እስራኤል ክርስቲያኖች በሚበዙበት ሰሜናዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት 21 ሰዎች ተገደሉ
የእስራኤል አየር ኃይል በርካታ ክርስቲያኖች በሚኖሩበት ሰሜናዊ የሊባኖስ አካባቢ በፈጸመው ጥቃት ከሃያ የሚልቁ ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ።
እስራኤል በሊባኖስ ለሳምንታት እያካሄደች ያለውን የአየር ድብደባ አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ በሊባኖስ የተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ ነው።
የሊባኖስ የጤና ሚንስቴር እንደገለጸው እስራኤል ብዙም ዒላማ አድርጋው በማታውቀው በሰሜን ሊባኖስ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሳቢያ 21 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።
በዚሁ ጥቃት ሌሎች 8 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ የእስራኤል ጦር ከሄዝቦላህ ጋር ከሚፋለምበት ሥፍራ ጋር በቅርበት የማይዋሰን እና በዋናነት የክርስቲያኖች መኖሪያ መንደር ነው።
ነዋሪዎች እንደሚሉት ይህ አካባቢ በአብዛኛው ከደቡብ ሊባኖስ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች የሚኖሩበት ነው።
በጉዳዩ ላይ የእስራኤል ጦር እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታያኔሁ ግን ሄዝቦላህን በየትኛውም የሊባኖስ አካባቢ “ከገባበት ገብተን እንፋለመዋለን” በማለት ዝተዋል።
“ሁሉም ነገር ዘመቻን ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህንን በእስካሁኑ ጉዟችን አሻሽለናል። በቀጣዮቹ ቀናትም የበለጠ እናሻሽለዋለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ከሰሞኑ በሄዝቦላህ የድሮን ጥቃት አራት ወታደሮች የተገደሉበትን እና ሌሎች የቆሰሉበትን የሰሜን እስራኤል የጦር ሰፈር ጎብኝተዋል።
ይህንን ተከትሎ የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ ድሮን ጥቃት ጠንካራውን የመከላከያ ሥርዓት በመጣስ በሠራዊቱ እና በጎላን ወታደራዊ ማሠልጠኛ ላይ እንዴት ጥቃት እንደተፈጸመ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህ በሄዝቦላህ በኩል የተፈጸመ ትልቁ ጥቃት ነው።
ሄዝቦላህ ይህንን ጥቃት የፈጸመው በሊባኖስ በአንድ ወር ውስጥ ለተገደሉ ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎች በቀል በሚል እንደሆነ ገልጿል።
ብዙዎቹ የእስራኤል የአየር ጥቃቶች ዒላማ የሚያደርጉት የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ በሆኑትን ደቡብ እና ምሥራቅ ሊባኖስን ነው።
ነገር ግን ሰኞ ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም. ጥቃቱ የተፈጸመባት አይተዋ የተባለችው ተራራማ መንደር ከሄዝቦላህ ይዞታ የራቀች እና በአብዛኛውም የክርስትና እምነት ተከታዮች የሚኖሩባት ከተማ ናት።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ አንድ ሰው “ማርያም እናቴ ሆይ” እያለ ይጮህ ነበር። በጭስ እና በአቧራ በተሞላው ፍርስራሽ ውስጥ የሰዎች አስከሬን ወድቆ ይታይ ነበር ተብሏል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው። አካባቢው ከደቡብ ሊባኖስ ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች የሚኖሩበት ነው።
ጥቃቱ የተፈጸመበት መኖሪያ ቤትም ከሁለት ሳምንት በፊት ተፈናቃዮች የተከራዩት ቤት እንደሆነ ተገልጿል።
የሊባኖስ የፀጥታ መረጃ ምንጮች ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል በሰጡት መረጃ መሠረት ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው አንድ ከመኪና ወርዶ ወደ ቤት ውስጥ የገባን ሰው ነው።
ጥቃቱ የተፈጸመውም ሰውየው ወደ ቤት ዘልቆ ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ነው። የሊባኖስ ጤና ሚንስቴር እንደገለጸው የሟቾችን ማንነት ለመለየት የዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ እየተደረገ ነው።
እስራኤል ሰኞ በፈጸመችው ጥቃት በደቡብ ናባቴህ አካባቢ የሄዝቦላህ ሬድዋን ኃይል የፀረ ታንክ ዋና አዛዥን መግደሏን አስታውቃለች። ሄዝቦላህ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
የእስራኤል ጦር ግን ወደ ሰሜን እና ማዕከላዊ እስራኤል ጥቃት የሚፈጽሙ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙንም ገልጿል።
ብዙዎቹ የተተኮሱት ሮኬቶችን ማክሸፉንም የገለጸው የእስራኤል ጦር፣ አንዲት ሴት ላይ ብቻ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)