ጣሊያን ጥንዶች ለማሕጸን ኪራይ ወደ ውጭ አገራት እንዳይሄዱ ከለከለች

ጣሊያን፤ ጥንዶች ማሕጸን ለመከራየት ወደ ውጭ ሀገራት እንዳይሄዱ የሚከለክል ሕግ በማጽደቅ ድርጊቱ በወንጀል የሚያስቀጣ መሆኑን ገልጻለች።

ጣሊያን ያገደችው ጥንዶች ወይም የፍቅር አጋሮች ልጅ ለመውለድ ሲባል ወደ ውጭ አገር በመጓዝ በገንዘብ በመደራደር ከሌላ ሴት ማሕጸን እንዳይከራዩ የሚያስችል ነው።

ወደ ውጭ አገራት በመሄድ የማሕጸን ኪራይ ከሚፈጽሙት በተጨማሪ በአገር ውስጥም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም እገዳ ጥላለች።

ይህንን ክልከላ ተላልፈው የተገኙ ግለሰቦች እስከ ሁለት ዓመት እስራት እና አንድ ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተገልጿል።

በጣሊያን ወግ አጥባቂ ፓርቲ የረቀቀው ይህ ሕግ፣ ብዙ ትችቶችን እያስተናገደ ነው። ተችዎቹ የጸደቀው ሕግ በተለይ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን ዒላማ ያደረገ ነው ብለውታል።

የማሕጸን ኪራይ ማለት በመካንነት ወይም በሌላ ምክንያት መውለድ የማይችሉ ሰዎችን ጽንስ ሌላ ሴት በማሕጸኗ እንድታሳድግ ማድረግ ነው።

ይህንን ድርጊት መውለድ የተሳናቸው ተቃራኒ ጾታዎች ብቻ ሳይሆኑ ወንድ ጥንዶችም [የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን] ይፈጽሙታል።

በጣሊያን ሕጉ የጸደቀው በአብላጫ ድምጽ ረቡዕ [06/02/2017 ዓ.ም] ነው። ሕጉ ከመጽደቁ በፊት ረቂቁ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

በተለይ ሰዎች በአገሪቱ ቤተሰብ አልባ መሆናቸው እና የወሊድ መጠን እያሽቆለቆለ መሆኑን በመጥቀስ ሕጉ እንዳይጸድቅ የሞገቱ በርካቶች ቢሆኑም በ84 ድጋፍ እና በ58 ተቃውሞ የአገሪቱ ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ ተደርጓል።

የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን የጸደቀውን ሕግ በጽኑ አውግዘውታል። እርምጃው የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂና ሜሎኒ ድጋፍም አለበት ተብሏል።

ራሳቸውን እንደ ክርስትያን እናት የሚቆጥሩት ጠቅላይ ሚንስትሯ፣ ልጆች መወለድ ያለባቸው ከወንድ አባት እና ሴት እናት ብቻ ነው ብለው ያምናሉ።

ሜሎኒ ቀደም ሲል ስለማሕጸን ኪራይ አላስፈላጊነት ሲናገሩ ተሰምተው ነበር።

በምርጫ ቅስቃሳቸው ወቅትም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የማይደግፍ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር።

በ2023 የእርሳቸው መንግሥት ከተመሳሳይ ጾታ የተገኙ ልጆችን እንዳይመዘገብ ለሚላን ከተማ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ሜሎኒ የማሕጸን ኪራይ የፈጣሪን ጸጋ እና ብቸኛ ስልጣን በገንዘብ መግዛት እንደሚቻል ለማሰየት የሚሞክር ማጭበርበር ነው ብለው ያምናሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሯ ብቻ ሳይሆኑ ምክትላቸው ማቴዮ ሳልቪኒም የማሕጸን ኪራይን በጽኑ አውግዘውታል። “ሴቶችን እንደ ኤቲኤም ማሽን የሚቆጥር ድርጊት ነው” ብለውታል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያ እንደሚሉት የማህጸን ኪራይ ከሚፈጽሙት 90 በመቶ የሚሆኑት የተቃራኒ ጾታ ጥንዶች ናቸው።

የማሕጸን ኪራይን በተመለከተ የተለያዩ አገራት የተለያየ ሕግ አላቸው። ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ጣሊያን እና ጀርመን የማሕጸን ኪራይን በሕግ የከለከሉ የአውሮፓ አገራት ናቸው።

በዩናይትድ ኪንግደም የማሕጸን ኪራይ ቢፈቀድም ጽንሱን ለምትሸከመው ሴት የተጋነነ ክፍያ መፈጸም ክልክል ነው። በአየርላንድ፣ ሆላንድ፣ ቤልጂየም እና ቼክ ሪፐብሊክ ፍርድ ቤት ስለማሕጸን ኪራይ ውሳኔ አይሰጥም።

ግሪክ ደግሞ የውጭ አገር ሰዎች የማሕጸን ኪራይ ቢፈጽሙ በሕጋዊነት ትቀበላቸዋለች። ነገር ግን ማሕጸን የምታከራየዋ ሴት ትዳር የሌላት መሆኗ መረጋገጥ አለበት።

አሜሪካ እና ካናዳ ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች የማሕጸን ኪራይን የሚፈቅዱ ሲሆን ጥንዶቹ ከውልደት ጀምሮ የወላጅነት መብትም ያገኛሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)