ሕይወት ሁሉም አባላቱ ዓይነ ስውር ወይም የዕይታ ችግር ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ

በምሥራቃዊ ኡጋንዳ የሚኖረው የ53 ዓመቱ ሞሰስ ሙጋቤ የዓይን ብርሃኑን ምን አንደጋረደው አያውቅም፤ ነገር ግን ለልቡም ለነፍሱም ቅርብ የሆነው ትዝታ ለመጨረሻ ጊዜ ያያት የማለዳ የፀሐይ ብርሃንን አይረሳትም።

“የዓይን ብርሃን ሙሉ በሙሉ እስከ ወዲያኛው ማጣቴን፣ ዳግም ማየት አለመቻሌን፣ ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ እጅጉን የከፋ ሕይወት እየመራሁ እገኛለሁ።”

በዓለም አቀፉ ዓይነ ስውርነት መከላከል ኤጀንሲ መረጃ መሠረት ሞሰስ ከሦስት ሚሊዮን በላይ መሆናቸው ከሚገመቱት ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል ማየት ከማይችሉ ኡጋንዳውያን መካከል አንዱ ነው።

በአፍሪካ የዓይን ብርሃናቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ 100 ሚሊዮን ዜጎች እንደሚኖሩ ይገመታል።

ምንም እንኳ በርካታ ኡጋንዳውያን በአቅራቢያቸው የሕክምና ተቋማት የሚያገኙ ቢሆንም በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ግን በቂ የሆነ የዓይን ሕክምና ለማግኘት ይቸገራሉ።

አገሪቱ በጣት የሚቆጠሩ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ነው ያሏት።

ሕክምና በሌለበት እንደ ሞሰስ ያሉ ዜጎች ከዓይን ብርሃናቸው ውጪ ለመኖር በፈጠራ የታገዘ ድጋፍ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ሞሰስ ከትዳር አጋሩ እና ከሦስት ልጆቹ ጋር በቪክቶሪያ ሐይቅ ሰሜናዊ ጫፍ በሉቡ መንደር ይኖራል።

ሞሰስ እኤአ በ2000 ለዓይነ ስውራን በተቋቋመ ትምህርት ቤት “ሉቡ የዓይነ ስውራን ቡድን” የተባለ ማኅበረሰብ ያስተባብራል።

ይህ ማኅበረሰብ 25 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሁሉም በተለያየ ደረጃ ዕይታቸውን ያጡ ናቸው።

ማኅበረሰቡ 10 ቤቶች ባሉት እንዲሁም ሁለት የጋራ መጸዳጃ ቤቶች በተሟሉለት ግቢ ውስጥ ይኖራል።

በየሳምንቱ ሰኞ ቅርንጫፎቹ ለበርካቶች ጥላ በሆነው ዛፍ ስር ተሰብሰብበው ጉዳያቸውን ይወያያሉ።

ስብሰባውን በሚያካሄዱበት ወቅት፣ ሞሰስ በሌሎች አባላት “ሊቀመንበር” እየተባለ ይጠራል።

ከቡድኑ አባላት መካከል አንዱ “ለመስማት ለምንቸገር ሰዎች የመስማት አቅማችንን የሚደግፍ መሳሪያ እንዲመጣልን ጠይቀናል” አለ።

ሌላ ሰው ደግሞ የልጆቻቸው ትምህርት ቤት ክፍያ በመጨመሩ የገባቸውን ስጋት ገለፁ።

ሞሰስ ለቀረቡ ጥያቄዎች እና ስጋቶች ፈርጠም ባለ ነገር ግን መግባባት በተጫነው ድምጽ ምላሽ ሰጠ።

“የአካል ጉዳተኞች ስለሆንን ሌሎች መብታችንን እንዲጋፉ አትፍቀዱ። እንናገራለን፤ ሁሉም ያለንን ዋጋ ማወቅ አለበት” ሲል ምላሽ ሰጠ።

ሞሰስ ለቢቢሲ ይህ ሳምንታዊ ስብሰባ ጠቃሚ ጎን እንዳለው ይናገራል።

“ራሳችንን እንዲሁም ልጆቻችንን በትምህርታቸው እንዴት መደገፍ እንዳለብን እንነጋገራለን። ልጆቻችንን እንዴት መመገብ፣ እንዴት ማልበስ እንዳለብን፣ እንዴት ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንደምንችል እንነጋገራለን።”

ዓይነ ስውርነት በኡጋንዳ

የሉቡ ነዋሪዎች በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የዓይን ብርሃናቸውን ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል አጥተዋል።

የዓይን ብርሃናቸውን ያጡት በአንኮሴርካ (የአንኮ በሽታ)፣ በስኳር ህመም፣ ካታራክት፣ ትራኮማ፣ በኩፍኝ ሊሆን ይችላል።

ሞሰስ እና በርካቶች ግን የዓይን ብርሃናቸውን ያጡበትን ምክንያት በአግባቡ በሕክምና ባለሙያ አልተመረመሩም።

ኤአአ በ1990 እና 2000 በምሥራቃዊ ማዩጌ የኦንኮ በሽታ (ሪቨር ብላይንድነስ) ተስፋፍቶ ነበር።

በሽታው የሚስፋፋው ጥገኛ ህዋሳቱን (ፓራሳይት) በያዘ ትል አማካኝነት ሲሆን፣ ወደ ሰው የሚዛመተው ደግሞ በፓራሳይቱ በተጠቁ ዝንቦች ንክሻ አማካኝነት ነው።

የኦንኮሰሪኪያሲስ በሽታ በቆዳ ማሳከክ እና የዓይን ብርሃንን በመቀነስ የሚታወቅ ሲሆን፣ የሚተላለፈውም በጥቁር ዝንብ አማካኝነት ነው።

እንደ ሉቡ ያሉ የሐይቅ ዳርቻ አሰፋፈሮች ደግሞ በተለየ ይጠቃሉ።

ይኹን እንጂ እኤአ በ2017 በርካታ የማኅበረሰብ ጤና ፕሮጀክቶች የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ብሎም ለማጥፋት ከተሠሩ በኋላ የኦንኮ በሽታ ከማዩጋ መጥፋቱ ተነግሯል።

ምንም እንኳ በሽታው ቢጠፋም የሉቡ “የዓይነ ስውራን መንደር” ግን ለህመሙ ሕያው ምስክር ሆኖ ቀርቷል።

“በምሽግ ውስጥ እንዳለ ወታደር ለመንቀሳቀስ እንዲያመቸን በሚል በጋራ አንኖራለን፤ ስለዚህ ምንም ነገር ቢፈጠር ለእኛ ለማስተባበር ቀላል ይሆንልናል” ይላል ሞሰስ።በኡጋንዳ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን አጥተዋል

የዓይን ሕክምና አገልግሎት እጦት

ዶ/ር ዋይስዋ ጁሊየስ የሉቡ መንደር በምትገኝ ባተር ቡካቴቤ ካውንቲ ብቸኛው ዶክተር ነው።

በማዩጌ ጤና ማዕከል በሳምንት ሁለት ቀናት ተገኝቶ ከሉቡ የሚመጡ ህሙማንን ያክማል።

በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን ለማጣታቸው አንዱ ምክንያት ድህነት እና የንጽህና አጠባበቅ ጉድለት ነው ይላል።

ነዋሪዎች ዓይናቸውን ሲታመሙ ከዘመናዊ ይልቅ ባሕላዊ ሕክምናዎችን ማስቀደማቸውም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል።

ዶ/ር ጁሊየስ እነዚህ ባሕላዊ እምነቶች ሰዎች ወደ ዘመናዊ ሕክምና እንዳይመጡ ያደረገ ሲሆን፣ በሚመጡበትም ወቅት በሽታው ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ስለሚሆን ዘላቂ ጉዳት ይዘው ይቀራሉ ሲል ያብራራል።

“መንግሥት በየወረዳዎች የዓይን ሐኪሞችን ቁጥር ቢጨምር የተሻለ መሥራት ይቻላል ብዬ አምናለሁ” ሲል ያክላል።

ዶ/ር አልፍሬድ ሙባንጊዚ በኡጋንዳ ጤና ሚኒስቴር ውስጥ የትሮፒካል በሽታዎች ባለሙያ ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ መንግሥት ሕክምና የሚያጠኑ ተማሪዎች በዓይን ሕክምና ስፔሻላይዝ እንዲያደርጉ ድጎማ እያደረገ ነው።

“ዶክተሮችን እያሰለጠንን ነው። መንግሥት በዓይን ሕክምና ስፔሻላይዝ እንዲያደርጉ የተለያዩ ድጎማዎችን እያደረገ ነው” ይላሉ።