እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በስብሰባ ላይ የነበሩ ከንቲባን ገደለች

እስራኤል ናቢቲያህ በተባለችው የሊባኖስ ከተማ ላይ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በእርዳታ አቅርቦት ላይ እየተወያዩ የነበሩትን ከንቲባ እና ሌሎች የከተማዋ ሠራተኞችን መግደሏን የግዛቲቱ አስተዳዳሪ አስታወቁ።

አስተዳዳሪዋ ሆዋይዳ ተርክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዛሬ [ረቡዕ] በተፈጸመው የእስራኤል ጥቃት በአካባቢው በተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ ላይ በመምከር ለነዋሪዎች እርዳታ ማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ስብሰባ ላይ የነበሩት ከንቲባው እና ረዳቶቻቸው ተገድለዋል።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ግን በናቢቲያህ የተፈጸመው የአየር ጥቃት ዒላማ ያደረገው “በርካታ የሄዝቦላህ ሽብርተኞችን ነው” በማለት ገልጿል።

ከንቲባው አሕመድ ካሂል በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የእስራኤልን ጥቃት በመሸሽ ለቀው ሲሄዱ እዚያው የቀሩትን ነዋሪዎች ለመርዳት ከሌሎች የማዘጋጃ ቤታቸው ሠራተኞች ጋር ስብሰባ እያደረጉ ነበር ተብሏል።

በጥቃቱ ከከንቲባው በተጨማሪ ሌሎች ስድስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በተፈጠረው ፍርስራሽ ስር ፍለጋ እየተካሄደ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል የአካባቢው አስተዳዳሪ ገልጸዋል።

በጥቃቱ የተቆጡት አስተዳዳሪዋ እስራኤል እያካሄደች ያለው የአየር ድብደባ ሙሉዋን ሊባኖስ በደፈናው ዒላማ ያደረገ መሆኑን “ሰላማዊ ሰዎች፣ ቀይ መስቀል፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሁሉም ተመትተዋል። አሁን ደግሞ የመንግሥት ሕንጻዎችን ዒላማ አድርገዋል። ይህ ተቀባይነት የሌለው ጭፍጨፋ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ቀደም ባሉት ቀናት እስራኤል ናቢቲያህ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በኦቶማን ዘመን የገበያ ቦታ የነበረን ስፍራ እንዲሁም ታሪካዊ ሕንጻዎች ወድመዋል።

ለሳምንታት የዘለቀው የአስራኤል የአየር ጥቃት አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ ዛሬ በደቡባዊ ቤይሩት ዳርቻ ላይ በተፈጸመ ድብደባ ሄዝቦላህ ይጠቀምባቸዋል ያለቻቸውን የመሬት በታች የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን ዒላማ ማድረጓን አስታውቃለች።

የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር በናቢቲያህ ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና 43 ሰዎች መቁሰላቸውን እረጋግጧል።

የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ እስራኤል “ሆን ብላ የማዘጋጃ ቤት ባለሥልጣናት እና ሠራተኞች ስብሰባን ዒላማ አድርጋለች” በማለት ድርጊቱን አውግዘዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግሥት የእስራኤልን ጥቃት የሚያስቆም የተኩስ አቁም እንዲያውጅ ጠይቀዋል።

“የዓለም አገራት በሊባኖስ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ግልጽ ወረራ ማስቆም ካልቻሉ፣ ሰላም አስከባሪዎችን ጭምር ዒላማ ያደረገውን ጠላት ከወንጀሉ ማን ሊያስቆመው ይችላል? ምንስ ተስፋ አለ?” ሲሉ የዓለምን ማኅበረሰብ ጠይቀዋል።

እስራኤል ከሦስት ሳምንታት በፊት በሊባኖስ ላይ ማካሄድ የጀመረችው የአየር ጥቃት እና የእግረኛ ጦር ወረራ እንደቀጠለ ሲሆን፣ እስካሁን ከ1500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)