ሰባት ጨቅላ ሕጻናትን በመግደል 15 የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባት ነርስ

የቀድሞዋ ነርስ ሉሲ ሌትቢ በዩናይትድ ኪንግደም በስፋት የምትታወቅ ገዳይ ናት።

ሕጻናትን አከታትሎ በመግደል ክስ ቀርቦባታል።

የቀድሞዋ ነርስ በእንግሊዘኛው አገላለጽ ሲሪያል ኪለር ናት። ሰባት ጨቅላ ሕጻናትን አከታትላ ገድላለች።

በአውሮፓውያኑ ከ2015 እስከ 2016 ሰባት ተጨማሪ ጨቅላ ሕጻናትን ለመግደል ሞክራለች።

የፍርድ ሂደቷ በአገሪቱ ታሪክ ረዥም ከሚባሉት አንዱ ነው። 15 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባታል።

በእስር ቤት ሳሉ ከሚሞቱ አራት የዩናይትድ ኪንግደም ሴቶች አንዷ ናት።

ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ግን የቀረቡትን ማስረጃዎች በተመለከተ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።

የቢቢሲ የምርመራ ክፍል የስታትስቲክስ፣ የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና እና የሳይንስ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

የተገደሉት ሕጻናት ወላጆች የፍርድ ሂደቱ ላይ በሚነሳ ጥያቄ ቅር መሰኘታቸው አልቀረም።

ሉሲ ጨቅላ ሕጻናትን በመግደልና የግድያ ሙከራ በማድረግ ነው የተከሰሰችው። የተጠቀመቻቸው መንገዶች ሕጻናቱ የደም ሥር ውስጥ በመርፌ አየር ማስገባት፣ በኢንሱሊን መመረዝ፣ ከፍተኛ የአእምሮ ጠባሳ ማሳደር እና ሆዳቸው ውስጥ አየር ወይም ፈሳሽ ማስገባት ናቸው።

በድርጊቱ ሳትጠረጠር በፊት ታታሪ እና ለሙያዋ ታማኝ ሠራተኛ እንደሆነች ይታሰብ ነበር።

ወንጀሉን ስትፈጽም አልታየችም። የቀረበባት ማስረጃ ቀጥተኛ ያልሆነ (በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ) ሲሆን፣ የፎረንሲክ ማስረጃም አልተገኘም።

የፍርድ ሂደቱ አካል ያልሆኑ ባለሙያዎች ከማስረጃ ጋር የተያያዘ ጥያቄ እያቀረቡ ያሉትም ለዚህ ነው።

ጠበቃዎች ባለሙያዎች ምስክርነት እንዲሰጡ ለምን እንዳልጠየቁ ግልጽ አይደለም።

አንድ የስታትስቲክስ ባለሙያ እንደሚሉት፣ ዐቃቤ ሕግ የክሱ ማጠንጠኛ ያደረገው መጥፎ ነገሮች በተከሰቱበት ጊዜ ሁሉ ሉሲ “በቦታው ነበረች” የሚለውን ነው።

ሉሲ ትሠራ የነበረው ካውንተስ ኦፍ ቸስተር በሚባል ሆስፒታል ነው። እአአ 2015 ድረስ በጨቅላ ሕጻናት ክፍሉ በዓመት ውስጥ ከአንድ እስከ ሦስት ሕጻናት ይሞቱ ነበር። ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ግን 13 ሕጻናት ሞተዋል።

በ2016 የሆስፒታሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ሉሲን መጠርጠር ጀመሩ።

ሕጻናቱ ሲሞቱ ሥራ ላይ የነበረችው ነርስ እሷ በመሆኗ ፖሊስ እንዲጠራ ተደረገ።

ፖሊስ በፍርድ ቤት ያቀረበው መረጃ፣ በሆስፒታሉ የተከሰቱ ሞቶችን እና ራሳቸውን የሳቱ ሕጻናትን ዝርዝር እንዲሁም በሆስፒታሉ ሥራ ላይ የነበሩ ነርሶችን ያሳያል።

እነዚህ ሲከሰቱ በሥራ ላይ የነበረችው ብቸኛ ነርስ ሉሲ ናት።

የስታትስቲክስ ባለሙያው ፕሮፌሰር ጄን ሀተን እንዳለችው፣ ይህ መረጃ የተሳሳተ ስሌት የተከተለ ነው።

ነርሶች ብዙ ሞት ያለበት ቦታ የሚገኙበት ሌላ ብዙ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ከግምት አልገባም ትላለች።

ነርሷ የታመሙ ሕጻናትን እየተንከባከበች ወይም ተጨማሪ የሥራ ሰዓት ወስዳ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ።

መረጃው በዓመቱ የተከሰቱ የተወሰኑ ሞቶች እና ራስ መሳቶችን ብቻ ያሳያል ትላለች ባለሙያዋ።

“ፖሊስ ጣልቃ የሚገባው ግድያ ተፈጽሟል ተብሎ ሲታመን ነው። ስለዚህ ሲመጡ ወንጀል ተፈጽሟል ብለው በማመን ነው። የሌሉ ነገሮችን እንዳሉ ሊያስቡ ይችላሉ።”የሉሲ የግል የውሎ ማስወሻ በፍርድ ሂደቱ ቀርቧል።

የኢንሱሊን ማስረጃ

ሉሲ ሁለት ጨቅላ ሕጻናት በሚመገቡበት ትቦ ኢንሱሊን ሰጥቶ ለመግደል በመሞከር ጥፋተኛ ተብላለች። የሕጻናቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ስማቸው ሳይጠቀስ ሕጻን ሀ እና ሕጻን ለ ተብለው ነው የተጠቀሱት።

ዐቃቤ ሕግ ሕጻናቱን ለመግደል ጥቂት ኢንሱሊን ብቻ ይበቃል ቢልም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያ አይስማሙም።

ፕሮፌሰር ጂኦፍ ቼስ በኒው ዚላንድ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካንትቤሪ ይሠራል።

ከ15 ዓመታት በላይ ኢንሱሊን እንዴት በጨቅላ ሕጻናት ላይ እንደሚሠራ አጥንቷል።

የንጥረ ነገር መሃንዲሷ ሔለን ሻነን አብራው ሠርታለች።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ሕጻን ሀ እና ሕጻን ለን ለመመረዝ ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንሱሊን ነው የሚያስፈልገው።

ከሆስፒታሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንሱሊን ስለመጥፋቱ ማስረጃ በፍርድ ቤት አልቀረበም።

ዶ/ር አደል ኢስማኤል በሰውነት ውስጥ ያለ ማክሮሞሎኪውል መለካትን (immunoassay test) በተመለከተ ከ30 በላይ ጥናቶች አሳትሟል።

“በጥናቴ እንዳገኘሁት ይህ ምርመራ ሲደረግ ስህተት ይገጥማል። 200 እጅ ስህተት ገጥሞኛል። ሁለተኛ ምርመራ የግድ ነው። ሕጻን ሀ እና ሕጻን ለን በተመለከተ ተጨማሪ የቤተ ሙከራ ምርመራ አልተደረገም። ሕጻናቱ ስላገገሙ ሆስፒታሉ ምርመራ አላዘዘም” ሲል ክፍተቱን ያስረዳል።ሉሲ ትሠራበት የነበረው ሆስፒታል

የጨረር ምርመራ

ሌላኛው ሕጻን ሐ ነው።

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2015 ላይ በ30 ሳምንት እርግዝና ተወለደ። 800 ግራም ይመዝን ነበር።

በጽኑ ህሙማን ማቆያ ሲታከም ነበር።

ሰኔ 13 ድንገት ህመሙ ተባባሰ። ሉሲ ከፍተኛ መጠን ያለው አየር ሆዱ ውስጥ በማስገባት ተከሳለች።

ሰኔ 12 ሕጻን ሐ የተነሳው ኤክስሬይ (የራጅ ምርመራ) ፍርድ ቤት ሲቀርብ፣ የሕጻኑ ሆድ የተነፋው በመመገቢያ ትቦው “አየር ስለተጨመረበት” ነው ተብሏል።

ዶ/ር ማይክል ሀል ኒውሮሎጂስት ነው። ጠበቆችን ያማከረው ባለሙያ እንደሚለው ሕጻን ሐ በሰው ስለመጎዳቱ ኤክስሬዩ አያሳይም።

ጠበቆቹ ለምስክርነት ፍርድ ቤት አልጠሩትም።

“ሆዱ ውስጥ ከፍተኛ አየር ለምን እንደተገኘ የሚያስረዱ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ሕጻኑ ለመተንፈስ ከተገጠመለት መሣሪያ ጋር የተያያዘ ይሆናል” ይላል።

ሉሲ ሕጻኑ ከመወለዱ በፊት እና በኋላ እንዲሁም ኤክስሬይ በተነሳበት ቀን ሥራ ላይ አልነበረችም።

ሕጻን ሐ ድንገት ጤናው ከመቃወሱ በፊት ደኅና እንደነበር ለፍርድ ቤት ቢገለጽም ቢቢሲ የተመለከተው ሰነድ እንደሚጠቁመው፣ ሕጻን ሐ ከጊዜው ቀድሞ በመወለዱ ምክንያት አደጋ ውስጥ ስላለ በቀን ሁለቴ በሐኪም መታየት ነበረበት።

ጡረታ የወጡት የጨቅላ ሕጻናት ባለሙያ ፕሮፌሰር ኮሊን ሞርሊ እንደሚሉት፣ ሕጻን ሐ የአንጀት መዘጋት አጋጥሞት እንደነበር አልተስተዋለም።

“ችግር የፈጠረው ያ ነበር። አፋጣኝ ቀዶ ሕክምና ቢደረግለት ሕይወቱ ይድን ነበር ብዬ አምናለሁ” ይላሉ ባለሙያው።

ሕጻን ሐ የሞተው በተፈጥሯዊ ሁኔታ እንደሆነ ይናገራሉ።

“በመመገቢያ ትቦው አየር እንዲገባ ተደርጓል የሚል ግራ የሚያጋባ መላ ምት ለምን መስጠት እንዳስፈለገ አልገባኝም።”

ሉሲ ላይ ፍርድ ቤት የቀረበው መረጃ ኤክስሬይን ብቻ የተመለከተ አይደለም። ሕጻን ሐ እሷ የምትከታተለው ሕጻን ባይሆንም እሱ ያለበት ክፍል ውስጥ ለመግባት መጠየቋን የሚያሳዩ አጭር የጽሑፍ መልዕክቶች ተገኝተዋል።

ሕጻኑ ራሱን ሲስት ሉሲን የሕጻኑ አልጋ አጠገብ እንዳየቻት አንዲት ነርስ ተናግራለች።

ሕጻኑ ከሞተ በኋላ ሉሲ የተለየ ባህሪ እንዳሳየች እና ፌስቡክ ላይ ወላጆቹን እንደፈለገች ተገልጿል።ሉሲ የፍርድ ውሳኔው ሲተላለፍ በፍርድ ቤት ተገኝታለች

የጉበት ጉዳት

ሌላው ሕጻን መ ነው።

ከሦስት ወንድሞቹ ጋር ሰኔ 2016 (እአአ) ነው የተወለደው። ጤናማ ነበር።

ሰኔ 23 ግን “ጤናው እጅግ ተቃወሰ” በሚል ፍርድ ቤት ጉዳዩ ቀርቧል።

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ባለሙያ ምስክር እንዳለው፣ ሕጻን መ ከመኪና አደጋ ጋር ተመሳሳይ የሆነ “የጉበት ጉዳት” ተገኝቶበታል።

ቢቢሲ ያነጋገራት የፓቶሎጂ ባለሙያ ግን ጥያቄዎች አሏት።

የሕጻኑ አስከሬን ላይ የተደረገ ምርመራ ጉበቱ ላይ የደረሰው ጉዳት እና ሞቱ ተፈጥሯዊ እንደሆነ ያሳያል።

ባለሙያዋ ሦስት ተመሳሳይ ጉዳቶች ከዚህ ቀደም እንደገጠሟት ትናገራለች።

ሕጻን መ ወደ ሌላ ክፍል ተዘዋውሮ ሕክምና እንዲደረግለት ሲጠየቅ ሉሲ ፈቃደኛ አለመሆኗ ፍርድ ቤት ተገልጿል።

የሕክምና ማስረጃን በማጭበርበር እና በሕጻኑ የደም ሥር አየር በማስገባት ዐቃቤ ሕግ ተጠያቂ አድርጓታል።ሉሲ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ስትውል።

ሾልከው የወጡ ሰነዶች

ቢቢሲ ያገኛቸው ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2016 ድረስ ሉሲ ትሠራበት የነበረውን ሆስፒታል የጨቅላ ሕጻናት ሞት ጉዳይ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከቶታል።

ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ሠራተኞች የጻፏቸው ሪፖርቶችም ይገኛሉ።

በመጋቢት 2015 (ከመጀመሪያው ሕጻን ግድያ ሦስት ወራት በፊት) የነርሶች ኃላፊ በጻፈችው ሪፖርት እንዳለችው፣ ሆስፒታሉ በቂ እና ብቁ ሠራተኞች አልነበሩትም።

ሁኔታውን ለማስተካከል ዕቅድ ቢኖርም ከአንድ ዓመት በኋላም ችግሩ ቀጥሏል።

በጽኑ የታመሙ ጨቅላ ሕጻናትን ወደ ስፔሻሊስቶች የሚወስዱ ሠራተኞች እጥረት ችግር ተጠቅሷል።

ሐምሌ 2015 በሆስፒታሉ አንድ አደገኛ ፀረ ተዋህሲ መድኃኒትን የሚቋቋም ባክቴሪያ ወረርሽኝ ተነስቶ ነበር።

በባክቴሪያው ምክንያት ሦስት ሕጻናት ሞተዋል።

ባክቴሪያውን ለማጥፋት ቢሞከርም ለስምንት ወራት ሳይጠፋ መቆየቱን ሰነዶች ይጠቁማሉ።

ቢቢሲ እነዚህን ጉዳዮች ከጨቅላ ሕጻናቱ ሞት እና ጉዳት ጋር በቀጥታ ባያስተሳስርም፣ በሆስፒታሉ የነበረውን ችግር ያሳያሉ።

የፍርድ ሂደቱ ውሳኔ አካል የሆነው ከሕዝብ የተውጣጣው ገምጋሚ የሕዝብ ዳኞች ቡድን እነዚህ ጉዳዮች በፍርድ ቤት አልቀረቡለትም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ሉሲ ጥፋተኛ ስለመሆኗ ወይም ስላለመሆኗ ፍረጃ ባይሰጡም፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሂደት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

ሉሲ ላይ የቀረበውን ማስረጃ ሁለት ከሕዝብ የተውጣጡ ገምጋሚዎች እና ሦስት የይግባኝ ፍርድ ቤት ዳኞች ተመልክተው 15 የተለያዩ የዕድሜ ልክ እስራቶች እንደተፈረዱ ዐቃቤ ሕግ ለቢቢሲ ገልጿል።

ሉሲ ዐቃቤ ሕግ ያቀረውን ማስረጃ የተሳሳተ ነው በሚል ይግባኝ ብትልም ጥያቄዋ ውድቅ ተደርጓል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

 

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

 

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)