ስደተኞች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባይገቡ ኖሮ አሜሪካ ምን ትመስል ነበር?

እየተካሄደ ባለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፉክክር በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች ዋነኛ ጉዳይ የምረጫ ቅስቀሳቸው ዋነኛው ርዕሰ ጉዳይ ነው።

የሪፐብሊካን እና የዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ዕጩ ተወዳዳሪዎች ወደ አሜሪካ በተለይም በሜክሲኮ ድንበር በኩል በሚገቡት ስደተኞቸ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

ዶናልድ ትራምፕ ስለ ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢነት ሲያወሱ ክስተቱን ከ“ወረራ” ጋር በማመሳሰለ ነው ደጋግመው የሚያስጠነቀቁት። ተመረጠው ወደ ሥልጣን የሚመለሱ ከሆነም ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኞች በጅምላ ለማባረርም አየዛቱ ነወ።

የዲሞክራቷ ተቀናቃኛቸው ካማላ ሃሪስ በበኩላቸው የቀድሞውን ፕሬዚዳንት በስደተኞች ዙሪያ “ፍርሃት እና መከፋፈል እያቀጣጠሉ ነው” ሲሉ ከሰዋቸዋል።

በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለሚያስፈልገው ለድንበር አጥር ግንባታ እና የሁለቱም ፓርቲዎች ለሚደግፉት የድንበር ደኅንነት ጥበቃ ሕግ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም አክለዋል።

ለመሆኑ ግን ሌላ አገር የተወለዱ በርካታ መጤዎችን ባቀፈችው አሜሪካ ውስጥ ስደተኞች ምን ዓይነት ሚና አላቸው? አሜሪካ ውስጥ ስደተኞች ባይኖሩ አገሪቱ ምን ትመስል ነበር?በሜክሲኮ በኩል የሚደረግ ስደት ጨምሯል

የሕዝብ ብዛት

ለዘመናት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አሜሪካ የገቡት ስደተኞች ባይኖሩ ኖሮ የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በእጅጉ ይቀንስ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2023 ከአሜሪካ ውጭ የተወለዱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ 47.8 ሚሊዮን ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህም ከአጠቃላይ የአሜሪካ ሕዝብ 14.3 በመቶ ያህሉን ይሸፍናል። ከጎረቤቷ ሜክሲኮ የመጡት ስደተኞች 10.6 ሚሊዮን በመሆን ቀዳሚ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፣ በዓለም በሕዝብ ብዛት የመጀመሪያዎቹን ደረጃ ከያዙት ሕንድ በ2.8 ሚሊዮን፣ ከቻይና 2.5 ሚሊዮን ስደተኞች በመምጣት የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የስደተኞች ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም አጠቃላይ የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ግን በወሊድ መጠን መቀነስ ምክንያት እየቀነሰ ይገኛል።

ከአውሮፓውያኑ 1930ዎቹ ወዲህ በአሜሪካ የወሊድ መጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝቅተኛ የሆነው እአአ በ2010 እና 2020 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ይህ ማለት አሜሪካ ልክ እንደሌሎች በርካታ አገራት በዕድሜ የገፉ ሰዎች በብዛት የሚኖሩባት፤ የጤና አጠባበቅ ወጪ እየጨመረ እና ለሥራ ዝግጁ የሆነ ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎች ቁጥር ይቀንሳል ማለት ነው።

በ2040 ደግሞ የሞት መጠን ከወሊድ ምጣኔ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ሲል፣ በአሜሪካ ምክር ቤት (ኮንግረስ) የበጀት ጽህፈት ቤት ትንበያ አመልክቷል።

በዚህም ምክንያት አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እና ስደተኞችን የሚደግፉ ቡድኖች ስደተኞች እንዲገቡ መፍቀዱ በተለይም ለገጠራማ አካባቢዎች የኢኮኖሚውን ለመጠበቅ ወሳኝ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ

ስደተኞች ባይኖሩ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ይጎዳል ሲሉ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ታሪክ ሐሰን ተናግረዋል።

“ስደተኞችን ሙሉ በሙሉ ካስወጣን የምናወራው የነፍስ ወከፍ የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ከአምስት እስከ 10 በመቶ ይቀንሳል። ይህም ማለት የአንድ ሰው ሃብት ይቀንሳል ማለት ነው” ብለዋል።

ስደተኞች “ምርታማነትን የሚያጎለብት ፈጠራን ይጨምራሉ። ስለዚህ በየትኛውም ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይሆንም። በአጠቃላይ የአሜሪካን ኢኮኖሚ አዲስ የፈጠራ አቅምን ያሳድጋል” ሲሉ ጥናታቸውን ተንተርሰው አሳውቀዋል።

ስደተኞች በሥራ ዕድሜ ክልል ውስጥ የመሆን ዕድላቸውም ሰፊ ነው። ስደተኞች ከአሜሪካ ሕዝብ 14 በመቶውን የሚወክሉ ሲሆኑ፣ 19 በመቶ የሚጠጋውን የሰው ሃይል ይይዛሉ።

በሰው ኃይል ተሳትፎም ከአገሬው ተወላጆች የበለጠ መጠን እንዳላቸው መንግሥታዊው የሠራተኛ ስታትስቲክስ ቢሮ ገልጿል።ስደተኞች የዕጩዎቹን የምርጫ ክርክር ሲከታተሉ

በ2022 እና 2034 መካከል ወደ አሜሪካ ከሚገቡት መካከል 16 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሆናቸው ስደተኞች ውስጥ 91 በመቶ ያህሉ ከ55 ዓመት በታች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከአጠቃላዩ የጎልማሶች ቁጥር 62 በመቶውን ይሸፍናል።

እንደ ግብርና ያሉ አንዳንድ የአሜሪካ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች የሚንቀሳቀሱት በስደተኞች ጉልበት ላይ ጥገኛ ሆነው ነው።

በአሜሪካ ብሔራዊ የግብርና ሠራተኞች ዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ 70 በመቶ የእርሻ ሠራተኞች ስደተኞች ናቸው። ነገር ግን አብዛኞቹ ሕጋዊ ምዝገባ የሌላቸው ሰነድ አልባ ናቸው።

እነሱን ማጣት “ብዙ የእርሻ ባለቤቶች ሰብሎችን ለማምረት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ለመሰብሰብ በቂ ጉልበት እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል” ሲሉ የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ምክር ቤት (ኤአይሲ) ተመራማሪ የሆኑት ናን ዉ ተናግረዋል።

ስደተኞች መግባታቸውን የሚተቹ ሰዎች የሚያቀርቡት አንድ መከራከሪያ በዝቅተኛ ክፍያ ለመሥራት ዝግጁ የሆኑ የውጭ አገር ሠራተኞች መብዛት የአገሬው ተወላጆችን ደመወዝ ይቀንሳል የሚለው ነው።

በአውሮፓውያኑ 2014 በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በስደተኞች ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ላይ በተደረጉ 27 ጥናቶች የስደተኞች ደመወዝ በተወላጆች ገቢ ላይ ያለው ተጽዕኖ ዜሮ ነው ሲል ደምድሟል።

በቅርቡ በምሥራቅ ኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት ደግሞ የስደተኞች ቁጥር መጨመር በደመወዝ ዕድገት ላይ “አነስተኛ ቢሆንም አዎንታዊ” ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አረጋግጧል።የአሜሪካ ቪዛ

ግብር

በታክስ/ግብር ገቢ ላይ ያለው ተጽዕኖስ?

በ2022 የስደተኛ ቤተሰቦች አንድ ስድስተኛውን ታክስ አስገብተዋል። ይህም በኤአይሲ ትንታኔ መሠረት 580 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል።

በሕጋዊ መንገድ የደረሱት ስደተኞች ብቻ አይደሉም ግብር የሚያስገቡት ይላሉ የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት ዉ።

ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ከጠቅላላው የስደተኛ ሕዝብ 23 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ። ከ11 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት ሰነድ አልባ ስደተኞች ውስጥ አራት ሚሊዮን ያህሉ ከሜክሲኮ የመጡናቸው ሲል የፒው የምርምር ማዕከል አስታውቋል።

የታክስ እና ኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ባደረገው ጥናት ደግሞ ሰነድ አልባ ስደተኞች በ2022 ብቻ ለፌዴራል፣ ለግዛቶች እና ለአካባቢያቸው ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ታክስ ከፍለዋል።

በኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የኢሚግሬሽን ሕግ እና የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ዳንኤል ኮስታ የስደተኞች ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በአገር አቀፍ ደረጃ አዎንታዊ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ግዛቶች በተለይም በአጭር ጊዜ ውስጥ አሉታዊ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በቅርቡ ባደረጉት ጥናት ዝቅተኛ ደሞዝ የሚያገኙ ስደተኞች አሉ። ለጥቅማጥቅሞች ብቁ መሆናቸው ግን “የፊስካል ሚዛኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አሉታዊ ተፅዕኖ ይወስደዋል” የሚለውን በምሳሌነት አንስተዋል።

በዚህ ምክንያት ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ወደሚገቡባቸው አካባቢዎች ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ለሚነሱ ተግዳሮቶች ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የስደተኞች እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆቫኒ ፔሪ በስደተኞች ምክንያት ማኅበረሰቦች ላይ የሚደርሰው ጫና በአሜሪካ ውስጥ የተወለዱ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር ከሚከሰተው ጋር ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።

“ግንባታው ካልተስተካከለ በአገልግሎቶች እና በቤቶች ላይ ጫና ይፈጥራል…” ብለዋል።ውጤታማው አፕል የተቋቋመው ከሶሪያ ስደተኞች በተገኘው ስቲቭ ጆብስ ነው

ፈጠራ እና የሥራ ፈጠራ

በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ወይም ልጆቻቸው ቀዳሚ ሥራ ፈጣሪዎች ሆነዋል።

ከፎርቹን 500 (በዓመታዊ ገቢያቸው ቀዳሚ የሆኑ 500) ኩባንያዎች ውስጥ 45 በመቶዎቹ በስደተኞች ወይም በልጆቻቸው የተቋቋሙ ናቸው። አንድ ቢሊዮን ዶላር ወይም ከዚያ በላይ ዋጋ ካላቸው ኩባንያዎች ውስጥ 55 በመቶዎቹ በስደተኞች ተመሥርተዋል።

ስደተኞች በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች ውስጥም ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። ብዙዎች ወደ አሜሪካ ያቀኑት በዓለም አቀፍ ተማሪነት ነበር።

በ2022-2023 የትምህርት ዘመን ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች 40 ቢሊዮን ዶላር ለአሜሪካ ኢኮኖሚ አዋጥተዋል። በትምህርት እና በኑሮ ወጪ ደግሞ ከ368 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሥራዎችን ደግፈዋል ሲል የዓለም አቀፍ ምሁራን ማኅበር አስታውቋል።55 በመቶ አሜሪካውያን ስደተኞች እንዲቀነሱ ይፈልጋሉ

የሕዝብ አስተያየት

ስደተኞች ለአሜሪካ ኢኮኖሚ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ቢሆንም በቅርቡ በጋሉፕ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ግን 55 በመቶ አሜሪካውያን ስደተኞች እንዲቀነሱ ይፈልጋሉ።

በተለይም በሜክሲኮ ድንበር በኩል ያለውን ሕገወጥ ስደተኝነትን በተመለከተ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ሰፊ የፖለቲካ መግባባት አለ።

ፕሮፌሰር ፔሪ እንደሚሉት ከሆነ አንዳንድ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ስደተኝነትን “ከድንበር ላይ ትርምስ” ጋር እኩል ያደርጉታል። ለዚህም ከስደተኝነት ሰፊ ተጽዕኖ ይልቅ በሕገወጥ መንገድ የመግባት ታሪኮች ላይ ያተኩራሉ ይላሉ።

“ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለ ስደተኝነት የሚሰሙት ዜና ከደቡብ የአገሪቱ ድንበር በሜክሲኮ በኩል ‘እንደጎርፍ’ ከልክ ባለፈ መልኩ በመግባታቸው ጎጂ ነው ብለው ያስባሉ” ሲሉ አክለዋል።

እንደቦስተን ዩኒቨርሲቲው ታሪክ ሐሰን ደግሞ “ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ስደተኝነት ከፍተኛ ስለነበር አዲስ መጤዎችን የማዋሃድ ማኅበራዊ አቅምን ሊጎዳ ይችላል” ብለዋል።

“ስደተኝነት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በባህላዊ ዘርፎች ላይ በጎ ተጽእኖ ቢኖረውም ሰዎች የማይመቻቸው ገጽታዎች ሊኖሩ ይችላሉ።”

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

 

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

 

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)