የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ተግባራዊነት ስለመዘግየቱ ምን ይላሉ?

ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ የባሕር በር፣ ሶማሊላንድ ደግሞ የአገርነት ዕውቅናን ለማግኘት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት ከተጋጋለ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው።

ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት በማለት ስምምነቱን የተቃወመችው ሶማሊያ ኢትዮጵያን ከመክሰስ እና ከማውገዝ በሻገር ችግሩ በአካባቢው ጦርነት እስከመቀስቀስ ሊያመራ ይችላል ስትል ቆይታለች።

በተጨማሪም ከግብፅ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት በመፈራረም ውጥረቱ ሌላ ገጽታ እንዲይዝ አድርጋለች።

ከየትኛውም አገር ይፋዊ ዕውቅናን ያላገኘችው ነገር ግን አንድ አገር ሊኖረው የሚገባውን መስፈርት እንደምታሟላ የሚነገርላት ሶማሊላንድ ከየትኛውም ወገን ተቃውሞ እና ጫና ቢመጣ ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሶማሊላንድ ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ ከቢቢሲ ሶማሊኛ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በደረሰችው የመግባቢያ ስምምነት እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የመግባቢያ ስምምነት ከምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተጠየቁት ቢሂ፣ “ምንም ነገር ሳይቀየር በነበረበት እንዳለ ነው። በመግባባት ደረጃ ላይ ነው ያለው። ሁሉም ወገን የተግባራዊነት ሰነዱ መቼ እንሚፈረም እየተጠባበቀ ነው” በማለት አስር ወራትን ያስቆጠረው ስምምነት እንዳለ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ሶማሊያ ተቃውሟዋን እያሰማች ሲሆን፣ ኢትዮጵያንም ሉዓላዊነቷን በመጣስ ከመክሰስ ባሻገር ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከምትገኘው ግብፅ እና ግንኙነታቸው እየሻከረ ካለው ከኤርትራ ጋር ዘርፈ ብዙ የትብብር ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ውዝግብ መፈጠሩን ያመለከቱት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ለምን ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ተፈራረመች በሚል “ሐሰን ሼክ [የሶማሊያው ፕሬዝዳንት] ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ከፈተ” በማለት ስምምነቱ ከሶማሊያ ግዛት ጋር ሳይሆን ራሷን ከቻለች አገር [ሶማሊላንድ] ጋር የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

“እኛ ከኢትዮጵያ ጋር ነው የተስማማነው። የእኛ ነው ወደሚለው [ፕሬዝዳንት ሐሰን] መሬት መሄድም ሆነ መቆጣጠር እንደማይችል ያውቀዋል። ለ34 ዓመታት ሁለት የተለያየን ነጻ አገራት ነን፤ ሁለት መንግሥታት ነን፤ ሁሉም ያውቀዋል” ብለዋል።

ከስምምነቱ በኋላ አለመግባባቱ መካረሩን የሚጠቅሱት ፕሬዝዳንት ቢሂ “ጦርነት ታቅዶ ነበር። ግብፅ እንድትገባበት ተደረገ፤ ውዝግብ ተፈጠረ። ይህ ተጨማሪ ነገር ነው፤ መፍትሄም አይሆንም” በማለት “ፕሬዝዳንት ሐሰን ሁለት የተለያየን መንግሥታት መሆናችንን ከተረዳ እና ከእኛ ጋር ንግግር ከፈለገ መልካም ነው” ሲሉ ሶማሊያም አገርነታቸውን ከተቀበለች ለንግግር በራቸው ክፍት መሆኑን አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በሶማሊላንድ መሬት የሚመለከታቸው ነገር አለመኖሩን ጠቅሰው “ለኢትዮጵያ መሬት ሰጡ” በማለትም የሚናገሩት የማይመለከታቸውን ጉዳይ ነው ሲሉ አጣጥለው ኢትዮጵያ ውስጥም ሶማሊዎች አሉ ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሶማሊዎች አሉ፤ በመንግሥት ውስጥም ቦታ ያላቸው ናቸው። ታዲያ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ተፈራረማችሁ በማለት ሶማሊያ ለምንድን ነው የምትከሰን?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ስለዚህም በመጪው ኅዳር 4/2017 ዓ.ም. በሶማሊላንድ በሚካሄደው ምርጫ ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩት ሙሳ ቢሂ ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የደረሰችው የወታደራዊ ትብብር ስምምነቱ የሶማሊላንድ ሕዝብ የነጻ አገርነት ፍላጎትን ለማስቆም የታለመ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነት አንድ ዓመት ሊሞላው ሁለት ወራት ቀርተውታል። ነገር ግን የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት እንደሚሉት መዘግየቱ ጉዳዩ ሰፊ ጊዜን የሚጠይቅ እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ወደ ተግባር ለመቀየር በርካታ ዓመታትን የሚጠይቁ መሆናቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።

በሶማሊያ በኩል የተደረገ ጫና በስምምነቱ መዘግየት ላይ ምንም ሚና እንደሌለው የተናገሩት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ቢሂ “የመግባቢያ ስምምነቱ የራሱን ጊዜ እየተከተለ ነው። የመጨረሻውን ሁለቱ አገራት የሚወስኑት ይሆናል” በማለት ጉዳዩ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ እጅ ላይ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት የተፈራረመችውን ግብፅን በተመለከተም፤ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ባለባት የአባይ ውሃ ውዝግብ ውስጥ ሶማሊያን በማስገባት እየተጠቀመችባት ወደ ጦርነት ልታስገባት ነውም ብለዋል።

የራሷ ችግር አለባት ያሏትን ግብፅ የሶማሊያ መንግሥት ወደ ቀጣናው ውዝግብ ማስገባቱ ትክክል አይደለም ያሉት ቢሂ፣ የወታደራዊ ስምምነቱ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ካለባት ውዝግብ በተጨማሪ በሶማሊላንድ ላይ ጭምር ያነጣጠረ ነው ሲሉ ከሰዋል።

“እሳቤው ግብፅን በመከራየት የደኅንነት ስምምነት በመፈራረም በሶማሊላንድ ላይ ለመጠቀም ነው፤ ነገር ግን ትክክል አይደለም። የራሷ ችግር ያለባት ግብፅ ከዚህ ችግር የምታተርፍበት አይሆንም። ስለዚህ ትኩረቱ የመግባቢያ ስምምነቱ ሳይሆን ሐሰን [ፕሬዝዳንት] ግብፅን በሶማሊላንድ ላይ ለመጠቀም ነው።”

በሶማሊላንድ ነጻ አገርነት ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር ለድርድር እንደማይቀመጡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሚደመጡት ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ጋር በተገናኙበት ጊዜ ይህንኑ አስረግጠው እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ላይ የመግባቢያ ስምምነቱን ከመፈረሙ ቀናት ቀደም ብሎ ቢሂ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጂቡቲ ላይ አግኝተዋቸው እንደነበር አስታውሰው “ጥቂት ቃላት ነው የተለዋወጥነው፤ እሱም ሁሉም ያውቀዋል። እሱም እኛ ‘ሶማሊላንድ ነጻ አገር ናት’ ስንል፣ ሐሰን ሼክ ደግሞ ‘ሶማሊያን ልከፋፍል አልችልም፤ እናንተም የእኛ አካል ትሆናላችሁ’ የሚል ምላሽ ሰጠ” ብለዋል።

የራሷ ምክር ቤት እና መንግሥት፣ ገንዘብ፣ ማዕከላዊ ባንክ፣ ጦር ሠራዊት ያላት ሶማሌላንድ በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ እና በአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ ምርጫ ታካሂዳለች።

ዘንድሮም ኅዳር 4/2017 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ ከሌሎች ሁለት ዕጩዎች ጋር በድጋሚ ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚወዳደሩ ይሆናል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)