ትራምፕ ለአሜሪካ ከፈጣሪ የተላኩ መሪ ናቸው ብለው የሚያምኑት ቀኝ ዘመም ክርስቲያኖች

በደቡብ ኦክላሆማ ግዛት ውስጥ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በሚኖሩባት ኤልጂን በሚገኘው የግሬስ ሪፎርምድ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን የእሑድ ጉባኤ ከመካሄዱ ከደቂቃዎች በፊት የ36 ዓመቱ ፓስተር ደስቲ ዲቨርስ ዝንጥ ብለው በፈገግታ ታጅበው ብቅ አሉ።

ወደ 100 የሚጠጉ ምዕመናንን ሰላም አሉ። አብዛኞቹ ብዙ ልጆች ያሏቸው ነጮች ናቸው።

በቤተ ክርስቲያኑ አዳራሽ ውስጥ ሕይወት የሌለው ሕፃን የሚመስል ሥዕል የያዙ አንዳንድ መጽሔቶች አሉ።

ፅንስ ማቋረጥ የዘመናችን “እልቂት” እንደሆነ ለመግለጽ “ይህንን በሚያነቡበት ጊዜ በአሜሪካ ውስጥ ሦስት ልጆች በእናቶቻቸው ማህጸን ውስጥ በግፍ ተጨፍጭፈዋል” ይላል ብለዋል።

ፅንስ ማቋረጥ፣ ከምጣኔ ሀብት እና ከስደተኞች ጉዳዮች ጋር ከሳምንት በኋላ በሚካሄደው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከዋና ርዕሰ ጉዳይ አንዱ ሆኗል።

እነዚህ መጽሔቶች መራጮች አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ በተዘጋጁበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ውስጥ ያሉ በጣም ወግ አጥባቂ የቀኝ ዘመም ፕሮቴስታንት መራጮች ዘንድ ፖለቲካ እና ሃይማኖት ምን ያህል እንደተሳሰሩ የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ነው።

በሞቃታማ የበጋ ቀናት የእሑድ ጉባኤ ጠዋት 4፡45 ላይ ይጀምራል። ፓስተሩ ጊታር በመጫወት ከምዕመናኑ ጋር ይዘምራሉ።

ዲቨርስ በኤልጂን የተወለዱ ሴናተር ሲሆኑ ስድስት ልጆች አሏቸው። በሃይማኖታዊ ጥናቶች የማስተርስ ዲግሪ እና በሪል ስቴት ንግድ ላይ የተሰማሩ ናቸው። እሑድ እሑድ ከቤተ መቅደስ ይሰብካሉ። ከሰኞ ጀምሮ ደግሞ በኦክላሆማ የሕዝብ እንደራሴዎች መሰብሰቢያ ውስጥ ሕጎችን ሲያወጡ ሊገኙ ይችላሉ።

በኦክላሆማ ውስጥ ፖለቲከኞች በአካባቢያቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ማገልገል ወይም ጠንካራ ግንኙነት መፍጠራቸው የተለመደ ነገር ነው።

በፖለቲካ እና በሃይማኖት ውስጥ ያለው የሁለትዮሽ አመራር በተለምዶ የዩናይትድ ስቴትስ መጽሐፍ ቅዱስ ጠናካራ ተጽእኖ ባለው ባይብል ቤልት ተብሎ በሚጠራው እና ኤልጂን በምትገኝበት ሰፊ የአሜሪካ ክፍል የተለመደ ነው። ይህ አካባቢ ቢያንስ ዘጠኝ የፕሮቴስታንት እና የሪፐብሊካን ግዛቶችን ያካተተ ሰፊ ግዛት ነው።

በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው ባይብል ቤልት ወግ አጥባቂ የፕሮቴስታንት መሪዎች የፖለቲካ ተጽዕኖ ዋና ማዕከል ነበር።

ዋናዋ እምብርት ደግሞ ኦክሎሃማ ናት። ከ80 በመቶ በላይ የአካባቢው የሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ሪፐብሊካን የሆኑበት ግዛት ስትሆን ጥልቅ ሃይማኖተኞችም ናቸው።

ፈጠሪ እና አገር በኦክላሆማ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉዳዮች ናቸው። ምክንያቱም ወግ አጥባቂ ክርስቲያኖች ባህላዊ አኗኗራቸው በለዘብተኛ ግራ ዘመሞች ስጋት ውስጥ እንዳለ ስለሚሰማቸው ነው።የአሜሪካ የሥልጣን ሰንሰለት እንዲስተካከል ሚፈልጉት ፓስተር ዲቨርስ

የሃይማኖት እና የፖለቲካ ግንኙነት

“ስለ ጉባኤው ምን ታስባለህ?” ሲሉ ዲቨርስ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቤን ለማወቅ የመጀመሪያውን ሙከራ አደረጉ።

ከረዥም ውይይት በኋላ የፖለቲካ አጀንዳቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ፅንስ ማቋረጥን ለማስቆም፣ የወሲብ ፊልሞችን ለማስወገድ እና የገቢ እና የንብረት ግብር መሰብሰብን ለማስቀረት እንደሚጥሩ ተናገሩ።

ዲቨርስ የረዥም ጊዜ ምኞታቸው ዩናይትድ ስቴትስን ወደ ክርስቲያን አገርነት መቀየር ነው።

ህልማቸውን ለማሳካት ወሳኙ ስትራቴጂ ደግሞ እስከ ላይኛው የመንግሥት እርከኖች ያሉ የፖለቲካ ሥልጣኖችን መያዝ ነው።

“ዋይት ሐውስን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መቀየር ይፈልጋሉ?” የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው “በምድር ላይ ያለ ነገር በሙሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው” ሲልሉ መለሱ።

የሪፐብሊካን ፓርቲው ሴናተር አክለውም “የሥልጣን አወቃቀሮችን መለወጥ አለብን” ሲሉ አክለዋል።

ከሌሎች የባይብል ቤልት ፓስተሮች በተለየ መልኩ ዲቨርስ ሙሉ በሙሉ በትራምፕ እንደተወከሉ እንኳን አይሰማቸውም።

“ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲን ወደ ግራ እየሳበው ነው” ሲል ይሞግታሉ።

ከዴቨርስ ጋር አብረው የሚሠሩት የ37 ዓመቱ የአምስት ሴቶች ልጆች አባት አሮን ሆፍማን በኦክላሆማ ውስጥ የኒው ባፕቲስት ቤተክርስቲያን ፓስተር ለመሆን በዝግጅት ላይ ናቸው።

እሳቸው ደግሞ በቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል ያለውን መስመር ማደብዘዝ ምንም ትርጉም እንደሌለው ያምናሉ።

“ክርስትናን ከፖለቲካ የሚያላቅቅ ምንም ዓይነት መንገድ የለም። አሜሪካኖች ክርስቶስን ረስተዋል” በማለት ዓይናቸው በእንባ ተሞልቱ ተናገሩ። የቀድሞዋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ሱዚ ስቲፋንሰን

ሃይማኖታዊ ውሳኔዎች

ይህ የባህል ጦርነት በተራ ሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል? መልሱ አዎ የሚል ነው።

በዚህ ዓመት ብቻ ቢያንስ በሦስት የባይብል ቤልት ግዛቶች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

በልዊዛኒያ ግዛት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ሁሉም የመማሪያ ክፍሎች አሥርቱ ትዕዛዛትን ግድግዳዎቻቸው ላይ እንዲለጠፉ ታዘዋል።

የአላባማ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ በማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጡ ሽሎች “ጨቅላ ሕፃናት ናቸው” ሲል ወስኗል። ይህም አንዳንድ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ክሊኒኮች ለጊዜው እንዲዘጉ አድርጓል።

የኦክላሆማ የትምህርት ኃላፊ ሪያን ዋልተርስ በሰኔ ወር ባሳለፉት መመሪያ በግዛቲቱ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አስገዳጅ ይሁን ማለታቸው መነጋጋሪያ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን ሰፊ ውዝግብ ቀስቅሶባቸዋል።

ኦክላሆማ በአገሪቱ ከፍተኛ የመምህራን እጥረት ካለባቸው ግዛቶች አንዷ ስትሆን፣ መመሪያው የሃይማኖት ነፃነትን የሚጻረር ነው በሚሉ መምህራን ዘንድ በበጎ አልተወሰደም።

የ44 ዓመቷ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ እና የቀድሞዋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ሱዚ ስቴፋንሰን “ቤተ ክርስቲያንን ከመንግሥት መለየት አለብን” ትላለች።

በአውሮፓውያኑ ግንቦት 2023 የኦክላሆማ መምህራን ማኅበርን “የአሸባሪ ድርጅት” ብለው የጠሩትን የሪፐብሊካኑን ዋልተርን ወቅሳለች።

ተመራጩ ዋልተርስ ከቢቢሲ የቀረበላቸውን የቃለ መጠይቅ ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

በርካታ ወላጆችም በውሳኔው ተበሳጭተዋል። በዚህ ውስጥም የኦክላሆማ የገጠር ትምህርት ቤቶች ጥምረት መሥራች የሆኑት ኤሪካ ራይት ይገኙበታል።

“መጽሐፍ ቅዱስን ከመጫን ይልቅ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስላለው ድህነት ሊያሳስባቸው ይገባል” ብላለች።

ክርስቲያን የሆነችው እና ሪፐብሊካኗ የኦክላሆማ ነዋሪዋ ራይት በግዛቲቱ ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች በቂ ገንዘብ እንደማይመደብላቸው እና በገጠር ያሉ አንዳንድ ልጆች በቤት ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ እንደማያገኙም የቅሳለች።

ከኦክላሆማ ከተማ በስተደቡብ አቅጣጫ ወደሚገኘው ኖብል ሲኬድ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በመኪኖች በሚጎተቱ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ መመልከት የተለመደ ነው።

“መጽሐፍ ቅዱስን ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ እንኳ የለም” ብላለች። በኦክላሆማ ያለው ድህነት ከሕዝቡ 15 በመቶውን አዳርሷል። ይህ አሃዝ በአንዳንድ የግዛቲቱ ክፍሎች ከዚህም በላይ በጣም ከፍ ያለ ነው።

በርካታ መጽሐፎችን ያሳተሙት በኦክላሆማ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሙኤል ፔሪ የፖለቲካ እና የሃይማኖት መመሪያው ትልቅ አጀንዳ እንደሆነ ያምናሉ።

ይህ አጀንዳ በጽንፈኛ መሪዎች የሚራገብ እና የክርስቲያን ብሔርተኝነት መርሆዎችን የሚከተል ነው ብለው ያምናሉ። ይህ ርዕዮተ ዓለም በአሜሪካ ሲቪል ሕይወት እና በወግ አጥባቂው አንግሎ ፕሮቴስታንታዊ ባህል መካከል ያለውን ውህደት የሚያበረታታም ነው።

“የክርስቲያን ብሔርተኝነት መስፋፋት በአሜሪካ ዲሞክራሲ ላይ ስጋት ይፈጥራል” በማለትም ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ጠቁመዋል።ፓስተር ጃክሰን ላህሜየር

“ትራምፕ ከፈጣሪ የተላከ ነው”

በድሃ ማኅበረሰቦች ውስጥ ትናንሽ አብያተ ክርስቲያናትን በማቋቋም፣ በባይብል ቤልት ውስጥ ያሉ ፓስተሮች በአማኞች መካከል ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ብዙዎቹንም ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ ወግ አጥባቂ መስመር ይመራሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ትራምፕ ለዚህ ቡድን ምርጥ መዘወሪያ ሆነዋል።

የኦክላሆማው ፓስተር ጃክሰን ላህሜየር የትራምፕ ታማኝ ደጋፊ ናቸው።

“ፓስተርስ ፎር ትራምፕ” [ትራምፕን የሚደግፉ ፓስተሮች] የተሰኘው ቡድን መሥራች የሆኑት ላህሜየር “ይህችን አገር እንዲያስተዳድር ትራምፕ በእግዚአብሔር ተልኳል” ብለዋል።

ዓላማቸውም በሚቀጥለው ምርጫ ትራምፕን ለመደገፍ “የወንጌላዊውንን ድምጽ ማሰባሰብ” ነው።

በሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከግድያ ሙከራ መትረፋቸውን “መለኮታዊ ተአምር ነው” በማለት ላህሜየር ጠርተውታል።

የቀድሞ የሴኔት ዕጩ ተወዳዳሪ በስልክ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “አገራችን ለእርስ በርስ ጦርነት አንድ እርምጃ ቀርቷታል” ብለዋል።

የፕሮቴስታንት ፓስተሮቹ እና የፖለቲካ አክቲቪስቶቹ እንደ ክርስቲያን ብሔርተኛ ለመቆጠር ፈቃደኛ አልሆኑም።

“ይህ መገናኛ ብዙኃን እኛን ለዲሞክራሲ ስጋት አድርገው ለመሳል በላያችን ላይ የጫኑት ስም ብቻ ነው። እውነት ግን አይደለም” ብለዋል።ፓስተር ፖል ብሌየር

በኦክላሆማ ከተማ ዳርቻ በኤድመንድ የፌርቪው ባፕቲስት ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑት ፓስተር ፖል ብሌየርም ራሳቸውን በዚህ መንገድ አይገልጹም።

“እኔ ክርስቲያን ነኝ? አዎ። ብሔርተኛ ነኝ? አዎ” ሲሉ ተናግረዋል። “ይህ ማለት እነሱ እኔን ሊሰይሙኝ እንደሚፈልጉት ክርስቲያን ብሔርተኛ ነኝ ማለት አይደለም” ብለዋል።

“ክርስቲያን ብሔርተኛ መሆን ስድብ ሆኗል” ሲሉም ተናግረዋል።

ፓስተር እና የቀድሞው የኦክላሆማ ሴኔት ዕጩ ተወዳዳሪ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ በቺካጎ ቤርስ ፕሮፌሽናል የአሜሪካ እግር ኳስ ተጫዋች በመሆን ያሳለፉበትን ጊዜ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ማሳየት ጀመሩ።

ዛሬ ብሌየር የፕሮቴስታንት መሪዎች ሃይማኖታዊ አጀንዳቸውን በፖለቲካ ውስጥ ለማስተዋወቅ ትምህርት የሚያገኙበትን “ሊበርቲ ፓስተርስ” የተባሉትን ማሠልጠኛ ማዕከሎችን ይመራሉ።

በሥልጠና ማዕከላቱ ውስጥ ፓስተሮቹ በመንግሥት ውስጥ የክርስቲያን ተጽእኖ ወይም የዜጎች የነጻነት መከላከያን የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ይማራሉ።

“ሥልጠናው የተነደፈው ፓስተሮች ሁሉንም የሕይወት ዘርፎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ እንዲያስቡ ነው” ብለዋል።

ራሳቸውም “አርበኛ ፓስተሮች” ብለው የሚጠሩ እና በመላው አሜሪካ የተስፋፋው የፕሮቴስታንት መሪዎች ቡድን አካል ናቸው።

ልክ እንደ ብዙዎቹ ሁሉ ብሌየርም አሜሪካ በ1776 ወደ ተመሠረተችበት ጊዜ ዕሴቶች መመለስ አለባት ብለው ያስባሉ።

“ከታሪክ አንጻር ክርስቲያኖች ሁልጊዜም በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ” ብለዋል።

ብሌየር እንደሚሉት ከሆነ ትራምፕ የ2020 ምርጫ አሸናፊ ነበሩ። ጥር 2021 በካፒቶል ላይ በተፈጸመው ጥቃት በመሳተፋቸው የታሰሩ ሰዎችን ደግሞ “የፖለቲካ እስረኞች” እንደሆኑ ያምናሉ።

በዘንድሮው ምርጫም ትራምፕ (በባለፈው ምርጫ ኦክላሆማ ላይ 65 በመቶ ድምጽ በማግኘት) ለሁለተኛ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።

ይህ ደግሞ የባይብል ቤልት በሚባሉት የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ወግ አጥባቂ የፕሮቴስታንት የፖለቲካ መሪዎች የሚጋሩት ተስፋ ነው።

ትራምፕ እና ምክትላቸው የሆኑት ጄዲ ቫንስ ያንን የፖለቲካ ትግል የሚያካሂዱ ሰዎች ምልክት ሆነዋል።ምዕመናን በጸሎት ላይ

ትራምፕ እና ጽንስ ማቋረጥ

በሥልጣን ዘመናቸው ለሦስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመት መስጠታቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት በደጋፊዎቻቸው ከሚመሰገኑባቸው ጉዳዮች አንደኛው ነው።

ይህም ለብዙ አስርት ዓመታት በአገሪቱ ከፍተኛው የፍትህ አካል ውስጥ ወግ አጥባቂዎች ድምጽ እንዲኖራቸው አድርጓል።

ለዚህ ወግ አጥባቂ አብላጫ ድምጽ ምስጋና ይግባውና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በ2022 በአገሪቱ ውስጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ፅንስ የማቋረጥ መብትን ያረጋገጠውን ብይን በመሻር ውሳኔውን በእያንዳንዱ ግዛት እጅ እንዲወድቅ አድርጓል።

የባይብል ቤልት አካላት ሆኑት እንደ ኦክላሆማ እና አርካንሳስ ያሉ ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥ ላይ በጣም ገዳቢ ሕጎች አሏቸው። ጽንስ ማቋረጥ የሚቻለው የእናቲቱ ሕይወት አደጋ ላይ ከሆነ ብቻ ነው።

ተቺዎች ግን እናትየው ለእንደዚህ ዓይነቱ መስፈርት ብቁ መሆኗን በሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ ለሐኪሞች በጣም ከባድ ነው ይላሉ።

በዘንድሮው ምርጫ ፅንስ የማቋረጥ ጉዳይ አንዱ ትልቅ ጉዳይ ነው። በባይብል ቤልት ውስጥ ሚገኘው እጅግ በጣም ወግ አጥባቂ የሆነው የሪፐብሊካን ፓርቲ ክንፍ ፅንስ ማቋረጥ እንዲታገድ ይፈልጋል። ትራምፕ ወደ ሥልጣን ቢመለሱ ይህ እውን ሊሆን ይችል ይሆናል ብለውም ያስባሉ።የትራምፕ ደጋፊዎች መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው

ወንጌላዊያን በዋይት ሐውስ?

ትራምፕ በሥልጣን ዘመናቸው ፌይዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ ኢኒሺዬቲቭ የሚባል አዲስ የመንግሥት ቢሮ እንዲፈጠር ትዕዛዝ ሰትተዋል።

ሰነዱን ሲፈርሙም “እምነት ከመንግሥት የበለጠ ኃይል አለው። ከእግዚአብሔር የበለጠ ኃይል ያለው ደግሞ ምንም ነገር የለም” ብለዋል።

በ2020 ትራምፕ በምርጫ ሲሸነፉ “አርበኛ ፓስተሮች” ወይም “የማጋ [ሜክ አሜሪካ ግሬት አጌይን/አሜሪካንን እንደገና ታላቅ ማድረግ] ፓስተሮች” የሚባሉት የሃይማኖት መሪዎች የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑ እንደተሰረቀባቸው ለማወጅ ወጥተው ነበር።

በርካቶችም በኦክላሆማው ባለሃብት ክሌይ ክላርክ የተመሠረተውን የቀኝ ዘመም የሪአዌከን አሜሪካ ንቅናቄን ተቀላቅለዋል።

ንቅናቄው ዛሬ በወንጌላውያን፣ የጦር መሳሪያ መያዝን በሚደግፉ፣ ፀረ ስደተኛ፣ ፀረ ተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ፣ ፀረ ኮሚኒስት አክቲቪስቶች እና በትራምፕ ንግግር የተወከሉ ሰዎች ሚሳተፉበትን መረሃ ግብሮችን ማዘጋጀቱን ቀጥሏል።

ብዙዎችም ከግራ ዘመሞች ጋር መንፈሳዊ ጦርነትን የሚዋጉ የእግዚአብሔር ወታደሮች እንደሆኑ ይቆጥራሉ። ከእነዚህ ሐሳቦች መካከል አንዳንዶቹ በፕሮጀክት 25 ውስጥ ተካትተዋል።

ይህ ፕሮጀክት በቀድሞ የትራምፕ አማካሪዎች የፌዴራል መንግሥትን ለማሻሻል እና የአሜሪካን ዋና ዋና ጉዳዮችን በተመለከተ የቀረበ አወዛጋቢ ሀሳብ ነው።

ትራምፕ ራሳቸውን ከፕሮጀክቱ አግልለዋል። በርካቶች ግን ከውጥኑ በስተጀርባ ያሉት ተፅዕኖ ፈጣሪ ወግ አጥባቂ እና ሃይማኖታዊ ቡድኖች ሪፐብሊካኖች ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ አጀንዳውን በትራምፕ ላይ ለመጫን እንደሚሞክሩ ያምናሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)