሞች የእስልምና አምስተኛው እና የመጨረሻው ምሰሶ ነው። በእስላማዊ የጨረቃ አቆጣጠር በአስራ ሁለተኛው ዱል ሂጃህ ወር ውስጥ ይከናወናል።

ዘንድሮ በሰኔ ሁለተኛው ሳምንት ተጀምሮ በሐምሌ ወር ይጠናቀቃል። በአካልም ሆነ በአዕምሮም አቅም ያለው ሙስሊም ሁሉ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ከየትኛውም ካለበት ቦታ ተነስቶ ይህንን ጉዞ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ዑምራ አጭር እና ጥቂት የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚያካትት አጭር ጉብኝት ሲሆን፣ በማንኛውም ጊዜ ሊጠናቀቅም ይችላል።

ነብዩ ኢብራሂም ካዓባን እንደገና ከገነቡ በኋላ ሰዎች በአላህ ትዕዛዝ ሐጅ እንዲያደርጉ ጋብዘዋል ሲሉ በባንግላዲሽ የእስልምና-አረብ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ሙሐመድ አብዱራሺድ ገልጸዋል።

ከሐጅ ሥነ-ሥርዓቶች መካከል ጣዋፍ የሚባል ካዓባን መዞርን እና ሳዓይ የሚባለው እምዲሁም በሳፋ እና በማርዋ ኮረብታ መካከል ሰባት ጊዜ የእግር ጉዞዎችን ማደረግን ያጠቃልላል።

እነዚህ የአምልኮ ሥርዓቶች ከሃጃር እና ከዘምዘም ጉድጓድ ታሪክ ጋር የተቆራኙ ሲሆኑ፣ እርሷ ያሳለፈችውን ጉዞም የሚደግሙበት ነው።

የዘምዘምን ውሃ መጠጣት ሐጅ ለማድረግ ግዴታ ባይሆንም፣ የነብዩ ሙሐመድ ሱና (ባህል እና አስተምህሮ) ተደርጎ ይቆጠራል። አብዛኛዎቹ ሐጃጆች ውሃውን የሚጠጡት ካዓባውን ከዞሩ እና በሳፋ እና በመርዋ ተራሮች መካከል ሰባት ጊዜ ከመመላለሳቸው በፊት ነው።

የዘምዘም ውሃ ወደ ሌሎች አገራት እንዴት ይደርሳል?

የዘምዘም ውሃ በዋነኝነት የሚሰበሰበው መካን በሚጎበኙ ምዕመናን ነው።

ቱሪስቶች የዘምዘምን ውሃ ይዘው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ቢፈቀድም፣ ለንግድ አገልግሎት ወደ ውጭ መላክ ግን በሳዑዲ ባለሥልጣናት ተከልክሏል። ይህ ቢሆንም ግን የዘምዘም ውሃ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ እየተሸጠ መሆኑ ተመዝግቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ በግንቦት 2011 ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ በዩኬ ውስጥ ባሉ ውስጥ የዘምዘም ውሃ ተብሎ ታሽጎ በሚሸጠው ውሃ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው አርሴኒክ ንጥረ ነገር መገኘቱን ጠቁሟል።

ምርመራው በሕገ ወጥ ሽያጩ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል። የሳዑዲ ባለሥልጣናትም ውሃው ንፁህ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ጥብቅ የጥራት ቁጥጥር እንዲያደረግ አድርጓል።

የሳዑዲ አረቢያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የጉድጓዱን የውሃ ጥራት ከማስተዳድር ባለፈ የዘምዘም ጥናት እና ምርምር ማዕከልን ይመራል።

ውሃው በፓምፕ ከጉድጓድ ወደ ውሃ ማጣሪያ እንዲገባ ይደረጋል። ቀጥሎ ይጣራ እና በማጠራቀሚያዎች ውስጥ ይከማቻል።

በየቀኑ በመኪኖች በመቶ ሺህዎች ሊትር የሚቆጠር የዘምዘም ውሃ ወደ መዲና ንጉሥ አብዱላዚዝ ሰበይ ማጠራቀሚያ በማድረስ ለታላቁ መስጂድ እና ለነብዩ መስጂድ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ ይደረጋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )