ሶማሊያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በ72 ሰዓታት ከአገሯ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

ከሶማሊላንድ ጋር በተፈረመ የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ቁርሾ ውስጥ የገባችው ሶማሊያ አሊ መሀመድ አደን የተባሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማት በ72 ሰዓታት ከአገሯ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች።

በኢትዮጵያ ኤምባሲ በአማካሪነት እያገለገሉ ያሉት አሊ መሃመድ አደን “ከዲፕሎማሲ ሚናቸው ጋር በማይሄዱ ተግባራት እየተሳተፉ ነው” ሲል የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቅምት 19/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አትቷል።

በሞቃዲሾ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት አሊ መሃመድ አዳን ይህ ማስታወቂያ በደረሳቸው በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፎባቸዋል።

የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊ ከዲፕሎማሲ ተልዕኳቸው ውጭ ስለተሳተፉበት ተግባር ዝርዝር ባይሰጥም ድርጊታቸው “በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የተደረሰውን የቪየና ስምምነትን የሚጥስ ነው” ብሏል።

ሚኒስቴሩ በቪየና የተደነገገውን ዲፕሎማቶች የሚሰማሩባቸውን አገራት ህግ እንዲያከብሩ እና በውስጥ ጉዳዮች ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚደግጉ አንቀጾችን ጥሰዋል ሲል ከሷቸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማቱ መባረር ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።

ሶማሊያ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ተቀማጭ የነበሩትን የኢትዮጵያ አምበሳደር ሙክታር ሞሐመድ ዋሬ በ72 ሰዓታት ውስጥ ሞቃዲሾን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟ ይታወሳል።

የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ወሰድኩት ባለችው እርምጃ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር ከማባረር በተጨማሪ አዲስ አበባ ያሉትን አምባሳደሯን ጠርታለች።

በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ እንዲሁም በፑንትላንድ ዋና ከተማ ጋሮዌ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በአንድ ሳምንት እንዲዘጉ በወቅቱ የሶማሊያ ምክር ቤት ውሳኔ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ፣ ሃርጌሳ የሚገኘውን የቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ሙሉ አገልግሎት ወደሚሰጥ ኤምባሲ ማሳደጓን የሶማሊላንድ የመረጃ የባህል፣ እና ሶማሊላንድ የመረጃ፣ የባህል እና የብሔራዊ መመሪያ ሚኒስትር አሊ ሐሰን መሐመድ (አሊ ማርሃን) ከጥቂት ወራት በፊት ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ ሶማሊላንድ ነጻነቷን በማወጅ እንደ አገር የተመሠረተችበትን ዕለት ግንቦት 10/2016 ዓ.ም. 33ኛ ዓመት ስታከብር ሃርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ወደ ኤምባሲ ማደጉን ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸውን በሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎም እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ አለም አቀፉ ማህበረሰብ “የኢትዮጵያን ጥሰቶች በማውገዝ ከሶማሊያ ጎን እንዲቆም” በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ “የባህር በር መዳረሻን ሽፋን በማድረግ የሶማሊያን ግዛቶች ለመጠቅለል እየሞከረች ነው” ሲሉ ከሰዋል።

በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሶማሊያውን ጠቅላይ ሚኒስትር አስተያየት ውድቅ አድርገው “የኢትዮጵያ ስም ከየትኛውም ውንጀላ ጋር በፍጹም ሊያያዝ አይችልም” ብለው ነበር።

በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ እየመጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ እንዲሁም በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረቶች ነግሰዋል።

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከር እየተገለጸ በሚገኝበት ወቅት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሶማሊያ እና ከግብፅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከሩ ነው።

በቅርቡም የግብፅ፣ የሶማሊያ እና የኤርትራ ፕሬዝዳንቶች የጋራ የሦስትዮሽ ጉባዔ ለማድረግ በኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ መገኘታቸው ይታወሳል።

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብፅ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናን ስጋት ላይ ጥሏል።

ግብፅ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ በሁለት ዙር በአውሮፓላን እና በመርከብ የተጫኑ የጦር መሳሪያዎች መላኳን ተከትሎ ውጥረቶቹ ተካረዋል።

የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች።

የሶማሊያ መንግሥትንም “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራ ይገኛል” ስትል ከሳለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)