“አውሮፓ መግባት፤ ወይም ሞት” – ካናሪ ደሴት ለመግባት የቆረጠው ሞሐመድ

ሴኔጋላዊው አርሶ አደር ሞሐመድ ኡዋሊ ውቅያኖስ አይቶ አያውቅም። ቢሆንም በጣም ፈታኝ ከሚባለው ጉዞ የሚያቆመው ያለ አይመስልም። ይህ ጉዞ አትላንቲክ ውቅያኖስን የጅምላ መቃብር ያስባለ ጉዞ ነው።

“ባለጀልባው ደውሎልኝ ተዘጋጅ ብሎ ነገረኝ። ፀሎት አድርጉልኝ። ጊዜው ደርሷል” ይላል።

ስደተኞች አደገኛ የሚባለውን የውቅያኖስ ጉዞ አቋርጠው አውሮፓ ይገባል። ይህ አስፈሪ መንገድ በምዕራብ አፍሪካ እና በስፔን ካናሪ ደሴቶች መካከል ያለ ነው።

ቢቢሲ አፍሪካ ይህን አደገኛ እና ምሥጢራዊ የሚባል መንገድ መመልከት ችሏል።

ሞሐመድ ወደ ደሴቷ መድረስ ከሚጓጉ በርካታ ስደተኞች መካከል ነው። የስደተኞች ቁጥር ከምን ጊዜውም በላይ ከፍ ያለበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው።

የደሴቷ መንግሥት ወደዚህ ስትመጡ የሚጠብቃችሁ “በጣም የተጨናነቀ እና ሊፈርስ የደረሰ” ሥርዓት ነው ይላሉ። የሞሐመድን ቁርጠኝነት ግን የሚገታው ያለ አይመስልም።

ሞሐመድ ከእንጨት በተሠራው የዓሳ አስጋሪዎች ጀልባ ተጎዞ ካናሪ ለመግባት ቀናት ሲከፋ ደግሞ ሳምንታት ሊወስድበት ይችላል። ውቅያኖሱ አመፀኛ ነው።

ከሴኔጋል እስከ ካናሪ ያለውን ውቅያኖስ ለማቋረጥ ከ1 ሺህ እስከ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር መጓዝን ሊጠይቅ ይችላል። ይህ ጉዞ ሜዲቴራኒያንን አቋርጠው ከሚጓዙ መርከቦች አንፃር 10 እጥፍ ሩቅ ነው።

ማዕበል እና ወጀቡን ተሻግሮ ማለፍ ቀላል አይደለም። የውሀ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል። እንቅስቃሴ ሲበዛ ደግሞ ህመም (ሞሽን ሲክነስ) ይከሰታል። አንዳንድ መንገደኞች በፍርሀት የሚያደርጉት ይጠፋቸዋል።

ሲመሽ ሁኔታው ይከፋል። ጨለማው ጥቅጥቅ ነው። በውሀ ጥማት እና በመጨናነቅ መካከል የሚፈጠረው አይታወቅም።

ከውቅያኖሱ ዳርቻ ራቅ ብሎ በሴኔጋሏ ታምባኮንዳ ግዛት የሚኖሩት የሞሐመድ ልጅ እና ቤተሰቦች ከግብርና የሚያገኘው ገንዘብ ላይ ጥገኛ ናቸው።

የ40 ዓመቱ አርሶ አድር ቤተሰቡን ካየ አንድ ዓመት አልፎታል። በውቅያኖስ አቋርጦ አውሮፓ ለመግባት ከመሞከሩ በፊት ወደ ባሕር ዳርቻው መጥቶ ቆይቷል።

በሴኔጋል የባሕር ዳርቻ በሞተር ብስክሌት የታክሲ አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ከወዳጅ ዘመዶቹ 1 ሺህ ዶላር አሰባስቦ ነው ወደ ካናሪ ለሚሄደው ጀልባ የከፈለው።

ሰው አዘዋዋሪዎቹ ብሬን ይበሉኛል ብሎ በማሰብ ገንዘቡን የሚሰጣቸው በቃላቸው መሠረት አውሮፓ ካስገቡት በኋላ እንደሆነ ነግሯቸዋል።

“ውቅያኖስ ላይ እያለሁ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም። የውቅያኖስ ክፉ መንፈስ ሊደፋኝ ይችላል” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

“ጀልባው ተገልብጦ ሁላችንም ልንሞት እንችላለን። ባሕር ውስጥ ብወድቅ ምን ይዤ ነው የምትርፈው? ከመሞት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። ቢሆንም የሚመጣውን ለመጋፈጥ ዝግጁ ነኝ።”

በርካታ ጀልባዎች ሰጥመዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል። አስፈላጊውን መሣሪያ ሳይዙ ባሕር መቅዘፍ ቀላል አይደለም። አንዳንዶች መንገዳቸውን ስተው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ውሀ እየገፈተረ ወደ ብራዚል ወስዷቸዋል።

ሞሐመድ ይህን አስፈሪ መንገድ ተሻግሮ አውሮፓ ከገባ በኋላ ሕይወቱን ቀይሮ ለሰፊው ቤተሰቡ ገንዘብ መላክ ያስባል።

ምንም እንኳ ሴኔጋል ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ጠንካራ የሚባል ምጣኔ ሀብት ብታዳብርም ከአገሪቱ ሕዝብ ከአንድ ሦስተኛው በላይ አሁንም በደህነት ይማቅቃል ይላል የዓለም ባንክ መረጃ።

“ሁሉንም ዓይነት ሥራ ሠርቻለሁ። ቢሆንም ሊሞላልኝ አልቻለም። ገንዘብ ከሌለህ ዋጋ የለህም። [ለቤተሰቦቼ] ያለኋቸው እኔ ነኝ ግን እጄ ላይ ገንዘብ የለም” ይላል።

ልክ እንደ ሞሐመድ ሁሉ በርካታ ስደተኞች ድህነት እና ግጭት በመሸሽ ከአፍሪካ አገራት ወደ አውሮፓ ይሻገራሉ።

የካናሪ ደሴቶች አውሮፓ መግባት ለሚሹ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዋናዋ መዳረሻ ሆናለች። ጣሊያን እና ግሪክ በሜዲቴራኒያን ባሕር በኩል ከሊቢያ እና ከቱኒዚያ የሚመጡ ስደተኞችን አንቀበለም ማለታቸውን ተከትሎ ነው ስደተኞች ፊታቸውን ወደ ካናሪ ያዞሩት።

በአውሮፓውያኑ 2023፤ 40 ሺህ ገደማ ስደተኞች ወደ ካናሪ ደሴት አቅንተዋል። ይህ በሦስት አስርት ዓመታት ታሪክ ትልቁ ቁጥር ነው። በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት 31 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ገብተዋል።

የአትላንቲክ ውቅያኖስ የአየር ሁኔታ ሲሻሻል ሁኔታዎች “እየከፉ ሊመጡ” ይችላሉ ይላል የደሴቷ አስተዳደር።

የካናሪ ደሴቶች ፕሬዝንት የሆኑት ፈርናንዶ ክላቪሆ፤ የውቅያኖሱ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፣ ፖሊስ እና የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞች ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል ሲሉ ለቢቢሲ አፍሪካ አይ ይናገራሉ።

“በርካታ ሰዎች መሞታቸው አይቀርም። ስደተኞችን መርዳታ ሊያቅተን ይችላል። ስደተኞቹ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል” ይላሉ።

“በአሁኑ ወቅት በሜዲቴራኒያን በኩል ወደ አውሮፓ መግባት አይቻልም። ይህ ማለት በጣም አደገኛ በሚባለው በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል ነው ሰዎች የሚመጡት ማለት ነው።”

ቢቢሲ ያናገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የስፔን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሁኔታው እጅግ ጉልበታቸው እንደዛለ ይናገራሉ።

አንድ ግለሰብ “የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሞት ማየት ሰልችቷቸዋል” ይላሉ።

ከካናሪ ደሴቶች መካከል ትንሿ ደሴት ኤል-ሂየሮ ትባላለች። ከ2023 ጀምሮ ወደ ደሴቷ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር የሕዝቡን ብዛት እጥፍ አድርጎት 30 ሺህ አድርሶታል።

የደሴቶቹ ፕሬዝደንት እንደሚሉት የሕዝብ ማመለሻ አውቶቡሶች ስደተኞችን ለማመላለስ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ዜጎች የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም አልቻሉም። ይህ ሁኔታ ወደ መጤ ጠልነት እና ማኅበረሰባዊ ነውጥ እንዳይሻገር ፍርሀት እንዳላቸው ይናገራሉ።

ስደተኞች ቁጥራቸው መብዛቱን ተከትሎ በስፔን አገራዊ ክርክር እየተካሄደ ይገኛል። ሕገ ወጥ ስደትን እንዴት መከላከል እና ለስደተኞች በተለይ ብቻቸውን ላሉ ሕፃናት እንክብካቤ ማድረግ እንደሚቻል ውይይት እየተደረገ ነው።

ሞሐመድ በስተመጨረሻ በሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎቹ ጀልባ አስፈሪውን የባሕር ላይ ጉዞ የሚጀምርበት ወቅት ተቃርቧል። ከዚህ በኋላ ዕጣ ፈንታው በእነሱ እጅ ነው።

“በጣም ብዙ ነን። ከጊኒ እና ከማሊ የመጡ ሰዎችም አሉ። በትናንሽ ጀልባ 10 እና 15 እያደረጉ ወስደውን ተለቅ ያለው ጀልባ ላይ ተሳፈርን። ከዚያ መንገዳችንን እንጀምራለን” ይላል።

ረዥሙን ጉዞ በድል ለመውጣት የሚያስችለውን ውሀ የሞላ ኮዳ እና የተወሰኑ ብስኩቶች ይዟል።

የመጀመሪያዎቹን ሁለት ቀናት በህመም ሲናወጥ ቆየ። ጀልባዋ በሰዎች ስለተጨናነቀች ብዙውን ጊዜውን ቆሞ ነው የሚያሳልፈው። የሚተኛው ደግሞ ውሀ እና ነዳጅ የተደባለቁበት መደብ ላይ ነው።

የያዘውን ኮዳ ውሀ በመጨረሱ ከውቅያኖሱ እየጨለፈ ለመጠጣት ተገዷል።

አንዳንድ ሰዎች በድንጋጤ እና በፍርሀት መጮህ ጀምረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መሥሪያ ቤት (አይኦኤም) መረጃ እንደሚያመለክተው የአትላንቲክ ውቅያኖስ መስመር በዓለማችን እጅግ አደገኛ እና ገዳይ ከሚባሉ መስመሮች አንዱ እየሆነ መጥቷል።

በ2024 (እአአ) ብቻ ቢያንስ 804 ሰዎች ሞተዋል አሊያም የደረሱበት አልታወቀም። ይህ አሃዝ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 74 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ባሕር ውስጥ ሰጥመው ቀርተው ያልተቆጠሩ በርካቶች ሊኖሩ ስለሚችል ይህ አሃዝ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

“በየ45 ደቂቃው አንድ ስደተኛ ይሞታል። ይህ ማለት ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪ ማፊያዎች እየበለፀጉ መጥተዋል ማለት ነው” ይላሉ የካናሪ ደሴቶች ፕሬዝደንት።

የተባበሩት መንግሥታት የአደገኛ ዕፅ እና ወንጀል ቢሮ እንደሚለው በዚህ መስመር ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ወንጀለኞች በዓመት እስከ 150 ሚሊዮን ዶላር ሊያተርፉ ይችላሉ።

ቢቢሲ ከሴኔጋል ወደ ካናሪ ደሴቶች ሰዎችን የሚያመላልሱ አዘዋዋሪዎችን አናግሯል። ስማቸው እንዲጠቀስ አይፈልጉም።

“ትልቅ ጀልባ ካለን ከ200 እስከ 300 ሰዎች ይጭናል። እያንዳንዳቸው 500 ዶላር አካባቢ ይከፍላሉ። ገንዘቡ ቀላል አይደለም” ይላሉ ሴኔጋላዊው የሰዎች አዘዋዋሪ።

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪ መሆኑ ወንጀል አይደለም ወይ? ተብሎ በቢቢሲ የተጠየቀው ይህ ግለሰብ “እውነት ነው ወንጀል ነው። የተያዘ ሰው ሊቀጣ ይገባል። ነገር ግን መፍትሔ የለውም። ሰዎች ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲሞቱ እያዩ ነው የሚመጡት።”

ሞሐመድ ለአምስት ቀናት ያክል ድምፁ ጠፋ። ለቢቢሲም ስልክ አልደወለም። በአምስተኛው ቀን ማታ አንድ ስልክ ጠራ።

ሞሐመድ የስፔኗ ካናሪ ደሴት ለመድረስ ግማሽ ቀን ይቀረው ነበር። ነገር ግን የጀልባዋ ሞተር ችግር አጋጠመው። ይህን ተከትሎ ጀልባዋ ወደ ሴኔጋል መመለስ ነበረባት።

ሞሐመድ ቢተርፍም በጉዞው ምክንያት እጅጉን ደካክሟል። ጤናው ተቃውሷል። ለዓመታት ያቀደው ጉዞ ሳይሳካ ቀርቷል። አሁን ወደ ቤተሰቡ ተመልሶ ለሁለተኛ ዙር ውቅያኖሱን ለማቋረጥ ገንዘብ እያሰባሰበ ይገኛል።

“ሁለተኛ ጊዜ መሞከሬ አይቀርም። በፈጣሪዬ እምላለሁ መሞከሬ አይቀርም። እሱ ይሻለኛል። ከሞትኩም የፈጣሪ ሥራ ነው።”

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)