በመቱ ከተማ የሙሉ ወንጌል አባላት በጎዳና ላይ ስብከት ወቅት በፖሊስ መደብደባቸውን ተናገሩ

በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦራ መቱ ከተማ ለሃይማኖታዊ ስብከት አደባባይ ወጥተው የነበሩ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አባላት በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ድብደባ ተፈጽሞባቸው ጉዳት እንደደረሰ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች እና በወቅቱ በስፍራው የነበሩ ግለሰቦች እንዳሉት ከሆነ የፀጥታ ኃይሎቹ በፈጸሙት ድብደባ የተጎዱት ሰዎች ከ20 በላይ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ተሻለ ኤጀርሶ በበኩላቸው የቤተክርስቲያኒቱ አባላት ያካካሄዱት የጎዳና ላይ ስብከት ከተገቢው የመንግሥት አካል ፈቃድ እንዳላገኘ ተናግረዋል።

የሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ፓስተር ብርሃኑ ዘለቀ በበኩላቸው ከመቱ እና አካባቢዋ የመጡ የቤተክርስቲያኒቷ አባላት እሁድ ግንቦት 25/2016 ዓ.ም ለጎዳና ላይ ስብከት በወጡበት በፖሊስ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

“ወደ ከተማዋ ጎዳና የወጣነው ወንጌል ለመስበክ ነው። ከአንድ ሺህ ሰው በላይ ይሆናል በወቅቱ የወጣው። መንገድ ሳንዘጋ በጎዳናው ላይ እየተንቀሳቀስን እየሰበክን ነበር። ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ነው። የፀጥታ ኃይሎች መጥተው አስቆሙን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የከተማው ከንቲባ በበኩላቸው “በዕለቱ በከተማችን የትኛውም የእምነት ተቋም በከተማዋ ጎዳና ላይ አምልኮ ለማካሄድ በሚል ፈቃድ አልጠየቀም፣ አልወሰደም። በከተማው ጎዳና ላይ ወጥተው የነበሩ ሰዎችን ፖሊስ አስቁሟቸዋል። ፖሊስ ያስቆማቸው ፈቃድ ስለሌላቸው እና የመሰባሰባቸው ምክንያት ባለመታወቁ ነው” ብለዋል።

የቤተክርስቲያኗ አባላት ደረሰብን ስላሉት ድብደባ የተጠየቁት አቶ ተሻለ “ስለደረሰ ድብደባ እና ጉዳት ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም” ብለዋል።

ፓስተር ብርሃኑ፣ የፀጥታ ኃይል አባላቱ ምዕመናኑን ካስቆሟቸው በኋላ እየዘመሩ የነበሩትን በመኪና ጭነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ መውሰዳቸውንም ይናገራሉ።

በኋላም የተቀሩትን እዚያው ጎዳና ላይ ትተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት በቁጥጥር ስር የዋሉትን ማስለቀቃቸውን ይናገራሉ።

የከተማው ከንቲባ በበኩላቸው “የጎዳና ላይ መሰባሰቡ ለሃይማኖታዊ ተግባር መሆኑን ስንረዳ ከፖሊስ ጋር ተነጋገርን በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት እንዲለቀቁ አድርገናል” ይላሉ።

ፓስተር ብርሃኑ ከሰዓት 10 ሰዓት ላይ የጎዳና ስብከት ማካሄድ መጀመራቸውን እና ማታ 1 ሰዓት አካባቢ ፖሊስ መጥቶ እየደበደበ እንደበተናቸው ገልጸዋል።

ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ ሰዎች በመቱ ፖሊስ እና ሚሊሻ አባላት በደረሰባቸው ድብደባ የተነሳ መጎዳታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ላይ ተሳታፊ የነበረው አማኑኤል ወርቁ የተባለው የቤተክርስቲያኗ አባል ፖሊስ ምዕመናኑን መደብደብ የጀመረው ሁሉ ነገር በሰላም እየተካሄደ በነበረበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።

“. . . ምንም ዓይነት ዱላም ሆነ ብረት አልያዝንም። ሰው በሰላም ተቀምጦ እየተሳተፈ ባለበት ወቅት መጥተው መደብደብ ጀመሩ። ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ይበልጥ የተጎዱት” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በፀጥታ ኃይሎች በደረሰባት ድብደባ ተጎድታ በካርል መቱ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል ማድረጓን የምትናገረው ኤደን ግርማ “በፖሊስ ቆመጥ ጭንቅላቴ ላይ ተመትቻለሁ። እጄ ላይም ድብደባ ደርሶብኛል። . . . ጭንቅላቴ ላይ የነበረው መፈንከት ተሰፍቷል” በማለት ከእሷ ጋር ከ30 በላይ ሰዎች ተጎድተው በሆስፒታል የሕክምና እርዳታ ማግኘታቸውን ገልጻለች።

ካኪ ቢኒያም በድብደባ ጉዳት ከደረሰባቸው እና በካርል መቱ ሆስፒታል የሕክምና ካገኙ መካከል ስትሆን፣ በኩላሊቷ እና በእጇ ላይ ጉዳት እንደደረሰባት አሁን ከሆስፒታል ወጥታ በግሏ ሕክምና እየተከታተለች መሆኑን ገልጻለች።

የመቱ ከተማ ከንቲባ የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ እምነት አባላት ግንቦት 3/2016 ዓ.ም. የጎዳና ላይ አምልኮ ለማካሄድ አስፈቅዳ እንደነበር የነበረ ቢሆንም ፕሮግራሙን ለእሁድ መቀየሩን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የከተማዋ ፖሊስ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ያለፈቃድ እና እውቅና መሰብሰባቸው “በከተማው መንገድ በመዝጋት ረብሻ ለመፍጠር” እንዳቀዱ አድርጎ ስላሰበ የደኅንነት ስጋት ይፈጥራል በሚል እንዳስቆማቸው ከንቲባው ጨምረው አስረድተዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ )