በምክክር ኮሚሽን ስብሰባ ላይ የነበሩ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ በፖሊስ ከተወሰዱ በኋላ ተለቀቁ
ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እያካሄደ በነበረው የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው ሲሳተፉ የነበሩ ተወካይ ከአዳራሽ በፖሊስ ተወስደው እንደነበር ለቢቢሲ ተናገሩ።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ አቶ ባንዲራ በላቸው የተባሉት የፓርቲው ተወካይ ተይዘው የነበረው “በስህተት” እንደሆነ ገልጾ ጉዳዩ እንዲፈታ ማድረጉን አታውቋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያካሂድ የነበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ የተጠናቀቀው ትናንት እሁድ ነው።
በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ የተካሄደው ይህ ውይይት ከ1,800 በላይ ተሳታፊዎች ለምክክር እንዲቀርቡ የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ያቀረቡበት ነው።
በዚህ ምክክር መድረክ ላይ ተወካዮቻቸውን ካሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ ካለፈው ሳምንት አርብ ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም ጀምሮ አምስት አባላቱ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ ሲሳተፉ እንደነበር የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንዲራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህ የፓርቲው ተወካዮች መካከል እንዱ የሆኑት አቶ ባንዲራ፤ የክልሉ ተሳታፊዎች ለምክክሩ የመረጧቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ባስረከቡበት የትናንቱ [እሁድ] መድረክ ላይም ተገኝተው እንደነበር ገልጸዋል። የውይይቱ ማጠናቀቂያ እየተካሄደ እያለ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ “ሲቪል የለበሱ ሰባት ገደማ” ግለሰቦች “በኃይል እና በጫና” ከአዳራሹ እንደወሰዷቸው አስረድተዋል።
“አዳራሽ ስልክ እያወራሁ ነበር። ስለ ስብሰባው፣ ስለ ውሎአችን ለራሴ አመራር ሪፖርት እያቀረብኩ እያለሁ መጀመሪያ መጥተው ከጆሮዬ ስልኬን ነጠቁ፣ ‘ና ውጣ’ አሉኝ” የሚሉት አቶ ባንዲራ፤ “አብዛኞቹ ሲቪል የለበሱ” ስለነበሩ በጊዜው ማንነታቸውን ለመለየት እንዳልቻሉ አስረድተዋል።
“በርካታ ቁጥር ያላቸው ስለሆኑ በኃይል እየገፈተሩ አስወጡኝ። ከሰዎች ጋር እንዳልገናኝ፣ መረጃ እንዳልሰጥ፣ ለቤተሰብ ሁሉ ደውዬ ‘በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነኝ’ የሚለውን ለማስረዳት እድል አልተሰጠኝም። ስልኬ ከእጄ ተቀማ በእንደዚህ አፈና ስለተወሰድኩ የተነገረኝ ነገር የለም” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ ከአዳራሽ እየወሰዷቸው በነበረበት ሰዓት “ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ” ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን የሚያስታውሱት የፓርቲው የጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ “ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን ትወሰዳለህ፤ ተረጋጋ” ተብሎ እንደተነገራቸው አስረድዋል።
በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገደቡም “ሲቪል የለበሱ” ግለሰቦች አቶ ባንዲራን ከአዳራሹ ይዘው መወሰዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አቶ ባንዲራ እንደሚገልጹት በአዳራሹ ከተያዙ በኋላ “ከወላይታ ሶዶ ከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ የአድማ ብተና ፖሊስ ካምፕ” ተወስደዋል። ወደ ካምፑ ከደረሱ በኋላ “በበርካታ የአድማ በታኝ አባላት” ታጅበው “ወደ ቁጫ ከተማ” ጉዞ ጀምረው እንደነበር ተናግረዋል።
ጉዞ ከጀመሩ በኋላ የፖሊስ አባላቱ፡“አበል አልተከፈለህም ይባላል፣ አጣርተን እንመልስህ” በማለት የምክክር ኮሚሽኑ ስብሰባ ሲካሄድበት ወደነበረው አዳራሽ እንደመለሷቸው ገልጸዋል። አቶ ባንዲራ፤ የተለቀቁት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ርብርብ” ነው ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።
የፓርቲው ጽህፈት ቤታ ኃላፊ መወሰዳቸውን ተከትሎ በአዳራሹ ውስጥ ይገኙ ለነበሩት ለሀገራዊ ምክክር አመራሮች አቤቱታ ማቅረባቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ተናግረዋል።
“[ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን] ኮሚሽነሮች ተጯጩኸን ስለነገርናቸው፤ ኮሚሽነሮቹ ከክልል ከፍተኛ አመራር ጋር ተነጋግረ ሁኔታው ካልታረመ አስቸጋሪ እንደሆነ ስለተናገሩ [አቶ ባንዲራን] መልሰዋል” ሲሉ ኮሚሽኑ ያደረገውን ጥረት ገልጸዋል።
አቶ ባንዲራ፤ “እኔን አጅበው የወሰዱ ፖሊሶች በሙሉ አዳራሹን ለቅቀው ከወጡ በኋላ፤ ኮሚሽነሮቹ በራሳቸው መኪና እና እጀባ ወደ ማረፊያ ቦታ ወሰዱኝ” ሲሉ ከተለቀቁ በኋላ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።
ቢቢሲ፤ ስለ ጉዳዩ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
ስለ ሁኔታው ጥያቄ የቀረበላቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቅሬታ አያያዝ አስተባባሪ አቶ ብዙነህ አሰፋ፤ የድርጊቱን መፈጸሙን አረጋግጠዋል። ይሁንና የፓርቲው ተወካይ መያዝ “ድንገታዊ” እና “በስህተት የተፈጸመ” እንደሆነ ገልጸዋል።
“[የፓርቲው ተወካይ] ተይዞ ነበረ፤ በኋላ ተጣርቶ ተለቅቋል። መያዙ ስህተት ነው” ያሉት አቶ ብዙነህ፤ ተወካዩ “አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይቅርታ ተጠይቆ” እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።
በፖሊስ ተይዘው በቆዩበት ጊዜ ለምን እንደተያዙ ማብራሪያ እንዳልተሰጣቸው የሚናገሩት አቶ ባንዲራ በበኩላቸው፤ ድርጊቱ የተፈጸመው “የቁጫ ሕዝብ ውክልና እንዳይኖረው፣ ፓርቲው በምክክሩ እንዳይሳተፍ ጫና ለማድረግ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ረዳት ፕሮፌሰር ገነነም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ፤ ራሳቸው ጭምር በኮሚሽኑ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ከተገኙ በኋላ “ዛቻ እና ማስፈራሪያ” ሲደርስባቸው የነበረ መሆኑን በማሳያነት ገልጸዋል። ይህንንም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጭምር “በደብዳቤ” ማሳወቀቸውን ተናግረዋል።
የኮሚሽን የቅሬታ አያያዝ አስተባባሪ አቶ ብዙነህ ግን የትናንቱ ድርጊት “ሆነ ተብሎ የቁጫን ማኅበረሰብ ወይም ተሳታፊ ለማጥቃት” የተፈጸመ እንዳልሆነ በመግለፅ ከተሳታፊዎቹ የተነሳውን ሀሳብ አስተባብለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ፤ ዛቻ እና ማስፈራሪያን በተመለከተ ከቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቅሬታ ደብዳቤ ደርሶት እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ብዙነህ፤ “በቃል ደረጃ የተነጋገርነው ነገር አለ። ትናንት የተከሰተውን ሁኔታ ጋር የተያያዘ የገባ ማመልከቻ የለም። የምንነጋገርባቸው ነገሮች ይኖራሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)