እስራኤል እርቃናቸውን ባሰረቻቸው ፍልስጤማውያን ወንዶች መካከል የተያዘችው የሦስት ዓመቷ ሕጻን

የእስራኤል ጦር ልብሳቸውን አስወልቆ በአንድ ስፍራ ላይ ሰብስቦ ከያዛቸው ፍልስጤማውያን ወንዶች መካከል አንዲት የሦስት ዓመት ሕጻን ያለችበት ፎቶ ይፋ ሆኗል።

ትንሿ ሕጻን ከጀርባ ቁጢጥ ብላለች።

ወታደሮቹ በጅምላ በቁጥጥር ስር ያዋሏቸውን ወንዶች እርቃናቸውን በውስጥ ሱሪያቸው ብቻ እንዲቀሩ አስገድደዋቸዋል። አንዳንዶቹም በዕድሜ አረጋውያን ናቸው።

በጦርነት በፈራረሱ ሕንጻዎች አካባቢ በሚገኝ አንድ ሜዳ ላይ በጅምላ እርቃናቸውን ተሰብስበዋል። ዓይናቸው ፎቶውን እያነሳ ባለው ሰው ላይ እንደተከሉ ናቸው።

ፎቶውን የሚያነሳው ግለሰብ የእስራኤል ወታደር ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

ምሥሉ በመጀመሪያ የተሠራጨው በእስራኤል መከላከያ ውስጥ ጠንካራ ምንጮች ባሉት ጋዜጠኛ ቴሌግራም ገጽ ላይ ነው።

ወንዶቹ ተጎሳቁለዋል። ፍራቻ እና ድካም እንደተጫጫናቸው በፎቶው ላይ እንኳን ማየት ይቻላል።

ሕጻኗ ካሜራውን ፊት ለፊት እየተመለከተች አይደለም። ምናልባትም ከካሜራው ውጭ ያለ ነገር ቀልቧን ስቦት ሊሆን ይችላል። ወይም ወታደሮቹን እና ያነገቱትን ጠመንጃ ማየት አልፈለገች ይሆናል።

የእስራኤል ጦር በጅምላ በቁጥጥር ስር ያዋልኳቸው ወንዶች የጦር መሳሪያዎች ይዘው ወይም የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ታጥቀው እንደሆነ እንዲሁም ከሐማስ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ለመመርመር እንደሆነ ነው ይላል።

አረጋውያን ሳይቀሩ እንዲህ ተጎሳቁለው እርቃናቸውን መታየታቸው የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ማን እንደሆነ ማሳያ ነው። የትንሿ ሕጻን በዚህ ስፍራ መያዝ፣ ፎቶዋ ላይ የሚታየው ገጽታ ማን ናት? ምን አጋጥሟት ነው? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

ፎቶው የተነሳው ከአንድ ሳምንት በፊት ነው። እስራኤል በተቀናጀ መልኩ በምትፈጽመው የማያባራ ጥቃት በዚህ ሳምንት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

በርካቶች ቆስለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን አጥተው ተፈናቅለዋል። በአየር ጥቃቱ ሕጻናት ተገድለዋል፤ በፍርስራሽ ስር ተቀብረው ሕይወታቸው ተነጥቋል።

የቢቢሲ አረብኛ ጋዛ ፕሮግራም የልጅቷን ማንነት ለማወቅ ፍለጋ ጀመረ። እስራኤል ቢቢሲንም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ወደ ጋዛ እንዳይገቡ ከልክላለች። ቢቢሲም መረጃዎችን ለማግኘት በቦታው ያሉ አስተማማኝ ጋዜጠኞችን እና የዜና ወኪሎችን ይጠቀማል።

የቢቢሲ አረብኛ ፕሮግራም ጋዜጠኞች በሰሜን ጋዛ የሚገኙ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ ላሉ ምንጮቻቸው ፎቶውን ላኩላቸው።

በ48 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ መጣ። አግኝተናታል የሚል።

የሦስት ዓመቷ ጁሊያ አቡ ዋርዳ አሁንም በሕይወት አለች። ለቢቢሲ የሚሠራው ጋዜጠኛ ታዳጊዋ ከቀየዋ ተፈናቅላ ወደተጠለለችበት ጋዛ ከተማ አቀና።የሶስት ዓመቷ ህጻን ጁሊያ ከአባቷ ጋር

በስፍራውም ሲደርስ ጁሊያ ከአባቷ፣ ከአያቷ እና ከእናቷ ጋር ነበረች።

ሕጻኗ የዶሮ የካርቱን ገጸባህርያት ሲዘፍኑ እየተመለከተች ቢሆንም የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለየት ያለ ጩኸት ድምጹን ለመስማት ፈታኝ አድርገውታል።

“ማነሽ?” አባቷ እየሳቀ ይጠይቃታል።

በተኮላተፈ አንደበቷ “ጁሊያ” መለሰች።

ከሳምንት በፊት በእስረኞች መካከል ያየናት ጁሊያ አካሏ አልተጎዳም። ፀጉሯ ደማቅ ሰማያዊ አበቦች ባሉት የፀጉር ጌጥ ተይዟል። ጋዜጠኛውን ጭንቅ ባለ ሁኔታ መመልከት ጀመረች።

ከዚያም አባቷ መሐመድ ከፎቶግራፉ በስተጀርባ ያለውን ታሪክ መናገር ጀመረ።

የእስራኤልን የአየር ጥቃት እና የከባድ መሳሪያ ድብደባ ለማምለጥ እና ሕይወታቸውን ለመታደግ ባለፉት 21 ቀናት ብቻ ቤተሰቡ አምስት ጊዜ ተፈናቅሏል።

ፎቶው በተነሳበት ዕለት የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን ፍልስጤማውያንን ከየቤቶቻቸው ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሲያስተላልፍ ሰምተዋል።

“የመሳሪያ ድምጽ ዝም ብሎ ሲንጣጣ ይሰማል። ወደ ጃባሊያ የስደተኞች ማዕከል ልናቀና ተነሳን” ይላል።

ቤተሰቡ የተወሰኑ ልብሶች፣ የታሸጉ ምግቦች እና ጥቂት የግል ንብረቶቻቸውን ይዘው ነው እንደገና ለመሰደድ የተነሱት።

መጀመሪያ ሁሉም ቤተሰቡ አንድ ላይ ነበር ሲጓዝ የነበረው። የጁሊያ አባት፣ እናቷ አማል፣ የአንድ ዓመት ከሦስት ወር ጨቅላ ወንድሟ ሃምዛ፣ አያቷ፣ ሁለት አጎቶች እና የአጎት ልጅ ነበሩ።

በግርግሩ መሃል አባቷ እና ጁሊያ ከሌሎቹ ጋር ተለያዩ።

አባት እና ልጅ በሚጎርፈው ሰው መካከል አብረው ተጓዙ። ጎዳናዎቹ የሞት ማዕከላት ሆነዋል። “አስከሬኖቹ ጎዳናዎች ላይ ተረፍርፈዋል። ሁሉ ነገር ወድሟል” ይላል መሐመድ።

በርካታ ሕጻናት በረገፉበት በዚህ ጦርነት አሰቃቂ እልቂትን ማየት የህጻናቱ የየዕለት እውነታ ከሆነ ከረመ።

በጅምላ እየተጓዘ የነበረው ሕዝብ የእስራኤል የፍተሻ ኬላ ላይ ደረሰ።

“በታንኮች ላይ የተጫኑ ወታደሮች እንዲሁም እግረኛ ጦር ነበር። ተፈናቅሎ እየተጓዙ ወደነበሩት ፍልስጤማውያን ተጠግተው ወደላይ መተኮስ ጀመሩ። ሕዝቡ ተኩሱን ሲሰማ እርስ በርስ መገፋፋት ጀመረ” ይላል።

ከዚያም ወንዶች ልብሳቸውን እንዲያወልቁ እና በውስጥ ሱሪያቸው እንዲቀሩ በወታደሮቹ ታዘዙ። የእስራኤል መከላከያ አጥፍቶ ጠፊዎችን ለመፈለግ እና የተደበቁ መሳሪያዎችን ለማግኘት ነው በሚል ፍልስጤማውያኑን እርቃን የማስቀረት ተግባር የተለመደ ተግባር ነው።

በዚህ የፍተሻ ኬላ ከልጁ ጋር ለሰባት ሰዓታት ያህል በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መሐመድ ይናገራል። በፎቶው ላይ ጁሊያ ተረጋግታ የምታይ ቢመስልም አባቷ ግን ምን ያህል እንደተጨነቀች ያስታውሳል።

ከተለቀቁ በኋላ “መጮህ ጀመረች፤ እናቷን እንደምትፈልግ ነገረችኝ” ይላል። የእነ ጁሊያን ቤተሰብ ጨምሮ የእስራኤልን ጥቃት ለመሸሽ የተፈናቀሉት ሰዎች አነስ ወዳለች ስፍራ ደረሱ።

በመጨረሻም ቤተሰቡ ተገናኘ። የቤተሰቡ ትስስር ጥብቅ ነው። ከጃባሊያ ቤተሰቦች ተፈናቅሎ ወደ ጋዛ ከተማ ሲመጣ ወዲያውኑ ነው ዘመድ ወዳጁ የሚሰባሰበው። ጁሊያም በሚወዷት ዘመድ፣ ወዳጅ ተከበበች። ጣፋጮች እና የድንች ቺፕስም ቀረበላት።

የሦስት ዓመቷ ጁሊያ በዚህች የጨቅላነት ዕድሜዋ ብዙ መከራ ማየቷን አባቷ ይናገራል። በጣም የምትወደው ያህያ የሚባል የአጎት ልጅ ነበራት።

የሰባት ዓመቱ ያህያ እና ጁሊያ ብዙ ጊዜ ጎዳና እየወጡ አብረው ይጫወቱ ነበር። ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ያህያ መንገድ ላይ እያለ እስራኤል በፈጸመችው የድሮን ጥቃት ተገደለ።የሶስት ዓመቷ ህጻን ጁሊያ ከአባቷ ጋር

ከያህያ ግድያ በኋላም “ድብደባ ሲፈጸም ወደላይ እያሳየች “አውሮፕላን” ትላለች። ቀና ብላ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ሲያንዣብቡ ሁልጊዜም እንደጠቆመች ነው” ይላል።

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ መረጃ መሠረት 14 ሺህ ፍልስጤማውያን ሕጻናት ተገድለዋል።

“ባልጀመሩት ጦርነት ሕጻናት በየቀኑ ዋጋ እየከፈሉ ነው” ሲሉ የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጆናታን ክሪክስ ይናገራሉ።

“ያገኘኋቸው አብዛኞቹ ሕጻናት የሚወዷቸውን ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ አጥተዋል” ይላሉ።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋዛ ሰርጥ ሁሉም በሚባል ደረጃ፣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት የአዕምሮ ጤና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይገምታል።

በሕይወት የተረፉ እንደ ጁሊያ ያሉ ሕጻናትን ዕድለኛ ማለት ከባድ ነው። ያየችውን ሰቆቃ፣ ያጣቻቸውን ቤተሰቦች እንዲሁም አሁን ያለችበትን ሁኔታ ለማሰብም ያስቸግራል። በዚህ ዕድሜዋ ሕይወት በአስደንጋጭ ሁኔታ እንደምትቀጭ እና ስለ ጥልቅ ሐዘንን ታውቃለች።

ሕጻናትን ቤተሰብ ነበር የሚጠብቀው ነገር ግን የአየር ጥቃት፣ የከባድ መሳሪያ ድብደባ፣ ረሃብ እና በሽታ ግን ከእነሱ አቅም በላይ ናቸው።

የጁሊያም የወደፊቷ ዕጣ ፈንታ በዕድል ላይ የሚወሰን ይሆናል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)