ለዘጠኝ ዓመታት በሐሰተኛ ማንነት በኢንተርኔት የተታለለችው አፍቃሪ

ሁሉ ነገር የተጀመረው በፌስቡክ ጓደኛ እንሁን በሚል ጥያቄ ነበር።

ለለንደን ነዋሪዋ ኪራት አሲ የልብ ሐኪሙ እና መልከ መልካሙ ቦቢ ያቀረበላት ጓደኛ እንሁን ጥያቄ ለየት ያለ ነበር።

ወዲያውኑም ነበር ማውራት የጀመሩት።

ቦቢ እንግዳ ሰው አልነበረም።

ሁለቱም በምዕራብ ለንደን የሲክ እምነት ተከታይ የሆኑት ማኅበረሰብ አባላት ናቸው።

በፌስቡክ ላይም የጋራ ጓደኞች ነበራቸው።

ይህንን የተመለከተችው ኪራት የቦቢን የፌስቡክ ጓደኝነት ጥያቄ በደስታ ተቀበለች።

ጓደኝነታቸውም የልብ የልባቸውን ከማውራት አልፎ ወደ ፍቅር ግንኙነት አደገ።

የሁለቱም ግንኙነት ተጠናክሮ ለመጋባት ቢያቅዱም ለዓመታት በኢንተርኔት ላይ ከማውራት ውጪ በአካል ተገናኝተው አያውቁም።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቦቢ ላለመገናኘት የሚሰጣቸው አስገራሚ እና ወጣ ያሉ ሰበቦች ነበሩ።

በአንድ ወቅት በጭንቅላት ደም መፍሰስ፣ በስትሮክ ተመትቻለሁ አለ።

ሌላ ጊዜ በተተኮሰበት ጥይት ቆሰለ። በሌላ ወቅት ደግሞ ለምስክሮች በሚሰጥ የጥበቃ ፕሮግራም ውስጥ ተካትቻለሁ አለ።

እነዚህን ምክንያቶች ብቻ ደግሞ እሱ ብቻ ሳይሆን የቦቢ ቅርብ ዘመዶችም በፌስቡክ መልዕክቶች ይህንኑ ይደግሙላታል።

በየቀኑ፣ ሌሊቱን ሙሉ ያወራሉ።

ቦቢ ጋር በአካል ባይገናኙም ስጦታዎችን ይልክላታል።

አፈቅርሻለሁ፣ እወድሻለሁ የሚሉ ቃላትን ያዥጎደጉድላታል። የታገቢኛለሽ ጥያቄውም የቀረበው በኢንተርኔት ነው።

እሱ ደስ የማይለውን ነገር ማድረግ ስለማትፈልግ የአንድ ሬድዮ ፕሮግራም አቅራቢነቷን አቁማለች።

ኪራት የወደፊት ሕይወቷን ከዚህ ሰው ጋር እየገነባች ነበር። ስለ ወደፊቱ ቤታቸው፣ ስለ ልጆች ያወራሉ።

ቤተሰቦቿም ስለወደፊት አጋሯ ሰሙ።

ከጥሩ ቤተሰብ ስለሆነ በበጎ ነው ያዪት።

ዛሬ፣ ነገ፣ በሰበብ ላይ ሰበብ እየጨመረ ሳያያት ዘጠኝ ዓመታት ተቆጠሩ።

ነገሩ ግራ የገባት ኪራት “ላይህ እፈልጋለሁ” ብላ ቆረጠች።

እሱም ተስማማ። ሆኖም መጨረሻ ላይ ሃሳቡን ቀየረ።

ብዙ ያየችበትን ‘ፍቅረኛዋን’ ለማየት የቆረጠችው ኪራት አፈላልጋ ወደ ቤቱ ሄደች።

ፊት ለፊት ያገኘችው እውነተኛው ቦቢ የኪራትን ማንነት አላወቀም፤ የምትለውም ነገር ግራ ነው የሆነበት።

ኪራት ለዓመታት ፍቅረኛዬ እያለች ስታዋራው የነበረው ሰው ቦቢ አልነበረም።

በጣም አስደንጋጭ እና ባልተጠበቀ ማጭበርበር የእሱን ማንነት በፌስቡክ ወስዳ ስታዋራት የነበረው የአጎቷ ልጅ ሲምራን ነበረች።

ቦቢ ኪራትን በድምጽ ሲያዋራት የቆየ ሲሆን፣ ለዚህም የአጎቷ ልጅ አንድ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) ትጠቀም ነበር።

ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቦቢን ሆና እንዲሁም የቦቢን ዘመዶችን ማንነት በፌስቡክ ፈጥራ ስታዋራት እና ከሁሉም ነገር ጀርባ ሆና ስታጭበረራት የነበረችው የአጎቷ ልጅ ሲምራን መሆኗ ያልተጠበቀ ድንገተኛ ክስተት ነበር።

ሲምራን የቦቢን፣ የወንድሙን፣ የአጎቶቹን ልጆች፣ የዘመዶቹን ፌስቡክ አካውንት እንደ አዲስ ፈጥራ ስትቆጣጠር እና ኪራትን ስታዋራት ነበር።

ኪራት ነገሩን መለስ ብላ አሁን ስታዬው “ምን ያህል ታውሬ ነበር?” ስትል ትጠይቃለች።

የኪራት አስደንጋጭ ታሪክ ቶርቶይስ በተሰኘው የፖድካስት ፕሮግራም ከሦስት ዓመት በፊት ቀርቦ ከፍተኛ ተደማጭነትን አግኝቷል።

በቅርቡ ደግሞ ኔትፍሊክስ ይህንን አስገራሚ ማታለል እና ምክንያት አልባ የጭካኔ ታሪክ ‘ስዊት ቦቢ፡ ማይ ካት ፊሽ ናይትሜር’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም አድርጎ አቅርቦታል።

ታሪኳን መናገሯ “እንዴት አንድ ሰው በዚህ ሊታለል ይችላል?” ብለው እንዲጠይቁ ሰዎች እንዳነሳሳቸው ትናገራለች።

በበጎ የሚያዩት እንዳሉ አንዳንዶችም እንደ ነፈዝ የተመለከቷት አልታጡም።

“አሁንም ደደብ ናት ለሚሉ ሰዎች ምንም ማለት አይደለም። ይህ የእነሱ አስተያየት ነው” በማለት ኪራት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ነገር ግን ኪራት የራሳቸውን ፍርጃ መስጠት እንደሌለባቸው እና ታሪኳንም ለመንገር አንደኛው ምክንያቷ ይሄ ነው ትላለች።

“ደደብ አይደለሁም። ጅል አይደለሁም። ታሪኬን ለመንገር የመረጥኩት እኔ ነኝ” ትላለች።

እንደዚህ ዓይነት ማጭበርበሮች እና ማታለሎች የተፈጸመባቸውም ታሪካቸውን እንደሚናገሩ ተስፋ አድርጋለች።

ታሪኳን ለሰሙ እና ፊልሙን ላዩ ሰዎች ሌላ የሚያነሱት ጥያቄ በዚህ መንገድ የተታለለች ሴት ራሷን ለሕዝብ ዕይታ እንዴት አጋለጠች የሚለው ነው።ትክክለኛው ቦቢ

‘በማኅበረሰባችን ኃላፊነት ተጭኖብናል’

ከሕንዷ ፑንጃቢ ግዛት ከመጡ ቤተሰቦች የተወለደችው ኪራት ታሪኳን በይፋ መናገሯ በደቡብ እስያ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደ ነውር የሚታዩ ነገሮችን ለማውጣት ስለፈለገች እንደሆነ ገልጻለች።

“እንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮችን አውጥተን ለመናገር በጣም እንፈራለን” ትላለች ኪራት።

በዚህም ምክንያት እንዲህ ዓይነት ማጭበርበሮች ሰለባ የሆኑ ሰዎች ብቻቸውን ይሰቃያሉ።

ለዚህም ማሳያ አንደኛው አባቷ ናቸው። በኪራት ላይ የደረሰባትን ማታለል በጭራሽ ማወቅ እንደማይፈልጉ ታስረዳለች።

“ምክንያቱም የተከሰተውን ነገር ለማወቅ እና ምን ያህል አሰቃቂ እንደነበር መጋፈጥ ህመም ነው” ትላለች።

“አባቴን እወደዋለሁ፣ እሱም እንደሚወደኝ አውቃለሁ። ነገር ግን ያደገበት ማኅበረሰብ እሴት ከእኔ ይለያል” ስትል ትገልጻለች።

ኪራት ስለተፈጠረው ነገር ከ‘እውነተኛው ቦቢ’ ጋር በቀጥታ እንዳልተነጋገሩ ገልጻ እናም ይህም ማኅበረሰቡ አስቸጋሪ የሚባሉ ውይይቶችን ለማድረግ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆንበት ማሳያ ነው ትላለች።

ምናልባት ከሌላ ባህል ብትመጣ ልምዷ ተመሳሳይ ይሆን ነበር ብላ ታስባለች።

ምላሿም “የተለዩ ውሳኔዎችን እወስናለሁ” የሚል ነው።

“ምክንያቱም በማኅበረሰባችን ኃላፊነት ተጭኖብናል። ከፍተኛ የቤተሰብ ጫናም ሌላኛው ነው” ትላለች።

‘ራሴን እንደ ሰለባ ብቻ አላይም’

ስዊት ቦቢ በኔትፍሊክስ መውጣቱን ተከትሎ አንዳንድ አሉታዊ አስተያየቶችን ብታስተናግድም ኪራት አሁንም እውነታውን ለመጋፈጥ ቆርጣለች። “ካያችሁኝ ለመቅረብ እና ለማናገር አትፍሩኝ” ስትል ኪራት ታስረዳለች።

“ለእኔ አወዛጋቢ ሊሆን የሚችል ነገር መናገር ከፈለጋችሁ ችግር የለውም እሰማለሁ። እንወያይበት” ትላለች ኪራት።

ታሪኳ በፖድካስት መውጣቱ ወይም በዘጋቢ ፊልም መታየቱ የተወሰነ እፎይታ ፈጥሮላት እንደሆነ በቢቢሲ የተጠየቀችው ኪራት እርግጠኛ እንዳልሆነች ተናግራለች።

ይህንን ሁሉ ማታለል ለዓመታት የፈጸመችው የአጎቷ ልጅ ሲምራን በዘጋቢ ፊልም ላይ አልሳተፍም በማለት ውድቅ በማድረጓ በአንዲት ተዋናይት ተወክላለች።

ኪራት በአጎቷ ልጅ ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ መሥርታ በፍርድ ቤት ረትታለች። የአጎቷ ልጅ ካሳ ከፍላታለች እንዲሁም በመጨረሻም ይቅርታ ጠይቃታለች።

ሆኖም በፊልሙ ላይ በተካተተው የሲምራን መግለጫ “ይህንን ጉዳይ የፈጸምኩት በትምህርት ቤት በልጅነት ጊዜ ባጋጠሙኝ ክስተቶች ምክንያት ነው። ይህ የግል ጉዳይ ነው እና መሠረተ ቢስ እና ጎጂ ውንጀላዎችን አካቷል” ስትል ተቃውወማለች።

ሲምራን ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ እንዳልቀረበባት የምትናገረው ኪራት ተጠያቂ እንድትሆንም ትፈልጋለች።

“ይህች ሰው በዚህ መንገድ እንዲህ መንቀሳቀሷ ሰላም አይሰጠኝም” ብላለች።

የአጎቷ ልጅ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ እና ተንኮል የተሞላበት ድርጊት ለምን እንደፈጸመችባት አሁንም አታውቅም።

ለምን? ለሚለው ምላሽ የላትም።

“በዚህ መንገድ እንዲህ ዓይነት ጥግ የሄደችበት ሁኔታ በፍጹም ምክንያት ሊፈለግለት አይገባም” ትላለች።

“ለምን እንዳላቆመች፣ በሰው ህመም መደሰት የሚገባኝ ነገር አይደለም” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

ምንም እንኳን ለምን ለሚለው ምላሽ ባታገኝም ሕይወቷን ከመቀጠል አልገታትም። እንደገና ከአንድ ሰው ጋርም የፍቅር ግንኙነት ጀምራለች።

“ሕይወቴን እንደገና ለመገንባት ጠንክሬ እየሠራሁ ነው። ሰለባ ነኝ ብዬ ብቻ አላስብም። የሕይወቴን ግቦች እና ህልሞች ለማሳካት መሥራቴን እቀጥላለሁ” ብላለች

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)