በመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ውስጥ የፓርቲ አባላትን የሚያግደውን አንቀፅ የሚሽር ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ
የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባል እንዲሆኑ የሚፈቅድ ረቂቅ የአዋጅ ማሻሻያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው።
አዲሱ ማሻሻያ በቦርዱ አቅራቢነት በፓርላማ ይሾሙ ነበሩትን የባለሥልጣኑን ዋና ዳይሬክተር ሹመት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰጥቷል። እነዚህን ማሻሻያዎች የተደረጉበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው “የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ” ነው።
ቢቢሲ የተመለከተው ረቂቅ አዋጅ መግቢያ ማሻሻያው ያስፈለገው “ከመገናኛ ብዙኃን ሪጉላቶሪ ሥልጣን እና ተግባራት አንጻር [በአዋጁ ላይ] አስተዳደራዊ ክፍተቶች የተስተዋሉ በመሆኑ [ነው]” ይላል።
“እነዚህን ክፍተቶች በማስተካከል የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዲቻል” ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ መዘጋጀቱን መግቢያ ያትታል።
ነገ በሚኖረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ረቂቅ አዋጅ ካደረጋቸው ማሻሻያዎች መካከል አብዛኛው የባለሥልጣኑን ቦርድ የሚመለከቱ ናቸው።
በነባሩ አዋጁ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተቀጣሪዎችን የቦርድ አባል ከመሆን የሚያግደው የአዋጅ ድንጋጌ በማሻሻያ ረቂቁ ተሰርዟል።
በ2013 ዓ.ም. የወጣው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት የቦርድ አባላት ሆነው የሚመረጥ ግለሰብ “የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ ያልሆነ” መሆን እንዳለበት ይደነግጋል።
ነገር ግን ይህ የአዋጁ ድንጋጌ ቢኖርም ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት በመጋቢት 2014 ዓ.ም. የመገናኛ ብዙኃን ባለሥጣን የቦርድ አባላት ሆነው ከተሾሙት ዘጠኝ አባላት መካከል አራቱ ከብልጽግና ፓርቲ እና የምክር ቤት ተመራጭ ነበሩ።
በጊዜው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ የነበሩት እና የአሁኑ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ሁሴን የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመው ነበር። የቀድሞዋ የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው በፓርላማው ተሹመው ነበር።
ከሁለት ባለሥልጣናት በተጨማሪ በጊዜው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ አቶ ሐሰን አብዱልቃድም በቦርድ አባልነት ተሹመዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህሯ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ ተመራጯ ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ ከተሾሙት የቦርድ አባላት መካከል ናቸው።
በጊዜው ይህ ሹመት በፓርላማ ሲጸድቅ ሹመቱ “የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን የጣሰ ነው” የሚል ትችቶች ቀርቦበት ነበር።
ከአንድ ዓመት በፊት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የታሰሩት አቶ ክርስቶያን ታደለ፤ “በምን አግባብ ነው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የገዢው ፓርቲ አባላት ይህን የዲሞክራሲ ተቋም በቦርድ አመራርነት እንዲመሩ ወደዚህ የቀረቡት?” የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር።
የፓርላማው የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ “ከመንግሥት አካላት የቀረቡ አመራሮችን በተመለከተ አዋጁ ላይ የተቀመጠውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ነው እንጂ የሚጣረስ አይደለም የሚል እምነት አለኝ” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ሹመት ከምክር ቤት አባላት በተጨማሪ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
ከሹመቱ አንድ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን “በተጻረረ መንገድ” የሾሟቸውን የቦርድ አባላት ከኃላፊነት እንዲያነሱ ጠይቆ ነበር።
የቦርድ አባላት ለሹመት ፓርላማ ሲቀርቡ ተጥሷል የተባለው የአዋጅ ድንጋጌ አሁን በማሻሻያ ረቂቁ ተሰርዟል።
ረቂቁ ማሻሻያ ያደረገበት ሌላኛው ጉዳይ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የሚሾሙበትን አካሄድ ነው። በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ዋና ዳይሬክተሩ የሚሾሙት በቦርዱ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነበር።
በረቂቅ ማሻሻያው ይህ ደንጋጌ፤ “የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል” ተብሎ ተስተካክሏል።
በነባሩ አዋጅ ለቦርዱ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት ኃላፊነቶች አሁን ለባለሥልጣኑ ተሰጥተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በነባሩ አዋጅ ቦርዱ ፈቃድ መስጠት እና መሰረዝን እንዲያከናውን የቦርድ አባል ወይም ኮሚቴ ውክልና መስጠት አይችልም ነበር።
በማሻሻያ ረቂቅ አውጁ መሠረት ቦርዱ ፈቃድ መስጠት እና መሰረዝን በውክልና ለማንኛውም የቦርድ ኮሚቴ ወይም የቦርድ አባል ለመስጠት የመወሰን ሥልጣን ይኖረዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)