የናይጄሪያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በሊቢያ አየር ማረፊያ የገጠመው ምንድነው?

ናይጄሪያ ከሊቢያ ጋር የነበራትን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለማካሄድ ወደ ቤንጋዚ የተጓዙት ተጫዋቾቿ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ተጉላልተዋል በሚል ጨዋታውን ሰረዘች።

ናይጄሪያ ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሊቢያ ጋር ጨዋታ ለማድረግ ማክሰኞ 05/2017 ዓ.ም. ድልድል ወጥቶላቸው ነበር። ነገር ግን የናይጄሪያ ተጫዋቾች በደረሰባቸው መጉላላት ምክንያት ጨዋታውን ለመሰረዝ ተገደዋል።

ተጫዋቾቹን ያያዘው አውሮፕላን ቤንጋዚ ማረፍ ሲገባው 230 ኪሎ ሜትር ወደምትርቀው አል አብራቅ ከተማ እንዲያመራ ተደርጓል። የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ኤርፖርቱ ውስጥ በተጫዋቾቹ ላይ ከፍተኛ መጉላላት መድረሱን ገልጿል።

የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ዊሊያም ትረስት ኤኮንግ ተጫዋቾቹ ላለመጫወት በመወሰን የአገራቸው መንግሥት እንዲረዳቸው መጠየቃቸውን ገልጿል።

የናይጄሪያ የስፖርት ልማት ሚንስቴር ደግሞ አሳሳቢ ጉዳይ የነበረው ተጫዋቾቹን በሰላም የመመለሱ ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሊቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ደግሞ ተጫዋቾቹ ላይ የደረሰው መጉላላት አሳሳቢ ቢሆንም፤ ጉዳዩ ግን ጨዋታውን ከመጉዳት ጋር አይያያዝም ብሏል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተጫዋቾቹ ላይ መጉላላት መፈጸሙን ተከትሎ ከሁለቱም አገራት የስፖርት ፌደሬሽኖች ጋር ንግግር እያደረገ ነው።

ጉዳዩም ወደ ሚመለከተው አጣሪ ቡድን መላኩን እና ጥፋት ሆኖ ከተገኘም ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የናይጄሪያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን የሚዲያ ማናጀር ፕሮሚስ ኤፎጌ በረራቸው ወደ አል አብራቅ ከተማ እንዲዞር ሲደረግ ምንም የተሰጣቸው ማብራሪያ አለመኖሩን ተናግረዋል።

“ስለጉዳዩ ማብራሪያ ለመስጠት ወደ እኛ የመጣ የሊቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አልነበረም፤ እኛን ለማገዝ ምንም ጥረት አላደረጉም። የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አማራጭ መንገዶችን ሲያፈላልግ እኛ ኤርፖርት ውስጥ ተዘግቶብን ነበር።”

“ልክ ኤርፖርት ውስጥ እስረኞች ነው የነበርነው” በማለት ፕሮሚስ አብራርተዋል።

የባየርሊቨርኩሰኑ ኮከብ ቪክቶር ቦኒፌስ ለ13 ሰዓታት ያለምግብ፣ ያለዋይፋይ እና ያለመኝታ አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፋቸውን በኤክስ ገጹ አስፍሯል።

የሊቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ግን ጉዳዩ በበረራ ሂደት የሚያጋጥም እና አዲስ አለመሆኑን ገልጾ ከናይጄሪያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ጋር የተፈጠረው መስተጓጎል በመረዳዳት እልባት እንደሚያገኝ እምነቱን ገልጿል።

የናይጄሪያው የስፖርት ልማት ሚኒስትር በበኩላቸው በጉዳዩ ዙሪያ ከካፍ ፕሬዝዳንት ጋር መነጋገራቸውንና በዚህ ምክንያትም የሊቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከባድ የዲሲፕሊን እርምጃ እንደሚወሰድበት ይጠብቃሉ።

ክስተቱ ካጋጠመ በኋላ ተጫዋቾቹ ከተፈጠረባቸው የስሜት መረበሽ ባሻገር ለደኅንነታቸው በመስጋት ጨዋታውን ላለማድረግ ወስነዋል።

ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ሊቢያ ናይጄሪያ ውስጥ በነበረው ጨዋታ በደል ተፈጽሞብኛል የሚል ቅሬታ ካስገባች በኋላ ነው።

የሊቢያ ባለሥልጣናት እንዳሉት ናይጄሪያ ከደረሱ በኋላ ወደ ፖርት ሃርኮርት እንዲሄዱ ተገደዋል። ከዚያም በተጨማሪ ኦዮ ወደተባለው ከተማ ለመሄድ 130 ኪሎ ሜትር “የምንጓዝበት አውቶብስ አላዘጋጁልንም” በማለት ከሰዋል። እነዚህን ክሶች ግን የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ውድቅ አድርጓቸዋል።

በተመሳሳይ የሊቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ፈጸሙት የተባለውን መጉላላት እንደማይቀበሉት ገልጸዋል።

ሊቢያ በሁለት አስተዳደር ተከፍላለች። አንደኛው የምሥራቁ ክፍል ሲሆን ቤንጋዚ ያለበት ነው። ሁለተኛው ደግሞ መዲናዋ ትሪፖሊ የምትገኝበት የምዕራቡ ክፍል ነው። ሁለቱም ገዥዎች የአገሪቱ ሕጋዊ መንግሥት እንደሆኑ ይገልጻሉ።

በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት ትሪፖሊ ያለው የናይጄሪያ ኢምባሲ ምንም ማድረግ አልቻለም።

ሁለቱ አገራት ባለፈው አርብ ናይጄሪያ ውስጥ ተጫውተው አስተናጋጇ ናይጄሪያ አንድ ለምንም አሸንፋለች። በማጣሪያው ድልድል ቡድን ዲ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ናይጄሪያ በሰባት ነጥብ ምድቡን ስትመራ፣ ሊቢያ ደግሞ በአንድ ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ትገኛለች።

የሊቢያ እግር ኳስ ቡድን ማክሰኞ የሚካሄደውን የማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ በሜዳው እንደሚገኝ አሳውቋል። ነገር ግን ናይጄሪያ ካልተገኘች ‘በፎርፌ’ ሶስት ነጥብ እና ሶስት ጎል ለሊቢያ ይሰጣል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)