በስኅተት የሰሜን ኮሪያ የአይቲ ባለሙያ የቀጠረው ኩባንያ መረጃውን ተሰረቀ

የሰሜን ኮሪያ የሳይበር ወንጀለኛ ከቤት ሆኖ እንዲሰራለት በስኅተት የቀጠረው ኩባንያ መረጃው እንደተሰረቀ አስታወቀ።

ስሙ ያልተጠቀሰው ኩባንያ በስኅተት ሰሜን ኮሪያዊውን ግለሰብ የቀጠረው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አዋቂ የሆነው ሰው የተሳሳተ መረጃ በማቅረቡ ነው።

ሰሜን ኮሪያዊው የኩባንያውን የኮምፒውተር መረባ ካገኘ በኋላ በጣም አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ሰርቆ ማስመለሻ የሚሆን ገንዘብ አምጡ ሲል ጠይቋል።

ምንም እንኳ ይህ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና አውስትራሊያ ቢሮዎች ያሉት ኩባንያ ስሙ እንዳይጠቀስ ቢጠይቅም ሌሎች እንዲማሩበት በሚል የተፈጠረው ነገር ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ፈቅዷል።

ምዕራባዊያን ኩባንያዎች ከቤታቸው ሆነው በሚሠሩ የሰሜን ኮሪያ የሳይበር ወንጀለኞች ሲታለሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ሰሜን ኮሪያዊው የአይቲ ባለሙያ ከወራት በፊት ነው ለኩባንያው ኮንትራክተር ሆኖ ከቤቱ እንዲሠራ የተቀጠረው።

ኩባንያው ባቀረበለት መረጃ መሠረት ከቤቱ ሆኖ ኮምፒውተሮችን በመበርበር የኮርፖሬት ኔትዎርኩን ማግኘት ችሏል። ቀጥሎ በጣም አስፈላጊ እና ምስጢራዊ ናቸው ያላቸውን በርካታ መረጃዎች ወደ ግል ኮምፒውተሩ አዛውሯል።

የሳይበር ወንጀለኛው ለኩባንያው ለአራት ወራት ያክል ደሞዝ እየተከፈለው ሠርቷል።

ምንም እንኳ ከምዕራባዊያን ሀገራት ወደ ሰሜን ኮሪያ ገንዘብ መላክ ባይቻልም ግለሰቡ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጠቅሞ ሳይቀበል እንዳልቀረ ተገምቷል።

ምዕራባዊያን ሰሜን ኮሪያ ላይ ከጣሏቸው ማዕቀቦች መካከል አንዱ የገንዘብ ዝውውር ነው።

ኩባንያው ግለሰቡን በአቅም ምክንያት ሲያባረው ነው በጣም ምስጢራዊ የሚባሉ መረጃዎችን የያዘ ኢሜል የደረሰው። ግለሰቡ 6 ዲጂት የሚሆን ገንዘብ በክሪፕቶከረንሲ እንዲከፈለው ጠይቋል።

መረጃ መዝባሪው ግለሰብ ኩባንያው የተጠየቀውን ገንዘብ የማይከፍል ከሆነ መረጃዎቹን ይፋ እንደሚያደርጋቸው አሊያም እንደሚሸጣቸው አስጠንቅቋል።

ኩባንያው የተጠየቀውን ገንዘብ ይክፈል አይክፈል አይታወቅም።

በተለይ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ የሰሜን ኮሪያ የሳይበር ወንጀለኞች ምዕራባዊያን ኩባንያዎችን ሠርሥረው እየገቡ ነው።

አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ፤ ሰሜን ኮሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ጥሩ ክፍያ ያላቸው ከቤት የሚሠሩ ሥራዎች ላይ እያሰማራቸው ለአገዛዙ ገንዘብ እንዲያመጡ እያደረገች ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

ባለፈው መስከረም ማንዲያንት የተባለው የሳይበር ደኅንነት ኩባንያ ባወጣው መረጃ መሠረት በርካታ ምዕራባዊያን ኩባንያዎች በስኅተት ሰሜን ኮሪያዊያንን ቀጥረዋል።

ባለፈው ሐምሌ አንድ ሰሜን ኮሪያዊ የአይቲ ባለሙያ እንዲሁ መረጃ ለመመዝበር ሲሞክር ሊደረስበት እንደቻለ ይታወሳል።

ግለሰቡ ፈተና አልፎ ከተቀጠረ በኋላ የሚጠቀምበት የኮምፒውተር መሣሪያ ሲላክለት ወዲያውኑ አዳዲስ ሶፍትዌሮች መጫን ሲጀምር ነው የተደረሰበት።

ባለሥልጣናት የአይቲ ባለሙያ የሆኑ ሰዎችን ስትቀጥሩ በተለይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከቤት የሚሠሩ ከሆነ ጥንቃቄ አድርጉ ሲሉ ለኩባንያዎች ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)