ወላጆቻቸው መቀያየራቸውን ዲኤንኤ ያሳወቃቸው የሁለቱ ሴቶች ታሪክ

በዌስት ሚድላንድስ ውስጥ ያሉ ሁለት ቤተሰቦች በወሊድ ጊዜ ልጆቻቸው ስለተቀያየሩ ከኤን ኤች ኤስ ካሳ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ጉዳዩ የተጀመረው የነበረውን ከፍተኛ ጉጉት ተከትሎ ነው። የዲኤንኤ ምርመራ ተደርጎ አስደንጋጭ ውጤት ተገኘ። ሁለት ሴቶች እና ቤተሰቦቻቸው ስለራሳቸው የሚያውቁትን ነገር ሁሉ በድጋሚ እንዲያጤኑት የሚያስገድድ ውጤት ነበር።

የቶኒ ጓደኞች እአአ በ2021 ለገና በዓል በቤት ውስጥ ዲኤንኤ ለመመርመር የሚያስችል መሣሪያ በስጦታ ሰጡት። ለሁለት ወራት ያህል መመርመሪያውን ኩሽና ውስጥ ማስቀመጡንም ረስቶት ነበር።

ከሁለት ወራት በኋላ ግን መመሪያው ትዝ አለው። ቶኒ ሳምንታዊው የጎልፍ ጨዋታው ተሰርዞ ደብሮት ቤት ቁጭ ብሎ ነበር።

በየካቲት አንድ ቀን ድረስ እንደገና አይኑን አልያዘም። በናሙና መቀበያ ቱቦ ውስጥ ምራቁን በማድረግ ለምርመራ ላከው።

ውጤቱ እሑድ ምሽት ደረሰ። ኢሜይሉ ሲደርስው ቶኒ እናቱ ጆአን ጋር ደውሎ እያወራት ነበር።

በመጀመሪያ ሁሉም ነገር እንደጠበቀው መስሎት ነበር። ውጤቱ ግን የሚያሳየው ሌላ ነው። የእናቱ ቤተሰቦች አየርላንድ ውስጥ ከሚገኝ ቦታ እንደመጡ ጠቆመ። በቤተሰቡ አባላት ውስጥ የአጎት ልጅ አለበት። እህቱም ተካታበታለች።

የእህቱን ስም ሲመለከት ግን የሚያውቀው ስም አልነበረም። በጄሲካ ምትክ ክሌር የምትባል ሴት እህቱ ሆና ተመዝግባለች (ለደህንነታቸው ሲባል የጄሲካ እና የክሌር ስም ተቀይሯል።)

ከጆአን አራት ልጆች ቶኒ የበኩር ልጇ ነው። ሦስት ወንድ ልጆችን ካገኘች በኋላ ሴት ልጅ ለመታቀፍ ፈለገች። ምኞቷ ተሳክቶ ጄሲካ እአአ በ1967 ሴት ልጅ አገኘች።

“ሴት ልጅ መውለዴ በጣም ደስ የሚል ስሜት ነበረው” ብላለች ጆአን።

የቶኒ የዲኤንኤ ውጤት ያልተጠበቀ መሆኑን ስትሰማ ጭንቀት ገባት። እሱም ደንግጦ ነበር። እንዲታወቅበት ግን አልፈለገም። አባቱ ከሞተ አሥር ዓመታት አልፈዋል። እናቱ በ80ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ተገኛለች። ከባሏ ህልፈት በኋላ ብቻዋን መኖር ጀምራለች። ሊያስጨንቃት አልፈለገም።

በማግስቱ ጠዋት እህቱ ናት የተባለችውን ክሌርን ለማግኘት ሲል የዲኤንኤ መመርመሪያ ኩባንያው ጋር መልዕክት ላከ።

“ሠላም ቶኒ እባላለሁ። የዲኤንኤ ምርመራ አድርጌያለሁ። እህት እንዳለኝ አሳውቃችሁኝ ነበር። ውጤቱ ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ። ስለጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ ልትሰጡኝ ትችላላችሁ?”

‘እንግዳ እንደሆንኩ ተሰማኝ’

ክሌርም ከሁለት ዓመት በፊት የልደት ስጦታ በሚል ከልጇ ተመሳሳይ የዲኤንኤ መመርመሪያ ተሰጥቷት ነበር።

የእሷም ውጤቷ እንግዳ ነበር። ወላጆቿ ከተወለዱበት ቦታ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራትም ይላል ውጤቱ። የማታውቀው እና ማብራራት የማትችለው የዘረመል ግንኙነት ነበራት።

በ2022 አንድ ተጨማሪ ቤተሰብ እንዳላት መልዕክት ደረሳት።

ግራ የሚያጋባ ነበር። በአንድ በኩል ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነበረው። ክሌር ስታድግ የቤተሰቡ አባል እንዳልሆነች ተሰምቷት አያውቅም።

“እንግዳ እንደሆንኩ ተሰማኝ” ብላለች። “በመልክም ሆነ በባህሪያት ምንም ተመሳሳይነት አልነበረንም” ትለኛለች። “በትክክልም እኔ የማደጎ ልጅ ነኝ ብዬ አሰብኩ።”

ክሌር እና ቶኒ መልዕክቶችን መቀለዋወጥ ጀመሩ። የተለያዩ ቤተሰባዊ ዝርዝር ጉዳዮችን መለዋወጥ ሲጀምሩ ክሌር በተወለደችበት ጊዜ አካባቢ ከጄሲካ ጋር በአንድ ሆስፒታል እንደነበሩ አወቁ። ጄሲካ የቶኒ እህት እንደሆነች እየተነገራት ነው ያደገችው።

በርካታ እውነታዎች ብቅ ማለት ጀመሩ። ሁለቱ ሕፃናት ሴቶች ከ55 ዓመታት በፊት ሲወለዱ ተለዋውጠዋል። በዚህ ምክንያትም በተለያዩ ቤተሰቦች ውስጥ ለማደግ ተገደዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ህጻናት በማዋለጃ ክፍል ውስጥ የሚቀየሩባቸው አጋጣሚዎች አልተለመደም። በ 2017 ፍሪደም ኦፍ ኢንፎርሜሽን ላቀረበው ጥያቄ ኤንኤችኤስ በሰጠው ምላሽ ህጻናት በስህተት ስለመቀያየራቸው የሚገልጽ ማስረጃ እንደሌለው ይገልጻል።

ከ1980ዎቹ ጀምሮ የተወለዱ ሕፃናት ወዲያውኑ የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ መታወቂያ (አርኤፍአይዲ) መለያዎች ይሰጣቸዋል። ይህም ቦታቸውን ለመከታተል የሚያስችል ነው። ከዚያ በፊት ግን የማዋለጃ ክፍል ሠራተኞች በእጅ በተጻፉ መለያዎች እና በአልጋ ላይ የሚለጠፉ ካርዶችን በማጣቀሻነት ይጠቀማሉ።

ዜናውን ለመቀበል የሞከሩት ክሌር እና ቶኒ ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መወሰን ነበረባቸው።

“ጉዳዩን ዝዚሁ ጋር መተው ከፈለግሽ ውሳኔሽን እቀበላለሁ። በድጋሚም አናነሳውም” ሲል ቶኒ ለክሌር ጽፏል።

ክሌር ግን ምንም ሳታመነታ ቶኒን ማግኘት ፈልጋለች። ከእሱ ጋር የምታጋራትን እናቷንም ለማየት ፍላጎት ነበራት።

“ላያቸው፣ ላገኛቸው፣ ላናግራቸው እና ላቀፋቸው ፈልጌ ነበር” ትላለች።

ቶኒ የዲኤንኤ ውጤቱን ለጆአን ነገራት። ይህ እንዴት ሆነ የሚለውን መልስ ለማግኘት በጣም ጓጓች።

እስከ1980ዎቹ ድረስ ህጻናት ሲወለዱ በጽሑፍ መረጃቸው ይጻፍ ነበር

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

በረዷማው ምሽት

ጆአን ሴት ልጇ የተወለደችበት ምሽት በግልጽ ታስታውሳለች። ቤቷ ልትወልድ ነበር። በነበረባት የደም ግፊት ምክንያት ወደ ዌስት ሚድላንድስ ሆስፒታል እንድትገባ ተደረገ።

“እሑድ ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ። ቀኑ በረዶዋማ ነበር” ብላለች።

ህጻኗ የተወለደችው ምሽት 4፡20 አካባቢ ነው። ጆአን በጣም የምትጓጓለኣትን ሴት ልጇን ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበር ያቀፈቻት። አዲስ የተወለደችውን ልጅ ቀይ ፊት እና የተጥመለመለውን ጸጉር ስትመለከት ታስታውሳለች።

እናቷ እንድታርፍ በሚል ህጻኗ ወደ ሕፃናት ክፍል ተወሰደች። ይህ በ1960ዎቹ የተለመደ አሠራር ነበር።ልክ እኩለ ሌሊት አካባቢ ጄሲካ እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ተወለደች።

በማግስቱ ጠዋት ጆአን ልጇ ክሌር ሳትሆን ጄሲካ ተሰጠቻት።

ህጻኗ ከሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት በተለየ መልኩ ጸጉሯ ጥቁር አልነበረም። ጆአን ግን ምንም አላሰሳሰባትም ነበር። ተመሳሳይ ቀለም ያላቸው አክስቶች እና የአጎት ልጆች በቤተሰቡ ውስጥ ነበሩ።

ባለቤቷ ጄሲካን ለማግኘት ሆስፒታል ሲመጣም ሴት ልጅ በማግኘቱ በጣም ተደስተኦ ስለነበር ጥርጣሬ አልገባውም ነበር።

ከሃምሳ አምስት ዓመታት በኋላ ክሌር ምን ዓይነት ሕይወት እንዳሳለፈች ለማወቅ ጆአን በጣም ፈለጋ ነበር። ደስተኛ ሆና አድጋ ይሆን?

እሷ መልስ ከማግኘቷ በፊት ህይወት ዘመኗን በሙሉ ጆአን እናቷ እንደሆነች በማመን ቶኒ ደግሞ ወንድሟ እንደሆነ ለኖረችው ጄሲካ ዜናውን ቶኒ መንገር ነበረበት።

ቶኒ እና ጆአን በአካል ሊነግሯት በመወሰን ወደ ጄሲካ ቤት ሄዱ። ሁልጊዜም እናት እና ልጅ እንደሚሆኑ ጆአን አረጋገጠችላት። ከዚያን በኋላ ግን ግንኙነታቸው እንዳልነበር ትናገራለች።

ጄሲካ ከዚህ ታሪክ ጋር በተያያዘ ቃለ መጠይቅ እንዲደረግላት ፈቃደኛ አልነበረችም።

‘ልክ ሆኖ ተሰማኝ’

ቶኒ የዲኤንኤ ውጤቱን ካገኘ ከአምስት ቀናት በኋላ ክሌር ወደ ጆአን አመራች።

ለዓመታት ወደ ሥራ ስትሄድና ስትመለስ በጆአን ሠፈር መኪናዋን ታስከረክር ነበር። ወላጅ እናቷ የምትኖርበት ቦታ እንደሆነ ግን አታውቅም ነበር።

ቶኒ መኪና መንገድ ላይ ሆኖ እየጠበቃት ነበር። “ሠላም እህቴ። ነይ እና እናታችንን አግኝያት” አላት።

ክሌር ጆአንን ካየችበት ቅጽበት ጀምሮ ሁሌም የሚተዋወቁ ያህል ይሰማት እንደነበር ገልጻለች። “እሷን ስመለከታት ‘አምላኬ ሆይ ዓይናችን አንድ አይነት ነው። አምላኬ ሆይ አንድ ሰው እመስላለሁ'” አለች።

“ልክ ሆኖ ተሰማኝ። “ሳስበው እሷ የጣትነቴ መልኬን ትመስላለች” ብላለች ጆአን።

ከሰዓት በኋላውን የቤተሰብ ፎቶግራፎችን ሲያዩ አሳለፉ። ክሌር ለቶኒ እና ለጆአን ስለጓደኛዋ፣ ልጆቿ እና የልጅ ልጆቿ ነገረቻቸው። እነሱም ስላላገኘችው ወላጅ አባቷም ሁሉንም ነገሯት።

በልጅነቷ ደስተኛ ነበረች ወይ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ክሌር ራሷን አሸሸች።

“ያኔ እውነቱን መናገር አልቻልኩም” ትላለች። “ወላጆቼ ገና ልጅ ሳለሁ ተለያዩ። አብረው ሆነው የነበረውን ጊዜ አላስታውስም። ያደግኩት በፍጹም ድህነት፣ በቤት እጦት ከማደግ ባለፈ ብዙ ጊዜ ርቦኝ ያውቃል። በጣም አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜ ነበር።”

ክሌር ላሳደገቻት እናቷ ዜናውን መንገር እስካሁን በህይወቷ ካጋጠማት ሁሉ ከባዱ ነገር እንደሆነ ተናግራለች።

ያሳደጓትን ሁለቱንም ወላጆቿን በግንኙነታቸው ላይ ምንም እንደማይለውጥ ለማረጋገጥ የቻለችውን ሁሉ እንዳደረገች ትናገራለች። እናቷ ከወራት በፊት ህይወቷ አልፏል።

የዘረመል ማንነት ጋር ከመተዋወቅ በተጨማሪ ክሌር ሌሎችም ነገሮችን አሳውቋታል። ከእኩለ ሌሊት በፊት በመወለዷ ልደት ቀኗ አንድ ቀን ቀደም ብሎ መደረግ ነበረበት። በዚህ ምክንያትም “የልደት ሰርተፊኬቴ፣ ፓስፖርቴ፣ የመንጃ ፈቃዴ – ሁሉም ነገር ስህተት ነበር” ስትል ገልጻለች።

‘አሳዛኝ ስህተት’

ከዚህ ክስተት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ክሌር እና ጄሲካ የተቀያየሩበትን ሆስፒታል ለሚቆጣጠረው የኤንኤችኤስ የበላይ አካል የዲኤንኤ ምርመራዎች ውጤቶችን በመግለጽ ቶኒ ደብዳቤ ጻፈ።

የበላይ አካሉ ስህተቱን አምኗል። ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ቢሆነውም እስካሁን በካሳ ጉዳይ አልተስማማም። ቶኒ እና ጆአን ባለፈው ዓመት እንደሚጠናቀቅ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

በኤንኤችኤስ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚያስተናግድ የኤንኤችኤስ ሪዞሉሽንን ቢቢሲ አነጋግሯል። በህጻናቱ መለዋወጥ ህጋዊ ተጠያቂነትን እንዳለበት ጠቅሶ “አሳዛኝ ስህተት” ተፈጥሯል ብሏል።

“ልዩ እና ውስብስብ ጉዳይ” እንደሆነ እና ሊከፈል የሚገባውን የካሳ መጠን ላይ ለመስማማት እየሠራ መሆኑን ጠቅሷል።

ክሌር እና ጆአን ምግብ እና ልብስን ጨምሮ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች እያወቁ ነው። በአየርላንድ ያሉ ዘመዶደቻቸውን ለማወቅ እረፈት ላይ ነበሩ። ያለፈውን ገናንም አብረው አክብረዋል።

ክሌር አዲስ ስላገኘችው ቤተሰቧ “በጣም ቅርብ ግንኙነት አለን” ስትል ተናግራለች። “ጊዜው ቢያልፍም አሁንም ቢሆን ከእነሱ ጋር የምችለውን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እፈልጋለሁ።”

ክሌር አሁን “እናቴ” ስትል ጆአንን የምትጠራት ቢሆንም ጄሲካ ግን እናቴ ማለቷን አቁማለች። ጆአን ግን ሴት ልጅ እንዳገኘች ይሰማታል።

“ጄሲካ ልጄ አለመሆኗ እኔ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም” ብላለች። እሷ አሁን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ልጄ ሆና ትቀጥላለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

 

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

 

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)