በአሜሪካ ያሉ አፍሪካውያን በምርጫው ምን ማሳካት ይፈልጋሉ?

አኔት ንጃዉ የቴክሳስ ነዋሪ ናት። ሴራሊዮን አሜሪካዊቷ ጠበቃ እና የንግድ ድርጅት ባለቤት ስትሆን “የእኛ ትልቁ ጉዳይ እንደ ስደተኞች በአሜሪካ የመኖር፣ የመስራት እና ድምጽ መስጠት መቻል ነው” ስትል ተናግራለች።

በቴክሳስ የሚኖሩ 300 ሺህ የአፍሪካ ዲያስፖራ አባላት በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማህበረሰባቸው ድምጽ እንዲሰጥ ጠንክረው እየሠሩ ነው።

“ምንም እንኳን በሁለቱ ዕጩዎች ስር እንዴት እንደሚቀጥል ባላውቅም ንግዴ እንዲቀጥል አረጋግጣለሁ” ስትል ንጃው አክላ ገልጻለች።

“ከዘር እና ከስደት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብዙ ክፍፍል እና ጥላቻ አለ። ይህ ደግሞ የእኛ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብላለች ናይጄሪያዊት አሜሪካዊቷ የአፍሪካ የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (አፍሪፓክ) መስራቿ ኔካ አቻፑ።

የቴክሳስ ግዛት ከዓመታት የቡሽ ቤተሰብ አባላት ዕጩ መሆን በኋላ የሪፐብሊካን መሰረት ሆናለች። ከአራት ዓመታት በፊት ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ የዲሞክራቱ ጆ ባይደን በ6.5 በመቶ አሸንፈዋል። ከ1996 ወዲህ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የተመዘገበ ጠባብ ውጤት ሆኗል።

አሁን የቴክሳስ ስነ-ሕዝብ እየተቀየረ ነው። በግዛቱ ውስጥ ያለው የአፍሪካ ዲያስፖራ ቁጥር ትልቅ የሚባለው ነው። በግዛቲቱ ናይጄሪያውያን፣ ጋናውያን፣ ኬንያውያን፣ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች በርካታ አፍሪካ አሜሪካዊያን ይኖራሉ። ምንም እንኳን ቁጥራቸው በፍጥነት በማደግ ላይ ቢሆንም በመንግሥት ችላ እንደተባሉ የሚሰማቸው በርካቶች ናቸው።በአፍሪካ አልባሳት ያሸበረቁ የቴክሳስ አፍሪካ አሜሪካዊያን

“እንደወጣት የሚያስጨንቀን ዋናው ነገር እንዴት እኖራለሁ? ወጪዎቼን እንዴት ከፍዬ ከጭንቀት እድናለሁ፤ ለወደፊቱስ ሳልጨነቅ እንዴት ገንዘብ እቆጥባለሁ የሚለው ነው” ስትል ከናይጄሪያ አሜሪካውያን ቤተሰቦች የተወለደችው እና የሚስ ናይጄሪያ አሜሪካ የቁንጅና ውድደር አሸንፊዋ ኡዴሜ አንቶኒ ገልጻለች።

በቴክሳስ የሚኖሩ አፍሪካዊያን ህይወት

‘ትንሿ ናይጄሪያ’ የሚል ቅጽል ስም የተሰጣት ሂውስተን በአሜሪካ ውስጥ ትልቅ ቁጥር ያለውን ናይጄሪያውያን ማህበረሰብ መኖሪያ ናት። ወደ 60 ሺህ ይገመታሉ።

በርካታ መንገዶቿ ከሌጎስ የሚመሳሰሉ ናቸው።

የናይጄሪያን እና የቴክሳስን ህይወት የሚያንጸባርቁ በናይጄሪያዊያን ባለቤትነት የሚተዳደሩ ንግዶችን እና የባህል ማዕከላትን አቅፋለች።

በቀለማት ያሸበረቁ የአፍሪካ ጨርቆችን የለበሱ ሰዎች በአፍሪካ የተለያዩ ቋንቋዎች ሲጨዋወቱ መስማት የተለመደ ነው። የአፍሮቢትስ ሙዚቃዎችን በሬስቶራንቶች ወይም በሱፐርማርኬቶች መስማትም በተመሳሳይ የተለመደ ነው።አይቪ ኦኮሮ

አፍሪካውያን ስደተኞች በስራ ፈጠራ፣ በአነስተኛ ንግዶች፣ በጤና አጠባበቅ እና በነዳጅ ዘርፎች ለቴክሳስ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋኦ አድርገዋል።

በአፍሪካውያን ስደተኞች ባለቤትነት የተያዙ አነስተኛ ንግዶች የአፍሪካን ባህል በምግብ፣ በአልባሳት እና በሌሎችም መንገዶች ከቴክስ ህይወት ጋር ያዋህዱታል።

ናይጄሪያዊ አሜሪካዊቷ ኢቪ ኦኮሮ ደግሞ “ሃይማኖትም የሕይወታችን በጣም አስፈላጊው አካል ነው” ብላለች።

ክርስቲያንም ሆንክ ሙስሊም ለመንፈሳዊ ህይወነታችንን ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን።”

በአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት፣ የማህበረሰብ ማዕከላት እና በአካባቢው ባሉ የንግድ ተቋማት ህብረተሰቡ ቢመርጥ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ትምህርት ተሰጥቷል።

በግዛቲቱ የሚኖሩ አፍሪካውያን ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም በማህበረሰቡ መካከል ያለው ተሳትፎ በታሪክ ዝቅተኛ የሚባል ነው።

የአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ጥናት እንደሚያሳየው 61 በመቶ የሚሆኑ እና በድምጽ መስጫ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ጥቁር ዜጎች ቴክሳስ ውስጥ ድምጽ ሰጥተዋል። ይህ አኃዝ አፍሪካዊ አሜሪካውያን እና አፍሪካውያን ስደተኞችን የሚያካትት ቢሆንም በግዛቲቱ የጥቁር መራጮች ተሳትፎን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳይ ነው።

ማአዚ ኦኮሮ የአይቪ አባት ሲሆን እአአ በ1977 ነበር አሜሪካ የገባው።

እሱና ሌሎች አፍሪካውያን ትኩረታቸውን አድርገው የነበረው ተምረው ወደ ትውልድ አገራቸው በመመለስ ለአገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደነበር ተናግሯል። በአሜሪካ የማህበረሰብ ተሳትፎ ላይ ብዙም ፍላጎት ስላልነበራቸው የግዴለሽነት ስሜት መፈጠሩን ይገልጻል።

“በአገሮቻችን በጣም እንኮራ ስለነበር በአሜሪካ ዲሞክራሲያዊ ሂደቶች ውስጥ መሳተፍ ይቅርና እዚህ የሚያቆየን ምንም ዓይነት ነገር እንዲኖር አንፈልግም ነበር” ብሏል።

ከበርካታ አሥርት ዓመታት በኋላ ግን እነዚህ የመጀመሪያው ትውልድ አፍሪካውያን በአሜሪካ ለረጅም ዓመታት ኖረው ጠንካራ ማህበረሰቦችን፣ ንግዶችን እና ቤተሰቦችን ገንብተዋል።

“እኛ ስላልተሳተፍን ታናናሾቻችን የፖለቲካውን ሂደት እንዲያዩ እና እንዲቀላቀሉ አርአያ አላስቀመጥንላቸውም። ይህ ግን መለወጥ አለበት! በዚህች አገር የፖለቲካ ሂደት ተሳትፎ ውስጥ ሚናችንን ማሳደግ አለብን” ይላል ኦኮሮ።

“አሁን ወደ ናይጄሪያ ፈጽሞ የማይመለሱ ናይጄሪያዊያን ልጆች አሉን። እነሱ ከተሳተፉ አፍሪካን የሚለውጥ ድምጽ መስጠት ይችላሉ።”ኔካ አቻፑ

የስደተኝነት ፖሊሲ የ2024 ምርጫ ዋና ጉዳይ ነው። ለብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች ደግሞ ጥልቅ ስሜት ቀስቃሽ ጉዳይ ነው።

ረዥም ቪዛ የሂደት፣ ለጥገኝነት ጠያቂዎች ውስን ዕድሎች መኖራቸው እና ግሪን ካርድ ተቀመጡት ጥብቅ መስፈርቶች ብዙዎች የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ስርዓትን ለመረዳት ከባድ ይሆንባቸዋል።

አንዳንዶች ሥርዓቱ ጥልቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያንጸባርቃል ወይ የሚል ጥያቄንም እንዲያነሱ አድርጓል።

“ፀረ-ጥቁርነት ቪዛ እስከማናገኝበት ደረጃ ድረስ ኢሚግሬሽን ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ይሆን?” ሲል የአፍሪክፓክ መስራቹ ኔካ አቻፑ ገልጻለች።

“የአፍሪካ ዲያስፖራዎች ከሁለቱም ዕጩዎች የሚፈልገው የበለጠ ሰብዓዊነት ያላቸውን ፖሊሲዎች ነው። ይህም ለአፍሪካውያን ዲያስፖራዎች ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካውያን ቤተሰቦች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆን አለበት” ብላለች።

ብዙ አፍሪካዊ ቤተሰቦች አሜሪካ ውስጥ እንዲሰፍሩ እና ሥራ እንዲያገኙ የሚያስችል የቤተሰብ መገናኛ እና የሥራ ፈቃድ ላይ አቻፑ የተሻለ ፖሊሲዎችን ማየት ትፈልጋለች።

ከፖሊሲዎች ጎን ለጎን በምርጫ ዘመቻው ውስጥ ስደተኞችን እንደወንጀለኛ ማየቱ በአሜሪካ ላሉ አፍሪካውያን የበለጠ አሳሳቢ ሆኗል።

ፖለቲከኞች የሚጠቀሙባቸው የዘረኝነት ንግግሮች ስደተኞችን በተለይም ከአፍሪካ እና ከሌሎች ታዳጊ አገራት የመጡትን በመጥፎ እንዲታዩ አድርጓል።

ቴክሳስ በሚገኘው የሳውዝ ዩኒቨርሲቲ የኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር እና ዲን የሆኑት ዶ/ር ክርስቲያን ኡላሲ በበኩላቸው “እንደ አሜሪካ ላለ ትልቅ አገር የሚወዳደር ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ መሳደብ፣ ማጥላላት፣ ማንቋሸሽ እና አንዳንድ ሰዎችን በመጥፎ መግለጽ፣ በሐሰት መፈረጅ ትክክል አይደለም” ብለዋል።

“ትውልድን ነጥሎ ወይም ዘርን ለይቶ ወንጀለኛ ብሎ መፈረጅ እና በበሽታ እንደተወረረ መግለጽ ለአገር አይጠቅምም። ለዚህ ቅጣት ሊኖርበት ይገባል። መራጫቾች በካርዳቸው ዕጩውን ሊቀጡ ይገባል” ብለዋል።

ሴራሊዮን አሜሪካዊቷ ጠበቃ እና የንግድ ድርጅት ባለቤት አኔት ንጃው በበኩሏ “እኔ ስደተኛ ነኝ። በልጅነቴ ነው ከቤተሰቤ ጋር እዚህ የመጣሁት። ትምህርት ቤት ገባሁ፣ ህግ ተማርኩኝ። ግብሬን እከፍላለሁ። ስለዚህ አንድ ሰው ስደትን እንደፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም ማጥቃት የሰብአዊነት አለመኖርን ያሳያል” ትላለች።

“ይህ ምርጫ ስለህብረተሰቡ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል። ማህበረሰቡ ደግሞ እኛን የሚከፋፍሉን እና እኛን የሚያበላሹን ሰዎች አይፈልግም።”የአፍሪካዊያን ስደተኞች ቁጥር በቴክሳስ እየጨመረ ነው

አሜሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለአፍሪካውያን ስደተኞች ሌላኛው አሳሳቢው ጉዳይ ነው።

እአአ 2021 አሜሪካ ውስጥ ወደ 2.4 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን ስደተኞች ነበሩ። ብዙዎች አሁንም ከትውልድ አገራቸው ጋር ቤተሰባዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዳላቸው ማይግሬሽን ፖሊሲ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ይህ ደግሞ የአሜሪካ-አፍሪካን መልካም ግንኙነት ማስቀጠል ጥልቅ ግላዊ ምክንያትም ይኖረዋል። አንዳንዶች ወደ አገራቸው በመደበኛነት ለመጓዝ የሚያስችላቸው ሁለት ዜግነት አላቸው።

“እንደ አሜሪካ አፍሪካዊ እዚህ የግል ሥራ ለመሥራት የሚያስችል፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚመራ፣ አፍሪካ ያላትን አቅም የሚያደንቅ እና ጠንካራ ትብብርን የሚያጎለብት መንግስት ተፈጥሮ ማየት እፈልጋለሁ” ይላል ማዚ ኦኮሮ።

እአአ በ 2022 ከሰሃራ በታች ላሉ አፍሪካ የተላከው ገንዘብ ወደ 53 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነበር። እንደዓለም ባንክ ከሆነ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ በአሜሪካ ከሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች የተገኘ ነው።

እንደ ኡደሜ አንቶኒ ላሉ ወጣቶች የአሜሪካ ኢኮኖሚ ስኬት ምርጫው ይወስነዋል።

“መኖር ወይም መቆጠብ ወይም ለቤተሰቦቻችን የምንሰጠው ትንሽ ተጨማሪ ነገር ከሌለን እና ግድ በሌላቸው ግለሰቦች የምንመራ ከሆነ ሀገር ቤት ላሉ ወገኖቻችን ገንዘብ መላክ ይከብደናል” ትላለች።

አፍሪካውያን መራጮች ገንቢ፣ ለመከባበር ቅድሚያ የሚሰጡ እጩዎችን ይፈልጋሉ። ይህም አፍሪካውያንን እንዲሁም አሜሪካን ሊጠቅም የሚችል አጋርነት እንዲሆን ነው ፍላጎታቸው።

“ይህንን ክፍተት ለማስተካከል እኛን በመጠቀም የአሜሪካ-አፍሪካን ግንኙነት ለማሳደግ አሜሪካውያን እንደ ሀብት ሊጠቀምባቸው የሚችላቸው ሰዎች ናቸው። እንደዕዳ መቆጠር የለብንም” ብላለች ኔካ አቻፑ።

ቴክሳስ ውስጥ የፖለቲካ ስልጣን ከዜጎች ተሳትፎ እንደሚመጣ ግንዛቤው እያደገ ነው። እንደአቻፑው አፍሪክፓክ ያሉ ድርጅቶች ማህበረሰባቸውን የበለጠ በዴሞክራሲያዊ ሂደት እንዲሳተፉ ለማስተማር እና ለማብቃት ጥረት እያደረጉ ነው።

“ውክልና ብቻ ሁልጊዜ ለውጥን አያረጋግጥም። ጥቂት አሸናፊዎች መኖራቸው ግን ጠቃሚ ነው። በፖለቲካዊ ስርዓቱ ውስጥ መገኘት አለብን” ብላለች አቻፑ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)