በፈረንሳይ የነብዩ ሞሐመድን ስዕል በማሳየቱ የተገደለው አስተማሪ ፍርድ ሒደት ተጀምሯል
ከአራት ዓመታት በፊት ከሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ውጭ ታርዶ የተገደለው ሳሙዔል ፓቲ ፍርድ ሒደት ፓሪስ ውስጥ መታየት ጀምሯል።
ከቼቼን ግዛት የመጣው አብዱላኽ አንዞሮቭ በወቅቱ ቢላ በእጁ ጨብጦ ይዞ ሳለ በፖሊስ መገደሉ አይዘነጋም።
የፍርድ ሒደቱ አስተማሪውን ማን ገደለው ሳይሆን እንዴት ሊገደል ቻለ የሚለውን የሚመለከት ይሆናል።
ለሚቀጥሉት ሰባት ሳምንታት የሚዘልቀው የፍርድ ሒደት እንዴት የአንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ ሕይወት በማኅበራዊ ሚድያ ምክንያት እንደተመሰቃቀለም ይመለከታል።
ፍርድ ቤት የቀረቡት አስተማሪው “የአምላክን ስም ያጎደፈ” ነው በሚል ማንነቱን የለዩ ሁለት ግለሰቦች፤ ለአብዱላኽ እርዳታ ያደረጉ ሁለት ሌሎች ግለሰቦች እና ትብብር አድርገዋል የተባሉ ተጨማሪ አራት ሰዎች ናቸው።
የሳሙዔል ፓቲ ግድያ ፈረንሳይዊያን ድንጋጤ ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ ትልቅ ዜና እንደነበር አይዘነጋም።
ሳሙዔል ፓቲ በሚያስተምርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተወዳጅነት የነበረው የታሪክ አስተማሪ እንደሆነ ይነገርለታል። ትምህርት ቤቱ ከፓሪስ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነው።
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2020 ስለመናገር ነፃነት እያስተማረ ነበር። ለታዳጊ ተማሪዎቹ ይህን ርዕስ በተደጋጋሚ አስተምሯል።
በአውሮፓውያኑ 2015 ቻርሊ ሄብዶ መፅሔት የነብዩ ሞሐመድን ስዕል አትሞ እንዴት አብዛኛው የመፅሔቱ አዘጋጆች ሊገደሉ እንደቻሉ በምሳሌ በመጥቀስ ነበር ሲያስተምር የነበረው። ለማስተማሪያ እንዲሆነው የካርቱን ስዕሎቹን ምስል ለተማሪዎች ሲያሳይ ነበር።
አስተማሪው ይህን ከማድረጉ በፊት ምናልባት ይህን ምስል ማየት የማይሹ ተማሪዎች ካሉ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ጠየቀ።
በሚቀጥለው ቀን የ13 ዓመቷ ታዳጊ ለምን ትምህርት ቤት እንደማትሄድ በአባቷ ተጠየቀች። አስተማሪው የነብዩ ሞሐመድን እርቃን ስዕል ሊያሳይ ስለሆነ ሙስሊም ተማሪዎች ውጡ ብሎ ሲጠይቀን በመቃወሟ መቀጣቷን ለአባቷ ተናገረች።
ነገር ግን አስተማሪው ሙስሊም ተማሪዎች ከክፍል ውጡ አላለም፤ ተማሪዋ ብትቀጣም ባለችው ምክንያት አልነበረም፤ አልፎም አስተማሪው ስለመናገር ነፃነት ትምህርት ሲሰጥ ክፍል ውስጥ አልነበረችም።
ቢሆንም በማኅበራዊ ሚድያ አማካይነት ወሬው በፍጥነት ተዛመተ።
የታዳጊዋ አባት ብራሒም ችኒና ታዳጊዋ ያለችውን ነገር በቪድዮ ቀርፆ የአስተማሪውን ስም እየጠራ በፌስቡክ ለቀቀው።
ቀጥሎ በአካባቢው ይኖር የነበረው ኢስላሚስቱ አብዱልሐኪም ሴፈሩዊ “እስልምና እና ነብዩ ሞሐመድ በሕዝብ ኮሌጅ እየተሰደቡ ነው” የሚል የ10 ደቂቃ ቪድዮ አሰራጨ።
በጥቂት ቀናት ውስጥ ትምህርት ቤቱ ከመላው ዓለም የማስፈራሪያ መልዕክት ይደርሰው ጀመር። አስተማሪው በተከፈተበት ዘመቻ ምክንያት ሕይወቱ በጣም እንደከበደ ለሥራ አጋሮቹ ተናገረ።
ከፓሪስ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሩዌን የሚኖረው የ18 ዓመቱ ስደተኛ አብዱላኽ አንዞሮቭ ዜናውን ሰማ። ቀጥሎ አሁን ፍርድ ቤት የቀረቡትን ተከሳሾች እርዳታ ጠየቀ።
አንደኛው ግለሰብ ቢላ ሲገዛ አብሮት ነበር። ሁለተኛው ግለሰብ ደግሞ ተመሳስሎ የተሠራ ሽጉጥ ሲገዛ ተባብሮት ቀጥሎ ወደ ትምህርት ቤቱ እየነዳ ወስዶታል።
አንዲት ሴትን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ከገዳዩ ጋር ስናፕቻት እና ትዊተር በተባሉ ማኅበራዊ ሚድያዎች የተነጋገሩ ናቸው።
ተከሳሾቹ ከጉዳዩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ቢያምኑም “የሽብር ግድያ ለመፈፀም ተባብረዋል” የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉትም። ጠበቃቸው ተከሳሾቹ በግልፅ የአስተማሪውን ድርጊት ቢቃወሙም ይገደል የሚለው ሐሳብ ግን አላነሱም ይላሉ።
ታዳጊዋ ከዓመት በፊት ታዳጊዎች ፍርድ ቤት ቀርባ ሐሰተኛ ክስ በማቅረብ ተከሳ ብይን ተሰጥቶባታል። ታዳጊዋ ፍርድ ቤቱ የጣለባትን ፍርድ ተላልፋ የምትገኝ ከሆነ ወደ እስር ቤት ትላካለች።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)