መስከረም አበራ በቀረበባት የኮምፒውተር ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተባለች
“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ መሥራች እና ባለቤት መስከረም አበራ በቀረበባት የኮምፒውተር ወንጀል ክስ ጥፋተኛ መባሏን ጠበቃዋ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ብይኑን ያስተላለፈው አርብ ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም. የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ልዩ ልዩ ከባድ ወንጀሎች ችሎት ነው።
ከጠበቆቿ አንዱ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በመስከረም አበራ ላይ ባቀረበው “በኮምፒውተር ተጠቅማ በኅብረተሰብ መካከል አመጽ፣ ሁከት እና ግጭት ለማነሳሳት ሞክራለች” ክስ ጥፋተኛ ናት ብሏል።
መስከረም ኢትዮ ንቃት በተሰኘው ዩቲዩብ ገጽ ላይ የተላለፉ ሁለት ፕሮግራሞች ናቸው በኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ጥፋተኛ ያሰኟት።
ቀዳሚው ፕሮግራም ሚያዝያ 4/2014 ዓ.ም. “መልዕክት ለጄኔራል አበባው ታደሰ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሦስት ቀናት በኋላ በተመሳሳይ የዩቲዩብ ገጽ ሚያዝያ 7/2014 “አማራ ክልል ምን እየተደረገ ነው?” በሚል ርዕስ የተላለፈ ነው።
ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት በሁለቱም ተደራራቢ ክሶች መስከረም አበራ ጥፋተኛ ሆና እንዳገኛት በይኖ የቅጣት ውሳኔውን ለማስተላለፍ ለኅዳር 2/2017 ዓ.ም። ቀጠሮ ይዟል።
መስከረም አበራ የቀረቡባት ክሶች “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን” የሚጋፉ ናቸው በማለት ያቀረበችው መከራከሪያ “የሃሳብ ነጻነት ገደብ ያለው” እና ካቀረበቻቸው ፕሮግራም አንጻር ፍርድ ቤቱ ተገቢነት ያለው ሆኖ አላገኘሁትም በማለት ውድቅ ማድረጉን ጠበቃ ሔኖክ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
መስከረም አበራ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ዓ.ም. በመተላለፍ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷም በእያንዳንዱ ክስ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቅጣት ፍርድ ቤቱ ሊበይንባት እንደሚችል የገለጹት አቶ ሔኖክ፤ ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ክሶች ደምሮ ተገቢ ነው የሚለውን የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በዛሬው ችሎት ከጥፋተኝነት ብያኔው በኋላ የቅጣት ማቅለያ እንዳላት መስከረም መጠየቋን የገለጹት ጠበቃ ሔኖክ ያቀረበቻው መከላከያዎች በሙሉ አንዳልታዩላትቅሬታ አቅርባለች።
“ለፍርድ ቤቱ ያቀረብኳቸው ወደ አስር የሚጠጉ የመከላከያ ቪዲዮዎች አሉ። ፕሮግራሞቹን ስሠራ መሠረት ያደረግኩባቸው ናቸው። ፍርድ ቤቱ ግን የተመለከተው አንደኛውን ቪዲዮ ነው” የሚል ቅሬታን አቅርባለች።
ፍርድ ቤቱ ሁሉንም ቪዲዮዎች እንደተመለከተ የገለጸ ቢሆንም እሷ ግን ብይኑ ካቀረባቻቸው መከላከያዎች የጠቀሰው አንዱን ብቻ በመሆኑ ሁሉም መከላከያዎች ታይተዋል የሚል እምነት እንደሌላት መግለጿን አስረድተዋል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እንዳስተላለፈ እና መከላከያዎቼ አልታዩልኝም የሚለውን በይግባኝ መጠየቅ እንደምትችል እና ለብያኔው የቅጣት ማቅለያ ታቀርቢያለሽ ወይ? ተብላ በድጋሚ መጠየቋን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል።
እሷም “የቅጣት አስተያየት አላቀርብም። ፍርድ ቤቱ ያቀረብኳቸውን መከላከያዎች ያላየልኝ ስለሆነ ከዚህም በኋላ የማቀርበውን ነገር ያይልኛል ብዬ አልገምትም። የቀረበብኝን ክስ አምኜ የማቀርበው የቅጣት ማቅለያ የለኝም” የሚል አስተያየት መስጠቷን ገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የሠራችው ፕሮግራሞች ሕብረተሰብን ከሕብረተሰብ አመጽ እና ሁከትን የሚያነሳሳ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ከበድ ያለ ቅጣት እንዲያስተላልፍባት ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱ የሚወስነውን የቅጣት ውሳኔ ተከትሎ መስከረም ያቀረበችው ሰፊ የሆነ መከላከያ እና ማስረጃ አልታየልኝም ቅሬታ በይግባኝ ወይም በዚሁ ይቋጭ የሚለው በደንበኛቸው ሂደት እንደሚወሰን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል።
የቪዲዮ ማስረጃዎቹ አልተዳሰሱም ከሚለው በተጨማሪ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላት የጠየቃቸቸው ባለሥልጣናት በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አለማግኘቱም ሌላ ጠበቃዋ የሚያነሱት ቅሬታ ነው።
መስከረም ታኅሣሥ 2015 ዓ.ም. ለተመሠረተባት የኮምፒውተር ወንጀል ክስ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ እና የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለን በመከላከያ ምስክርነት እንዲጠሩላት ጠይቃ ነበር።
“እነዚህ ምስክሮች የሚያስረዱላት ጉዳይ ምን እንደሆነ እሱን በአስረጂነት ካቀረበች በኋላ መጥሪያ እንደሚደርሳቸው ተገልጾላት ነበር” ብለዋል ጠበቃው።
እሷም በምላሹ “በአሠራሩ መሠረት መጥሪያ ለመስጠት ምንድን ነው የምታስረዳው ተብሎ ፍርድ ቤቱ መጥሪያ አይጽፍም። ምስክሩ ከቀረበ በኋላ ነው ምስክሩ ምን እንደሚያስረዳ ለፍርድ ቤቱ ነጥብ የሚያስይዘው በሚል ብትከራከርም ፍርድ ቤቱ አልተቀበላትም” ይላሉ።
“ይህ ነገሩን የሚያጓትት እና መፍትሄ የማገኝበት ስላልሆነ መከላከያ ምስክሮቼን አንስቻለሁ” ማለቷንም ጠበቃዋ ገልጸዋል።
መስከረም አበራ ከዚህም በተጨማሪ በእነ ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ፣ ከዳዊት በጋሻው፣ ከጎበዜ ሲሳይ እና ከገነት አስማማው ጋር “የሽብር ድርጊት በመፈጸም” ወንጀል ክስ እንደቀረበባት ይታወሳል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)