እስራኤል የተባበሩት መንግሥት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲን አገደች
የእስራኤል ፓርላማ የተባበሩት መንግሥት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ በእስራኤል እና እስራኤል በምትቆጣጠረው ምስራቅ እየሩሳሌም እንዳይንቀሳቀስ የሚያግድ አዋጅ አፅድቋል።
በውሳኔው መሠረት በተለምዶ ኡንርዋ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ በሶስት ወራት ውስጥ አካባቢውን ለቆ መውጣት አለበት።
በኤጀንሲው እና በእስራኤል ባለሥልጣናት መካከል የሚደረገው ግንኙነት የሚቋረጥ ሲሆን ድርጅቱ በጋዛ እና በዌስት ባንክ መንቀሳቀስ ሊያዳግተው ይችላል።
የእስራኤል ጦር ወደ ጋዛ የሚያስኬደውን መንገድ ስለሚቆጣጠር ኤጀንሲው ያለጦሩ ፈቃድ ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባት አይችልም። ኤጀንሲው በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ያለ ብቸኛው የተባበሩት መንግሥታት ተቋም ነው።
የኡንርዋ ሠራተኞች እስራኤል ውስጥ ለመሥራት የነበራቸው ፈቃድ የሚሰረዝ ሲሆን ምስራቅ እየሩሳሌም የሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤትም ይዘጋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አዲሱ ሕግ “በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል እንዲሁም በቀጣናው ሊፈጠር የሚገባውን ሰላም እና ፀጥታ የሚያጨልም ነው” ያሉ ሲሆን የኡንርዋ ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ በበኩላቸው “የፍልስጤማዊያንን ስቃይ የበለጠ የሚጨምር” ውሳኔ ነው ብለዋል።
ዩናይትይት ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን በእስራኤል ውሳኔ የተሰማቸውን ስጋት ገልፀዋል።
የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ውሳኔውን “በፍፁም ትክክል ያልሆነ” ሲሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ደግሞ “በጋዛ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ የሚጎዳ ነው” የሚል ስጋታቸውን አሰምተዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ኡንርዋ በጋዛ ሰርጥ ሰብዓዊ እርዳታ በማድረስ “ትልቅ” ሚና የሚጫወት ኤጀንሲ መሆኑን አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት ከ2 ሚሊዮን በላይ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን እርዳታ የሚያገኙት በኤጀንሲው በኩል ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ “በሽብርተኝነት ተግባር ላይ የተሰማሩ የኡንርዋ ሠራተኞች ተጠያቂ ሊሆን ይገባል” ብለው ነገር ግን በጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኤክስ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የእስራኤልን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ተባብረን ለጋዛ ሰላማዊ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳት ለማድረስ ዝግጁ ነን” ሲሉ ፅፈዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን።
እስራኤል ኡንርዋ በጋዛ በመንቀሳቀሱ ያላትን ተቃውሞ ለዓመታት ስታሰማ ብትቆይም በተለይ በቅርብ ዓመት የበለጠ ቅዋሜዋ ጠንክሯል።
እስራኤል እንደምትለው የኡንርዋ ሠራተኞች በጋዛ ከሐማስ ጋር ይሠራሉ፤ አልፎም 19 የኡንርዋ አባላት ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም ባደረሰው ጥቃት ላይ እጃቸው አለበት ስትል ትወቅሳለች።
ኡንርዋ በእስራኤል ክስ መሠረት ምርመራ ከፍቶ ወቀሳ የቀረበባቸውን 9 የኤጀንሲውን አባላት ያባረረ ቢሆንም እስራኤል ጠለቅ ያለ ማስረጃ አላቀረበችም ሲል ተችቷል።
ኤጀንሲው እንደሚለው ከሐማስ ጋር የሚተባበረው የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ብቻ ነው።
ኡንርዋ ለበርካታ አስርት ዓመታት በጋዛ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን የሰብዓዊ እርዳታ ጨምሮ የጤና አገልግሎት እና ትምህርት ሲያቀርብ ቆይቷል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)