በሶሻል ሚዲያ ተመልካች እና ገንዘብ ለማግኘት አደጋ የሚጋፈጡ አሜሪካውያን ተጽእኖ ፈጣሪዎች

የአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ባለፈው ሳምንት ሚልተን በሚባል አደገኛ አውሎ ነፋስ እና የባሕር ወጀብ ተመትታለች።

ትላልቅ ህንጻዎችን ሲደረምስ፣ ድልድዮችን ሲያፈራርስ፣ የቤቶችን ጣሪያ ሲገነጣጥል፣ ትልልቅ ቁሶችን ሲያንሳፍፍ የሚታየውን አውዳሚውን አውሎ ነፋስ እና የባሕር ወጀብ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሲሸሹት የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪው ማይክ ስሞልስ ጁኒየር ዘሎ ከመሃል ላይ ገባ።

ማይክ የሚንሳፈፍ ፍራሽ፣ ጃንጥላ እና የሚበላትን የታሸገች ኑድልስ ይዞ ነው ለተመልካቾቹ ለማሳየት ወደ ከባዱ አውሎ ነፋስ የገባው።

አውሎ ነፋሱ እና ወጀቡ ዛፎችን እየገነደሰ በነበረበት ባለፈው ሳምንት ማይክ ስልኩን ይዞ ኪክ በተሰኘ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በቀጥታ ማስተላለፍ ጀመረ።

በቀጥታ የሚከታተሉት ተመልካቾች ቁጥር 10 ሺህ ላይ ከደረሰ ፍራሹን ይዞ የውሃ ማዕበሉ ውስጥ እገባለሁ አለ።

አስር ሺህ ተመልካቾች ላይ ሲደርስ ውሃው ውስጥ ገባ።

ብዙም ሳይቆይ አስጨነቀው። “አውሎ ነፋሱ በከፍተኛ ሁኔታ መንፈስ ጀመረ። መዋኘት ስለማልችል አጠገቤ የነበረውን ግንድ አቀፍኩት” ብሏል።

ማይክ የተገኘበት ታምፓ ቤይ የተሰኘው ስፍራ ባለሥልጣናት ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ለቀው እንዲሄዱ ትዕዛዝ የሰጡበት አካባቢን ይሸፍናል።

ማይክ ከታምፓ ቤይ ሆኖ አውሎ ነፋሱን በተመለከተ ለአንድ ሰዓት ያህል ያስተላለፈው የቀጥታ ዘገባ በኪክ ማኅበራዊ መድረክ ላይ 60 ሺህ ዕይታዎችን አግኝቷል።

ቪዲዮው ኤክስን ጨምሮ ወደተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሻገረ ሲሆን፣ በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አይተውታል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ራሳቸውን በቀጥታ በመቅረጽ ማስተላለፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትርፋማ እያደረጋቸው መጥቷል።

ሆኖም በማኅበራዊ መድረክ የይዘት ፈጣሪዎች መካከል ፉክክሮች መጨመራቸውን ተከትሎ እነዚህ የቀጥታ ሥርጭቶችን የበለጠ ዕይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ አደገኛ ሁኔታዎች ሲሞከሩ ታይተዋል።

በርካቶች ማይክ በማኅበራዊ ሚዲያ ታዋቂነቱን ለመጨመር ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሏል ሲሉ ተችተውታል።

ማይክ ከዚህ አውሎ ነፋስ እና ወጀብ በደህና መውጣቱን ለቢቢሲ ቢናገርም “ዋጋው የሚያዋጣ” ከሆነ እንደገና ይህንኑ አደገኛ ተግባር እንደሚደግመው አልደበቀም።

የቀረቡበትን ትችቶች አስመልክቶ ምላሽ የሰጠው ማይክ የፈጸመው ጉዳይ “አወዛጋቢ” እንደሆነ ያምናል። በተጨማሪም ይህንን አውሎ ነፋስ ለመቅረጽ ያደረገው ጥረት ሕይወቱ አደጋ ላይ ቢወድቅ ሊታደጉት የሚችሉትን እንዲሁ አደጋ ላይ እንደሚጥል አላጣውም።

ነገር ግን “ከይዘት ፈጣሪ ዕይታ አንጻር ሳየው ታዳሚዎች እንዲህ ዓይነት ጽንፍ የወጡ ነገሮችን ማየት ይወዳሉ” ሲል ይከራከራል።

የታምፓ ፖሊስ በበኩሉ “ነዋሪዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸውን አካባቢዎች ችላ ማለት ሕይወትን አደጋ ላይ ይጥላል። ግለሰቦች እነዚህን ማስጠንቀቂዎች ችላ ሲሉ የራሳቸውን ደኅንነት ብቻ ሳይሆን የበርካቶችን ሕይወት ለመታደግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሚጥሩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተጨማሪ ፈተናዎችን ይፈጥራሉ” ሲል አስጠንቅቋል።

አክሎም “ሆን ብሎ ራስን አደጋ ላይ መጣል ወሳኝ ሃብት ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲዞር እና ሌሎችን የመታደግ ተግባራትን ሊያዘገይ ይችላል” ብሏል።

የአሜሪካ ደቡባዊ ምሥራቅ የባሕር ዳርቻ ክፍሎችን ያወደመው የዘንድሮው አውሎ ነፋስ እና ወጀብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

ደረጃ አምስት አደገኛ በሚል በተፈረጀው ሚልተን በተሰኘው አውሎ ነፋስ እና የባሕር ወጀብ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አካባቢያቸውን ለቅቀው ለመውጣት ተገድደዋል።

በሚልተን ኸሪኬን ምክንያት እስካሁን ቢያንስ 16 ሰዎች ሲሞቱ ሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲቋረጥባቸው አድርጓል። ቤቶቻቸው በወጀቡ የተወሰደባቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እንደታደጓቸው ተዘግቧል።

ከሚልተን በተጨማሪ ሄሌኔ የሚባል አውሎ ነፋስ እና የባሕር ወጀብ የተቀላቀለባት አሜሪካ በሁለት ሳምንታት ውስጥ አምስት ክስተቶችን አስተናግዳለች።

በእነዚህ አውሎ ነፋሶች እና የባሕር ወጀቦች ውስጥ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በኪክ እና ቲክቶክ በቀጥታ ከሚያስተላልፉት ማኅበራዊ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ውስጥ ማይክ አንዱ ነው።

ማይክ የቀጥታ ሥርጭቶችን ማስተላለፍ የሙሉ ጊዜ ሥራው እንደሆነ ይናገራል።

ማይክ አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ ይዘቶችን ሲሠራ የመጀመሪያው አይደለም። ለምሳሌም ያህል በመኝታ ክፍል ውስጥ ርችቶችን ማቀጣጠል፣ ፈጣን ምግብ በሚያዘጋጁ ሬስቶራንቶች ላይ ሠራተኞች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ ይገኝበታል።

ከአወዛጋቢ ይዘቶች በተጨማሪ ራሱን ለአደጋ ሲያጋልጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከሚልተን በፊት ፍሎሪዳን ጨምሮ ሌሎች ግዛቶችን የመታውን ሄሌኔ አውሎ ነፋስ እና የባሕር ወጀብ ድንኳን ተክሎ ለአምስት ሰዓታት ያህል በቀጥታ አስተላልፏል።

በአንድ ጎዳና ስር ድንኳኑ ውስጥ ሆኖ ከዚህ ኸሪኬን እተርፋለሁ እያለ በስልኩ ቀርጿል። “ለምን? ሰዎችን ለማዝናናት?” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ከሱ በሜትሮች ርቀት የባሕሩ ወጀብ ከፍተኛ ነበር።

እንደ ኪክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚያገኟቸው ዕይታዎች ብዛት ገንዘብ ይከፍላሉ እንዲሁም በርካቶችም ልገሳዎችን ይሰጣሉ።

ማይክ በዚህ በቀጥታ ባስተላለፈው ሥርጭቱ ምን ያህል ገንዘብ እንዳገኘ ባይገልጽም እንደ ይዘታቸው አንዳንዶች በሰዓት ከ300 እስከ 400 ዶላር ያገኛሉ ብሏል። አውሎ ነፋሱን በቀጥታ በማሳየት በቂ ገንዘብ እንዳገኘም አክሏል።

ዕይታውን ለመጨመር ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይል ቢመስልም የደኅንነቱን ጉዳይ በቁም ነገር እንደሚያየው እና ጉዳቶችን እንደሚገመገም አጥብቆ ገልጿል።

ከዚህ ተፈጥሯዊ ቀውስ ከተረፈ በኋላ በሙሉ ልብነት የሚናገረው ማይክ “አልሞትኩም። አለሁ። እየተዝናናሁ ነው” ሲል መልሷል።

የማይክን ይዘት እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ኃላፊነትን በተመለከተ ኪክን ቢቢሲ የጠየቀው ሲሆን፣ “በይዘት የፈጠራ ሥራዎች ላይ ተጽእኖ አናደርግም፤ ጣልቃ አንገባም። ነገር ግን ይዘቱ ሕገወጥ ወይም መመሪያዎቻችንን የሚጥስ ከሆነ እናግዳለን” ብሏል።

የማይክ ይዘት በድረገጻቸው ላይ የሰፈረውን “ደኅንነት መጀመሪያ፣ ደኅንነት ለራስ፣ ለታዳሚዎች እና ለሕዝብ” የሚለውን መመሪያ ጥሶ እንደሆነ ኪክ ሲጠየቅ ምላሽ አልሰጠም።

ቲክቶክ በበኩሉ በቀጥታ ዘገባ ወቅት አንዳንድ ይዘቶች ገንዘብ ለማግኘት ብቁ እንዳልሆኑ ለቢቢሲ ገልጿል።

እነዚህም “ሌሎችን የሚያታልሉ፣ የሚያጭበረብሩ ይዘቶች ወይም ዕይታን ለማግኘት አወዛጋቢ ጉዳዮችን መሥራት እንዲሁም ተጋላጭ ሰዎችን መጠቀም” እንደሆነ አትቷል።

የማይክ የኸሪኬን ቪዲዮዎች አሁንም አሉ።

ማይክ ራሱን አደጋ በሚጥሉ ይዘቶች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ሕይወት አደጋ ሊጥል እንደሚችል ለቀረበለት ጥያቄ ምን እየሠራ እንደሆነ እንደሚገነዘብ ተናግሯል።

“አታድኑኝ” የሚለው ማይክ “ሌላ አውሎ ነፋስ እና የባሕር ወጀብን ከቀረጽኩኝ፤ ምንም እንዳታደርጉ፤ እሺ። ምንም ማለት አይጠበቅባችሁም። ሕይወታችሁን አደጋ ላይ መጣል የለባችሁም። በጭራሽ” ብሏል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)