ለ58 ዓመታት ቦትስዋናን በበላይነት የመራው ፓርቲ በምርጫ ተሸነፈ
በአልማዝ በበለጸገችው ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ቦትስዋና ፖለቲካዊ ስር ነቀል በሚባል ለውጥ አገሪቱን ለ58 ዓመታት ያህል በበላይነት ያስተዳደረው ገዥ ፓርቲ በምርጫ መሸነፉን የመጀመሪያው ውጤት አሳየ።
አገሪቱ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ከአውሮፓውያኑ 1966 ጀምሮ አገሪቷን የመራት የቦትስዋና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቢዲፒ) ሶስት የፓርላማ ወንበሮችን ብቻ ማሸነፉን አርብ፣ ጥቅምት 22/ 2017 ዓ.ም ይፋ የሆነው የቆጠራ ውጤት ያሳያል።
ገዢውን ፓርቲ አምብሬላ ፎር ዲሞክራቲክ ቸንጅ (ዩዲሲ) የተሰኘው ፓርቲ ሊተካው የተዘጋጀ ይመስላል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞክግዌትሲ ማሲሲ ፓርቲያቸው ረቡዕ በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ በሰፋ ድምጽ መሸነፉ ግልጽ ነው ሲሉ አምነዋል።
ምንም እንኳን ቦትስዋና በአስደናቂ ለውጥ ላይ የተጓዘች አገር ብትሆንም በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ የምጣኔ ኃብት ቀውስ፣ ከፍተኛ ስራ አጥነት የገዢውን ፓርቲ ተቀባይነት በከፋ ጎድቶታል።
“በክብር ከስልጣንም ሆነ ከኃላፊነቴ እለቃለሁ እና ከሲመቱ በፊት ባለው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እሳተፋለሁ” ሲሉ አርብ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
አክለውም “ተቃዋሚዎች ባስመዘገቡት ድል እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እመኛለሁ። የምርጫውን ውጤትም በጸጋ እቀበላለሁ። በዲሞክራሲያዊ ሂደታችን ኩራት ይሰማኛል እናም የህዝብን ፍላጎት አከብራለሁ” ብለዋል።
ደጋፊዎቻቸው ተረጋግተው ከአሸናፊው አዲሱ መንግሥት ጎን እንዲቆሙም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አሸናፊው ዩዲሲ እና ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች በመዲናዋ ጋቦሮኔ እና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች በድሉ ላይ የተሰማቸውን ደስታ እየገለጹ ይገኛሉ።
“ይህንን ለውጥ በህይወቴ ውስጥ አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር” ሲል በጋቦሮኔ ጎዳናዎች ላይ ሰልፍ ከወጡት መካከል የ23 ዓመቷ ተማሪ ምፎ ሞጎሮሲ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግራለች።
“ገዢው ፓርቲ ለረጅም ዘመናት በስልጣን ላይ ቆይቷል እናም አገራችን የተሻለች እንድትሆን በምርጫ ያስወገደው ትውልድ አካል በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል” ብላለች።
በሰብዓዊ መብት ጠበቃ ዱቦ ቦኮ የሚመራው አምብሬላ ፎር ዲሞክራቲክ ቸንጅ በመጀመሪያ ደረጃ ቆጠራው መሰረት 27 መቀመጫዎችን አሸንፏል።
ፓርቲው እስካሁን ባለው በፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መቀመጫ እንደኖረው ያረጋገጠው ሲሆን 31 መቀመጫዎችን ካሸነፈ ብቻውን በዋነኝነት ገዢ ፓርቲ መሆን ይችላል።
ፓርቲው ሰራተኞች ጥሩ ደመወዝ የሚያገኙበት ፣ የስራ እድል የሚፈጠርበት እና ሃብት ለሁሉም ዜጎች በተገቢው መንገድ የሚከፋፈልበት አዲስ የምጣኔ ኃብት ስትራቴጂ ለመንደፍ ቃል ገብቷል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)