በአሜሪካ ምርጫ እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን ማንን ይደግፋሉ? ትራምፕን ወይስ ካማላ?

ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመረጡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ደስታቸውን ለመግለፅ አንድ መንደር በስማቸው ሰየሙ።

ትራምፕ ሃይትስ በጎላን ተራሮች አካባቢ የሚገኙ ድንጋያማ እና በማዕድን የተሞላ ሥፍራ ነው።

ትራምፕ የጎላን ተራሮች ያሉበትን ቦታ የእስራኤል ነው ብለው ዕውቅና ሰጡ። በግማሽ ምዕተ ዓመት ይህ ያደረጉ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ናቸው።

ጎላን በአውሮፓውያኑ 1967 ጦርነት ከሶሪያ የተወሰደ መሬት ሲሆን፣ በኋላ የእስራኤል ክፍል ሊሆን ችሏል።

በዚህ ሥፍራ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥራቸው ትንሽ ነው። ከሁለት ደርዘን አይበልጥም። ወታደሮችም በአካባቢው ይኖራሉ።

ሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ አሊያም ዲሞክራቷ ተቀናቃኛቸው ካማላ ሃሪስ መመረጣቸው ለቀጣናው ሀገራት ምን ትርጉም አለው?

ኤሊክ ጎልድበርግ እና ባለቤቱ ሆዳያ አራት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ትራምፕ ሃይትስ ያቀኑት ትንሿን መንደር ለመጠበቅ በሚል ነው።

ባለፈው ዓመት መስከረም ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከፈተች። በስተደቡብ በኩል እስራኤል የሐማስ አጋር ከሆነው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር ስትዋጋ ተመልክተዋል።

ውጊያው እነ ኤሊክ ከሚኖሩበት 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ሲካሄድ የነበረው።

“ባለፈው አንድ ዓመት የሚያምረው አረንጓዴ ጓሯችን በጭስ ታፍኖ ነበር። ሄዝቦላህ ሮኬት ወደኛ ሲተኩስ ለማየት ተገደናል” ይላል ኤሊክ። “ይህ የጦርነት ቀጣናዊ ነው። መቼ እንደሚጠናቀቅ የምናውቀው ነገር የለም።”

ኤሊክ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር “ትክክለኛው ነገር እንዲያደርግ” ይጠይቃል። ትክክለኛው ነገር ምንድነው? ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ “እስራኤልን መደገፍ” ነው።

“መልካሞቹን ሰዎች መደገፍ። ትክክለኛ እና ትክክለኛ ያልሆነውን ነገር መለየት” ይላል።ኤሊክ እና ባለቤቱ

እስራኤል ውስጥ በብዛት የሚሰማ ሐሳብ ነው። ትራምፕም ይህን ሐሳብ ያንፀባርቃሉ።

ትራምፕ ፕሬዝደንት ሳሉ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ዘንድ ተቀባይነት ነበራቸው። እስራኤል ስትቃወመው የነበረውን ከኢራን ጋር የተገባውን የኑክሌር ስምምነት ውድቅ አድርገዋል። ከአረብ ሀገራት ጋር ስምምነት እንዲኖር አግዘዋል። እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ብለዋል።

ኔታኒያሁ በአንድ ወቅት “በዋይት ሐውስ ታሪክ ምርጡ የእስራኤል ጓደኛ” ሲሉ ትራምፕን አንቆለጳጵሰዋቸዋል።

አሜሪካውያን ድምፃቸውን ለመስጠት ዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ኔታኒያሁ ለሪፐብሊካኑ ዕጩ ያላቸውን አድናቆት ከመግለፅ አልተቆጠቡም።

በቅርቡ የተሰበሰበ ድምፅ ውጤት እንደሚጠቁመው ሁለት ሦስተኛው እስራኤላዊያን ትራምፕ ፕሬዝደንት ሆነው ቢመረጡ ይሻሉ። ከ20 በመቶ በታች የሚሆኑት ደግሞ ካማላ ሃሪስ ወደ ዋይት ሐውስ እንዲመጡ ይፈልጋሉ።

በመካነ ይሁዳ ገበያ ማዕከል ስትገበያይ የነበረችው የ24 ዓመቷ ጂሊ እንደምትለው ካማላ ሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ ደጋፊዎች እስራኤል የዘር ጭፍጨፋ አካሂዳለች ብለው ሲወቅሱ የመስማማት ምልክት ማሳየታቸው “ትክክለኛ አቋማቸውን” ያንፀባረቀ ነው ትላለች።

ምክትል ፕሬዝደንቷ “[ድምፁን የሚያሰማው ግለሰብ] እያለ ያለው ነገር ትክክል ነው” ብለው ነበር።

ነገር ግን ከቅስቀሳው በኋላ በሰጡት አስተያየት እስራኤል የዘር ጭፍጨፋ እያደረገች ነው ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።

በገበያ ማዕከሉ ስትዟዟር የነበረችው ሪቭካ ዶናልድ ትራምፕን “መቶ በመቶ” እንደምትደግፍ ትናገራለች።

የእስራኤል ዜጎች እንደሚያምኑት አጋር ሀገራት ጫና አይፈጥሩም፣ አይወቅሱም አሊያም እንቅፋት አይሆኑም።

ካማላ ሃሪስ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። በተለይ ደግሞ ሰብዓዊ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ባፈለው ሐምሌ በዋይት ሐውስ ኔታኒያሁን ካገኟቸው በኋላ በጋዛ ስላለው ሁኔታ “ዝምታን እንደማይመርጡ” ገልፀው ለኔታኒያሁ “በጋዛ ያለው ስቃይ እና የንፁሃን ግድያ” እንደሚያሳስባቸው መናገራቸውን ጠቁመዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ጦርነቱ የሚያበቃው እስራኤል “ድል ስታደርግ ነው” ይላሉ። የተኩስ አቁም ስምምነቱን የማይቀበሉት ትራምፕ ኔታኒያሁ “የሚያደርጉትን አድርገው” ጦርነቱን እንዲቋጩ ይፈልጋሉ።ኔታኒያሁ እና ካማላ ሀሪስ

በርካታ ፍልስጤማውያን በሁለቱም ዕጩዎች ላይ ተስፋ የላቸውም።

“ዲሞክራቶች መልካም አይደሉም። ነገር ግን ትራምፕ የሚመረጡ ከሆነ ሁኔታዎች እጅግ የከፉ ሊሆኑ ይችላሉ” ይላል ዌስት ባንክ የሚገኘው ፍልስጤማዊው ተንታኝ ሙስጠፋ ባርጎቲ።

“ካማላ ሃሪስ ተመረጡ ማለት ምናልባት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ ማለት ነው።”

በጋዛው ጦርነት ምክንያት እንደ ሳዑዲ አረቢያ ያሉ የአሜሪካ አጋሮች ፍልስጤም ራሷን የቻለች ሀገር እንድትሆን ጥሪ ማቅረብ ጀምረዋል።

ነገር ግን ሁለቱም ዕጩዎች ፍልስጤም ራሷን የቻለች ሀገር ስለመሆኗ ጉዳይ የምርጫ ቅስቀሳ አጀንዳቸው ውስጥ አላካተቱም።

ትራምፕ በምርጫ ክርክር ወቅት ፍልስጤም ሀገር የመሆኗን ጉዳይ ይደግፉታል? ተብለው ሲጠየቁ “የምናየው ይሆናል” የሚል መልስ ነው የሰጡት።

በርካታ ፍልስጤማውያን ሀገር የመሆን ጉዳይ በተለመከተ ተስፋ የቆረጡ ይመስላል። በተለይ ደግሞ በአሜሪካ ላይ ተስፋ ቆርጠዋል።

“አሜሪካ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመጠበቅ ረገድ ስኬታማ አይደለችም የሚል እሳቤ አለ። ከአንድም ሁለት ሦስቴ የፍልስጤማውያንን እምነት በልታለች፤ ከእሰራኤል ጋር ወግናለች” ይላል ሙስጠፋ።

በመካከለኛው ምሥራቅ ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ የኢራን ነገር ነው። ትራምፕ በቅርቡ እስራኤል “የኑክሌር ጣቢያ እንድትመታ እና ለተቀረው ሌላ ጊዜ እንድትጨነቅ” ምክር ለግሰው ነበር።

“ትራምፕ ኃይለኛ ጎናቸውን ስለሚያሳዩ ኢራኖች እንዲህ አይተናኮሱም ነበር” ይላሉ በአሜሪካ የቀድሞው የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ አያሎን።

ትራምፕም ሆኑ ሃሪስ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንድትገነባ አይፈልጉም። በሌላ በኩል እስራኤል ከአረብ ሀገራት በተለይ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላት ግንኙነት የለዘበ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

ለእስራኤል እና ለአሜሪካ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ካማላ ሃሪስ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ የነበረውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያስቀጥላሉ ብለው ያምናሉ።

ዶናልድ ትራምፕ ግን ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት አዳጋች ነው። ቢሆንም አሜሪካ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ አይሹም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)