ኢራን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልብሷን በማውለቋ የታሰረችው ሴት እንድትፈታ ተጠየቀ

የኢራን ባለስልጣናት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልብሷን በማውለቋ ለእስር የተዳረገችው ሴት እንዲፈቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጠይቀዋል። ተማሪዋ ልብሷን ያወለቀችው ሂጃብ መልበስ የሚያስገድደውን ሕግ በመቃወም ነው ብለዋል።

ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በተዘዋወረ ቪዲዮ ልብሷን በማውለቅ በውስጥ ሱሪዋ እና ጡት መያዣ ደረጃ ላይ ተቀም ትታያለች።

በኋላም በቴህራን ኢስላሚክ አዛድ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ምርምር ማዕከል ግቢ ውስጥ በእርጋታ ስትራመድ ታይታለች።

በሁለተኛው ቪዲዮ ደግሞ ግለሰቧ የውስጥ ሱሪዋን ስታወልቅ ይታያል። ብዙም ሳይቆይ ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች አስገድደው ወደ መኪና ሲያገቧት ታይተዋል።

አዛድ ዩኒቨርሲቲ ግለሰቧ “የአዕምሮ መታወክ” አጋጥሟት እና ወደ “ሳይካትሪ ሆስፒታል” ተወስዳለች ብሏል።

በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ኢራናውያን መግለጫውን ከመጠራጠር ባለፈ “የሴት፣ ህይወት፣ ነፃነት” እንቅስቃሴ አካል አድርገው አቅርበውታል። በእንቅስቃሴው በርካታ ሴቶች ጸጉራቸውን እንዲሸፍኑ እና ረጅም ልብስ እንዲለብሱ የሚደነግገውን ህግ በአደባባይ ሲጥሱ ታይተዋል።

ኩርዳዊቷ ማሕሳ አሚኒ “በተገቢው መንገድ” ሂጃብ አልለበሰችም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አገር አቀፍ ተቃውሞ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ራሱን “የኢራን የተማሪዎች ንቅናቄ ሚዲያ” ብሎ የሚገልጸው እና ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው የአሚካቢር ጋዜጣ ቴሌግራም ቻናል ግለሰቧ የጸጉር መሸፈኛ ባለመልበሷ ከደህንነቶች ጋር ወደ ግጭት እንዳመራች ዘግቧል። በፍጥጫ ወቅት ልብሷን ማውለቋንም አስታውቋል።

በቁጥጥር ስር ውላ ወደ መኪና ስትገባ ጭንቅላቷ ከመኪናው ጋር በመጋጨቱ ደም እንደፈሰሳት እና እና ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዷን አክሏል።

ግለሰቧ ወደ አዛድ ዩኒቨርሲቲ መማሪያ ክፍሎች ገብታ ተማሪዎችን መቅረፅ እንደጀመረች አንድ እማኝ ለቢቢሲ ፋርስ ተናግሯል። መምህሩ ድርጊቷን ሲቃወም እየጮኸች ሄዳለች ብሏል።

እንደ ዓይን ምስክሮች ከሆነ ግለሰቧ ተማሪዎቹን “ላድናችሁ ነው የመጣሁት” ብላቸዋለች።

“አስገዳጅ ሂጃብ መልበስ ላይ ተቃውሞዬን ስገልጽ የጸጥታ ኃይሎች ከያዙኝ በኋላ ቤተሰቦቼ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለብኝ እንዲናገሩ ጫና ተደርጎባቸዋል” ስትል መቀመጫዋን ካናዳ ያደረገችው የሴቶች መብት ተሟጋቿ እና በ2018 ተቃውሞ ወቅት የጸጉር መሸፈኛ ሂጃቧን በማውለቋ የሦስት ዓመት እስራት የተፈረደባት አዛም ጃንግራቪ ትናግራለች።

“ቤተሰቦቼ አላደረጉትም። ብዙ ቤተሰቦች ግን የሚወዷቸውን ሰዎች ለመጠበቅ የተሻለው መንገድ እንደሆነ በማሰብ ጫና ውስጥ ገብተዋል። እስላማዊው ሪፐብሊክ የሴቶችን የአእምሮ ጤንነት ጥያቄ ውስጥ በመክተት ለማጥላላት የሚሞክረው በዚህ መንገድ ነው” ስትል አክላለች።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ኢራን “በኃይል የታሰረችው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በአስቸኳይ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ አለባት” ብሏል።

“እስክትፈታ ድረስም ባለስልጣናት ከማሰቃየት እና ሌሎች እንግልት ሊከላከሏት ይገባል። ቤተሰቦቿ እና ጠበቃ ማግኘት ይገባታል። በእስር ወቅት በእሷ ላይ የተፈጸሙ የድብደባ እና የወሲባዊ ጥቃት ውንጀላዎች ገለልተኛ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል። ጥቃት አድራሾችም ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ሲልም አክሏል።

በኢራን የተባበሩት መንግስታት ልዩ ልዑክ የሆኑት ማይ ሳቶ ቪዲዮውን በኤክስ ላይ ለጥፈው “የባለሥልጣናት ምላሽን ጨምሮ ይህንን ክስተት በቅርበት እከታተላለሁ” ሲሉ ጽፈዋል።

ኢራን ውስጥ በእስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊቷ የኖቤል የሠላም ተሸላሚ ናርጅስ መሐማዲ ጉዳዩ በጣም እንዳሳሰባት ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።

“ሴቶች ተቃውሞ ለማሰማት ዋጋ እንከፍላለን። እኛን በጉልበት ማንበርከክ ግን የማይታሰብ ነው።”

“በዩኒቨርሲቲው ተቃውሞዋን ያሰማችው ተማሪ ሰውነቷን የጭቆና እና የተቃውሞ ምልክት አድርጋዋለች። እንድትፈታ እና በሴቶች ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ እንዲያቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ” ስትል አክላለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

 ምንጭ፡– (ቢቢሲ)