በሱዳን አንድ አውሮፕላን ተመትቶ መውደቁን ተከትሎ ሩሲያውያን ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ

በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር አካባቢ አንድ ንብረትነቱ የሩሲያ እንደሆን የሚገመት ዕቃ ጫኝ አንቶኖቭ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተመትቶ መውደቁን ተከትሎ የሩሲያ ዜጎች ጭምር ሳይገደሉ እንዳልቀረ ተነግሯል።

የሱዳን ሁለቱ ተፋላሚዎች በስፋት በዋጉበት የዳርፉር ቀጠና አንድ የሩሲያ የበረራ አባላትን የያዘ አውሮፕላን ተመትቶ ወድቋል መባሉን እያጣራ መሆኑን በሱዳን የሩሲያ ኢምባሲ አስታውቋል። የወታደራዊ ምንጮች ለሱዳን መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ከሆነ ኢልዩሽን 2-76 የተሰኘው ሩሲያ ስሪት አውሮፕላን የሱዳን መከላከያ ወደ ተቆጣጠራት ኤል-ፋሸር ከተማ መድሃኒት እና መሣሪያ ለማድረስ እየተጓዘ ሳለ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመበት።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሰጠው ማብራሪያ “ንጹሃንን ለመጨፍጨፍ ተልዕኮ ይዞ በግብጽ ወታደሮች የሚበር ሩሲያ ሰራሽ የጦር አውሮፕላንን መትተን ጥለናል” ብሏል። ነገር ግን ተመትቶ የወደቀው አውሮፕላን ለውጊያ የሚያገለግል ሳይሆን እቃ ጫኝ አውሮፕላን መሆኑ ተረጋግጧል።

18 ወራትን በዘለቀው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ግብጽ ለሱዳን ጦር መሣሪያ እንደማታቀርብ አስተባብላለች። በስልጣን ፍትጊያ ምክንያት በፈረንጆቹ 2023 ሚያዚያ ወር ላይ የተጀመረው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት በዓለም አስከፊውን የሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። በጥናት የተደገፉ ግምቶች እንደሚያሳዩት በዚህ ጦርነት ቢያንስ እስከ 150 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ከአጠቃላይ 50 ሚሊዮን የሱዳን ሕዝብ መካከል ቢያንስ 10 ሚሊዮን የሚሆኑት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

በሱዳን የሚገኘው የሩሲያ ኢምባሲ የአውሮፕላኑን ተመትቶ መከስከስ ተከትሎ ጉዳዩን ለማጣራት እና የበረራ አባላት የነበሩትን ሩሲያውያን ማንነት ለመለየት ከሱዳን ወታደር ጋር ተባብሮ እየሠራ መሆኑን ገልጿል። የሱዳን ትሪቢውን ድረገጽ ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ በበረራው የነበሩት ሦስት ሱዳናውያን እና ሁለት ሩሲያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው በቻድ ድንበር አካባቢ ማልሃ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መሆኑን የወታደራዊ ምንጮችን ድረ ገጹ ጠቅሶ ዘግቧል። በምዕራብ ዳርፉር ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል የወታደራዊ ኃይሉ የተቆጣጠራት ብቸኛ ከተማ ኤል ፋሽር ስትሆን ከባለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃት እየተፈጸመባት ይገኛል። የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አውሮፕላኑን መትቶ ከጣለ በኋላ የአውሮፕላኑን ጥቁር ሳጥን መያዙን እና አውሮፕላኑ ለምን ተልዕኮ ወደስፍራው እንዳመራ የሚያስረዳ ማስረጃ ማግኘቱን ገልጿል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወር ቪዲዮ እንደሚያሳየው አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ የፈጥኖ ደራሹ ኃይሉ ወታደሮች ተሰባስበው ሰነዶችን ሲመለከቱ ይስተዋላል። ቢቢሲ እንዳረጋገጠው ደግሞ የአንድን ግለሰብ ማስረጃ የሚያሳዩ የሩሲያ ፓስፖርት፣ ደቡብ አፍሪካ የተገኘ የመንጃ ፈቃድ እና የሥራ መታወቂያዎችን መመልከት ችሏል። የመጀመሪያ ጥናት እንደሚያሳየው የሰነዶቹ ባለቤት ምናልባትም በሩሲያ የጦር አካዳሚ ተምሮ መኖሪያውን ግን ደቡብ አፍሪካ ያደረገ ሳይሆን አይቀርም።

አንደኛው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊ 50 የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ [ረብል] ይዞ ይታያል። በርግጥ ቦታው አውሮፕላኑ ከተከሰከሰበት ቦታ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አልተቻለም።

አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት ደግሞ የአደጋው መንስኤ ምናልባትም የቴክኒክ ብልሽት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የፈጥኖ ደራሹም ሆነ የሱዳን ሠራዊት አውሮፕላኑ የወደቀው ተመትቶ መሆኑን ገልጸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ አውሮፕላኑ በስህተት ዒላማ ተደርጎ ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ ያነሳሉ።

ይህንን የሚሉ ሰዎች ምክንያታቸው ተመትቶ ወደቀ የተባለው አውሮፕላን ባለቤት ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር ወዳጅነት እንዳለው የሚያመላክቱ መረጃዎች ተገኝተዋል በማለት ነው። በርግጥ የመካከለኛው ምስራቅ አገሯ ኤምሬትስ፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከማስታጠቅ ጋር የሚነሳባትን ክስ አስተባብላለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኤምሬትስ እንደሚደገፍ ተጨባጭ መረጃ ማግኘቱን ገልጿል።

በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ግጭት ለማቆም የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። አብዛኛው ክፍሏ በፈጥኖ ደራሹ በተያዘችው መዲናዋ ሱዳን ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገ ሲሆን፣ ሠራዊቱ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላይ ሰፊ የአየር ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል።

በዋድ ማዳኒ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በተቆጣጠራት ገዚራ ግዛት ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ ከ50 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን የአካባቢው የማሕበረሰብ ተቆርቋሪዎች ገልጸዋል።

እርዳታ ለማድረስ ወደ አንድ መስጂድ የሄዱ ሰዎች ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ቢያንስ 30 የእርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል ብለዋል። ጥቃቱ ከፍተኛ በመሆኑም ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የተጎጅዎች ማንነት መለየት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)