የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ የማይቀለበስ አቋም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ሐሙስ ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላችው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ላይ ነው።

በሦስተኛው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ከተገኙት 320 አባላት መካከል፤ 15ቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ የማቅረብ ዕድል አግኝተዋል። ከእነዚህ ጥያቄ አቅራቢዎች መካከል አብዛኞቹ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተመራጭ የፓርላማ አባላት ናቸው።

እነዚህ የምክር ቤት አባላት በጥያቄ እና አስተያየቶቻቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለአመራራቸው” በርከት ያሉ ሙገሳ እና ውዳሴዎችን አሰምተዋል።

የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት ደግሞ ከሰላም እና ከፀጥታ፣ ከምጣኔ ሃብት እና ከዲፕሎማሲ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ እና ማብራሪያቸውን በሁለት ክፍል ለይተው ለፓርላማ አባላት አቅርበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሾች ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

“ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ያስፈልጋታል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የባሕር በር በማግኘት ጉዳይ ላይ መንግሥታቸው “ወደ ኋላ የማይል ይፋዊ አቋም” አለው በማለት ነገር ግን ይህንን ለማሳካት ጦርነትም ሆነ የኃይል አማራጭን እንደማይፈልጉ አመልክተዋል።

“ፍላጎታችንን ማሳካት የምንሻው በሰላማዊ አማራጭ ነው። ይህ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ጥያቄ ነው፤ እኛ ባናሳካው ልጆቻችን ያሳኩታል፡፡ ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር ላይ ወረራም ሆነ ጥቃት አትፈጽምም” በማለት ነገር ግን ኢትዮጵያን ለመንካት የሚሞክሩ ካሉ ለመመከት የሚያስችል አቅም አገሪቱ እንዳላት ገልጸዋል።፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያን ማንም ሰው ዛሬ በኃይል ሊወር አይችልም። ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም አለን፤ ስንገዛ ስንሸምት የነበርንባቸውን በውጊያ ክፍተት የገጠሙ ነገሮችን ማምረት ጀምረናል” ሲሉ ተናገሩ።

ዐቢይ በምላሻቸው ማጠቃለያ፤ “[ሌሎች] አገራት ኢትዮጵያን ሊወሩ ይችላሉ የሚል ስጋት” ያለባቸው ሰዎች መኖራቸውን በመጥቀስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ኢትዮጵያን ማንም ሰው ዛሬ በኃይል ሊወር አይችልም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም አለን፤ ስንገዛ ስንሸምት የነበርንባቸውን [እና] በውጊያ ክፍተት የገጠሙ ነገሮችን ማምረት ጀምረናል። ሰው አንነካም ከነኩን ግን ለማንም አንመለስም ስጋት የለብንም” ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት ከወረራ ጋር የተያያዘ ጥያቄም ሆነ ስጋት ባያቀርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን “ስጋት አይግባችሁ ማንም ቢመጣ አሳፍረን እንመልሳለን ማንንም ግን አንነካም እኛ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ እና ከሕዳሴው ግድብ ጋር የተያያዙ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ተከትሎ “ኢትዮጵያ የሶማሊያን ግዛት ልትወስድ ተስማማች የሚል ትርክት ነው ለመፍጠር የተሞከረው” ያሉት ዐቢይ፤ “እኛ ግን የ50 ዓመት ነው ሊዝ የፈረምነው። እንዴት ነው የ50 ዓመት ሊዝ መሬት መቀማት የሚሆነው?” ሲሉ ተናግረዋል።

ዐቢይ አክለውም “ከሶማሊያ ጋር ምንም አጀንዳ የለንም እኛ አጀንዳችን ኢኮኖሚያችን እያደገ ነው ሕዝባችን እያደገ ነው። እኛ ከፈረስን ሁላችሁም ትጠፋላችሁ ትልቅ ስለሆንን ጥያቄያችን ይሄ ነው” ብለዋል።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የባሕር በር አልባ ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር መተላለፊያ ማግኘት አለባት የሚል አቋም የያዘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በተደጋጋሚ ፍላጎቱን ሲገልጽ ቆይቷል።

በዛሬው የምክር ቤት ውሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በርን በተመለከተ “ኢትዮጵያ የማይናወጥ ብሔራዊ ጥቅም አላት፣ ዓለም ዛሬም ይስማ የቀይ ባሕር መተላለፊያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። በዚህ ጉዳይ ላይ የምንሽኮረመም፣ የምንደበቅ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል” ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላው ያብራሩት ጉዳይ ከኤርትራ ጋር የተያያዘ ነው። “ከኤርትራ ጋር አንዳንድ ወሬ ይነሳል የምንፍለገው ሰላም ነው። ከዚያ የከፋ ነገር ካልመጣ በስተቀር በእኛ አነሳሽነት በኤርትራ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ነገር አይፈጸምም” ብለዋል።

“አማራ [ክልልን] የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገናታል”ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድጠቅላይ ሚኒስትሩ የማብራሪያቸውን ሁለተኛ ክፍል የጀመሩት በሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ነው። በዚህኛው ክፍል በተለየ መልኩ ስለ አማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዛሬው ዕለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረቡ አባላት መካከል የአማራ ክልልን ጉዳይ ያነሱት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ዶ/ር አበባው ደሳለው ናቸው።

ዶ/ር አበባው፤ “በአሁኑ ሰዓት በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ብሶት አለ። በተለይም በአማራ ክልል ያለው ችግር ደግሞ አጠቃላይ አገሪቱን እኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ምስቅልቅል እንዲሆን ያደረገ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የፓርላማ አባሉ አክለውም “አሁንም ንጹሃን ዜጎች በከባድ መሳሪያ እና በድሮን እየሞቱ ነው። ሲቪል ተቋማት የሚባሉ የጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤቶች እየወደሙ ነው። በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልል እና በተለያዩ አካባቢዎች እስር ቤቶች የተጨናነቁት ያለፍርድ በታጎሩት አማራዎች ነው” ብለዋል።

“መንግሥት የሰላም እና የፀጥታ ችግርን ለመፍታት እየሄደ ያለው አካሄድ ወታደራዊ ነው” ያሉት ዶ/ር አበባው፤ “ፖለቲካዊ አካሄድን ለምን አልደፈረም? ለምንድን ነው ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ መንግሥት የደከመው?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

አባሉ መንግሥት “ለእውነተኛ ድርድር እና ውይይት በይፋ ጥሪ አቅርቦ ችግሩን ለምንድን ነው ለመፍታት የማይተጋው? የጅምላ እስር፣ የጅምላ ግድያስ የሚቆመው መቼ ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችንም አስከትለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው “በተደጋጋሚ” የሰላም ጥሪ ማወጁን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

“በአማራ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ፣ በኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች [ጋር] ንግግር አለ” ያሉት ዐቢይ፤ “ነገር ግን ንግግር የሚያደርጉትን እና ሰላም የሚፈልጉትን ሰዎች እንዴት ትነጋገራለህ ከዚህ መንግሥት ጋር ብለው የሚወቅሱ ሰዎች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶ/ር አበባው በአማራ ክልል የጅምላ እስር፣ ግድያ እና እንግልት አለ ማለታቸውን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸው ልምድ ግን ተለየ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ባለፉት ስድስት ዓመታት አማራ የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገናታል” ያሉት ዐቢይ፤ “አማራ ክልል የብልጽግና መንግሥት የፈጠረውን ኢንደስትሪ በየትኛውም ዘመን አግኝቶ አያውቅም” ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህ ንግግራቸውም የተወሰኑ የአማራ ክልል ከተሞችን እየጠቀሱ የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎችን ዘርዝረዋል።

“የአማራ ክልል ላይ እኛ ልማት ነው እያመጣን ያለነው ልማቱን እንደልባችን እንዳንሰራ ያደናቀፉን ሰዎች ግን አሉ” ያሉት ዐቢይ፤ “እዚያ የሚፈሰው ጥይት ድካም ተሰብስቦ በጣም ብዙ ቁም ነገር ሊሠራ ይችላል” ብለዋል።

ከጅምላ እስር ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዐቢይ “በጅምላ የፓርላማ አባላት፣ በጅምላ የፖለቲካ ሰዎች የምናስር ቢሆን እርስዎም ይታሰሩ ነበር። በጅምላ አይደለም በግብር ነው ሰው የሚታሰረው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

“ሥራቸው የብላክ ማርኬት ማሯሯጥ የሆኑ ኢምባሲዎች አሉ”

ከሰላም እና ከፀጥታ እንዲሁም ዲፕሎማሲ ጉዳዮች በተጨማሪ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይም ሰፋ ያለ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። የዐቢይ የኢኮኖሚ ማብራሪያ ሰፊውን ጊዜ የወሰደው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው “የኢኮኖሚ ሪፎርም” ላይ ነው።

መንግሥታቸው “ሪፎርም” የጀመረው “አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንድ” እና “አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለት” ብሎ መሆኑን ዐቢይ ለምክር ቤት አባላት አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት መጨረሻ መተግበር ጀመረው የፖሊሲ ለውጥ “እነዚያን ሪፎርሞች የቋጨንበት ለቀሪ ሥራዎች መቋጫ ያበጀንበት የመጨረሻው የሪፎርሙ አካል ነው እንጂ አሁን የተጀመረ ሪፎርም አይደለም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “ይሄ ሪፎርም እውነት ለመናገር ቀድሞ መጀመር ነበረበት በጣም ነው የዘገየው፤ ኢትዮጵያን አይመጥንም” ሲሉ ተደምጠዋል።

“የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ሪፎርም በጣም ተጠቃሚ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ነው” ያሉት ዐቢይ፤ “ይህ ሪፎርም ባይሠራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፈርስ ነበር” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “በዚህ ሪፎርም 900 ቢሊዮን ብር የተራዘመ ቦንድ” ማግኘቱን ገልጸዋል።

“ንግድ ባንክ ወደቀ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ 30ውም ባንኮች ወደቁ ማለት ነው። ዋናው የኢትዮጵያ ባንክ ንግድ ባንክ ነው፤ እሱን ማዳን የባንክ ሴክተሩን ማዳን ነው” ሲሉ “የኢኮኖሚ ሪፎርሙ” ለባንክ ዘርፉ ያለውን ሚና አብራርተዋል።

ጨምረውም ከውጭ ምንዛሬ እና ትዩዩ ገበያ ጋር በተያያዘ ባንኮችን፣ ኤምባሲዎችን እና ኩባንያዎችን በኃይለ ቃል ወቅሰዋል።

“ባንኮች ኮሚሽን ስለለመዱ፣ በትክክለኛው ሕጋዊ መንገድ ከሚሠራው ይልቅ የትይዩ ማርኬት ውስጥ ተዋናይ መሆን ስለሚጠቅማቸው የኢትዮጵያ የፋይናሻል ሥርዓት ጤናማ በሆነ መንገድ እንዳያድግ የሚያበላሹ ግለሰቦች እና ቡድኖች አሉ፤ እነዚህ በባንክ ስም የሚዘርፉ ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ባንኮች ሕግ እና ሥርዓት አክብረው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገትን በሚያረጋግጥ መንገድ ሊሠሩ ይገባል እንጂ በባንክ ስም የአራጣ ሥራ የሚሠሩ ከሆነ ችግር ነው” ብለዋል።

ከባንኮች በመቀጠል ዐቢይ ወቀሳ ያቀረቡባቸው በውጭ አገራት ያሉ የአገሪቱን ኤምባሲዎችን ነው።

በዚህ ወቀሳቸው “ቀጥ ብለው የኢትዮጵያን ሀብት የመዝረፍ እና የውጭ ምንዛሬ ቢዝነስ የሚሠሩ ኢምባሲዎች አሉ” ብለዋል። አክለውም “ሥራቸው ይሄ የሆነ ላይም ጥብቅ ክትትል ይደረጋ የማይታረሙ ከሆነ እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“ጤናማ ዝምድና የማያደርግ የትኛውንም ኤምባሲ እኛ አንፈልግም” ያሉት ዐቢይ፤ “እኛ የምንፈልገው ጤናማ ሕጋዊ ሥርዓት ያለው መንገድ የሚከተልን ብቻ ነው። ያን ሥራ የሚሠሩ ነገር እንዳናበላሽ የታገስናቸው ሥራቸው ግን የብላክ ማርኬት ማሯሯጥ የሆኑ ኢምባሲዎች አሉ” ብለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)