በሕንድ በሐሰተኛ ቦምብ ጥቃት ዛቻ በረራዎች ለመዘግየት እና አቅጣጫቸውን ለመቀየር ተገደዱ

ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 10 የሕንድ አውሮፕላኖች ላይ ሐሰተኛ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ በመሰንዘሩ ምክንያት በርካታ በረራዎች ለረጅም ሰዓታት እንዲዘገዩ እና አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ተገደዱ።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ትናንት ማክሰኞ የቦምብ ጥቃት እንደሚፈጸምበት የተነገረው የኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ አውሮፕላን አየር ላይ እንዳለ ፍንዳታ ቢያጋጥመው በሚል ሕዝብ ከሚበዛባቸው አካባቢዎች እንዲርቅ በሁለት የሲንጋፖር አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች ታጅቦ እንዲያርፍ ተደርጓል።

ከዚህ ክስተት ከሰዓታት በፊት ደግሞ ከዋና ከተማዋ ዴልሂ ወደ አሜሪካ ቺካጎ ይጓዝ የነበረ የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል በካናዳ እንዲያርፍ ተደርጓል።

በሕንድ አየር መንገዶች ላይ የሚሰነዘር ሐሰተኛ የቦምብ ጥቃት ዛቻ ያልተለመደ ነገር አይደለም፤ ነገር ግን ከሰኞ ጀምሮ አሁን በድንገተኛ ሁኔታ የጨመረውን የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም።

ቢቢሲ ከሕንድ ሲቪል አቪዬሽን እና የአየር ትራንስፖርት ደኅንነት ባለሥልጣናት ማብራሪያ ለማግኘት በኢሜይል ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኝም።

ይህ የጥቃት ማስፈራሪያው በአንድ አየር መንገድ ላይ ብቻ የተሰነዘረ አይደለም። ኤር ኢንዲያ፣ ኢንዲጎ፣ ስፓይስጄት እና ኤር ፍላይትስ የተባሉት አየር መንገዶች የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደርሷቸዋል።

ሰኞ ዕለት ከሙምባይ የተነሱ ሦስት ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ የቦምብ ጥቃት ዛቻ በኤክስ (ትዊተር) ላይ ከተሰነዘረ በኋላ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ተደርጓል። ከዚህ መልዕክት ጋር በተያያዘ ፖሊስ አንድ ታዳጊን በቁጥጥር ስር አውሏል።

አሁን አገልግሎት እንዳይሰጥ በተደረገ በሌላ የኤክስ ገጽ አማካኝነት በተሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች ምክንያት ማክሰኞ ሁለት የኤር ኢንዲያ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሰባት በረራዎች ችግር ገጥሟቸው ነበር። ማስፈራሪያዎቹ ላይ የአየር መንገዱ፣ የአካባቢ ፖሊስ እና የበረራ ቁጥሩ መጠቀሱን መልዕክቱን በፎቶ ያስቀሩ ሰዎች ተናግረዋል።

ኤር ኢንዲያ ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ከተሰነዘሩት ዛቻዎች ጀርባ ያሉትን ሰዎች ለመለየት ከባለሥልጣናት ጋር በመተባበር የደረሰውን መስተጓጎል ለማስተካከል እና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።

በሕንድ ውስጥ ያሉ እያንዳንዱ አውሮፕላን ማረፊያ የቦምብ ስጋትን የሚከታተል እና የአደጋውን ክብደት በመገምገም እርምጃ የሚወስድ ኮሚቴ አለው። የተሰነዘረው የጥቃት ዛቻን መሠረት በማድረግም የቦምብ አስወጋጅ ቡድን፣ አነፍናፊ ውሾች፣ አምቡላንስ፣ ፖሊስ እና ዶክተሮች እንዲሳተፉ ሊደረግ ይችላል።

በተጨማሪም መንገደኞች እና የበረራ ሠራተኞች ከነ ሻንጣቸው ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ተደርገው በድጋሚ ፍተሻ ይደረግባቸዋል። የበረራ ኢንጂነሪንግ እና ደኅንነት ቡድኖችም አውሮፕላኑን እንደገና እንዲበር ከመፈቀዱ በፊት ፍተሻ ያደርጋሉ።

በዚህም ምክንያት በሚከሰተው መዘግየት አየር መንገዶችን እና የደኅንነት ተቋማትን በሺዎች የሚቆጠር ዶላር እንዲከስሩ ያደርጋቸዋል።

ወደ ሌሎች አገራት የሚጓዙ በረራዎችን በተመለከተም አሁን በሴንጋፓር እና በካናዳ እንደሆነው ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሳተፉ የሚያስገድድ ሁኔታ ይከሰታል።

የሲንጋፖር የመከላከያ ሚኒስትር ማክሰኞ እንዳሉት ሁለቱ የአገሪቱ ተዋጊ ጄቶች ኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ አይሮፕላን በሰላም ቻንጊ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ከማረፉ በፊት “በጥድፊያ አጅበውታል” ብለዋል። አውሮፕላኑ ከሕንድ ማዱራይ ወደ ሲንጋፖር እየተጓዘ ነበር።

አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ኃላፊነቱን ፖሊስ ተረክቦ ምርመራው በመካሄድ ላይ መሆኑ ተነግሯል።

ሌላኛው በካናዳ በኩል ወደ ቺካጎ እየተጓዘ የነበረው እና የቦምብ ጥቃት ዛቻ የተሰነዘረበት የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን ለጥንቃቄ ሲባል ኢኳሉዊት በተባለ አየር ማረፊያ እንዲያርፍ ተደርጎ የካናዳ ፖሊስ ምርመራ እያደረገበት ነው።

ኤር ኢንዲያ ዛሬ ረቡዕ እንዳለው መንገደኞቹ በካናዳ አየር ኃይል አውሮፕላን ወደ ቺካጎ ይወሳዳሉ። ነገር ግን የቦምብ ጥቃት ዛቻ የተሰነዘረበት አውሮፕላን መቼ ጉዞውን እንደሚያደርግ የታወቀ ነገር የለም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)