የብሔራዊ ባንክ ውሳኔን ተከትሎ ንግድ ባንክ የዶላር መሸጫ ዋጋውን በ8 ብር ቀነሰ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ በሚገዙበት እና በሚሸጡበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዶላር መሸጫ በስምንት ብር ቀነሰ።

መንግሥት ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ ዋጋ እንዲወሰን ያወጣውን አዲስ ፖሊሲ ተከትሎ በባንኮች የሚካሄደው የውጭ ምንዛሪ ግብይት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ የባንኮች አንድ ዶላር የመግዣ ዋጋ ከ115 ብር በላይ መድረሱ ይታወቃል። ባንኮቹ ለደንበኞቻቸው አንድ ዶላርን የሚሸጡበት ዋጋ ደግሞ እስከ 128 ብር ከፍ ብሏል።

በዚህ የግብይት ሂደት ውስጥ በአገሪቱ ያሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የመሸጫ እና የመግዣ ዋጋቸውን በየዕለቱ እየወሰኑ ይፋ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ በመግዣ እና በመሸጫ ዋጋቸው መካከል የጎላ ልዩነት ሲታይ ቆይቷል። በአብዛኛዎቹ ባንኮች በዶላር መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸው መካከል ያለው ልዩነት ከ10 በመቶ በላይ ነው።

በዚህም መሠረት የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ባስተዋወቀው አዲስ ፖሊሲ፤ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ የመግዣ እና የመሸጫ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ወስኗል።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥታዊው እና በአገሪቱ ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ቀናት የውጭ ምንዛሪ ሲገበያይበት በነበረው ዋጋ ላይ ጉልህ ቅናሽ አድርጓል።

ንግድ ባንክ ዛሬ ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም. ባወጣው ዕለታዊ የውጭ ምንዛሬ ግብይት የዋጋ ዝርዝር ላይ የዶላር የመሸጫ ዋጋው ከትናንቱ ጋር ሲነጻጸር የስምንት ብር ቅናሽ አሳይቷል። ባንኩ ያደረገው ይህ ማስተካከያ በአንድ ዶላር መሸጫ እና መግዣ ዋጋ መካከል ያለውን ልዩነት ወደ ሁለት በመቶ አውርዶታል።

ንግድ ባንክ ሰኞ ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም. የዶላር የመሸጫ ዋጋው 123.63 የነበረ ሲሆን መግዣው ደግሞ 112.39 ነበር። ይህም በሁለቱ ዋጋዋች መካከል የነበረው ልዩነት የ9.2 በመቶ ነበር።

የብሔራዊ ባንክ ውሳኔን ተከትሎ ንግድ ባንክ ዛሬ ማክሰኞ ባደረገው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ዋጋ ማስተካካየ የዶላር መግዣ 113.13 ተደርጓል። መሸጫውን ደግሞ ወደ 115.39 በመውረድ የስምንት ብር ቅናሽ ታይቶበታል። ይህ የባንኩ እርምጃ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የሁለት በመቶ ልዩነት ውስጥ የሚገኝ ነው።

ብሔራዊ ባንክ አዲሱን መመሪያ በተመለከተ በአገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም ባንኮች በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን እስከ ረቡዕ ድረስ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አዟል።

እስካሁን ባንኮች በሚያወጡት ዕለታዊ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መሠረት ፀደይ ባንክ በመግዣ እና በመሸጫ ዋጋው መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ንግድ ባንክን የተከተለ ሲሆን፣ ሌሎቹም ተመሳሳዩን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ቢቢሲ የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ላይ በደረገው ዳሰሳ እንደሚያሳየው በውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋ መካከል ከፍተኛው ልዩነት የታየው በአዋሽ ባንክ ላይ ነው። ባንኩ ትናንት ይፋ ባደረገው የዶላር መሸጫ እና መገበያያ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት የ11.5 በመቶ ነው።

ባለፉት ወራት በአገሪቱ ውስጥ በሚካሄደው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ያሉ ሂደቶችን ሲከታተል መቆየቱን የገለጸው ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች በሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ግዢ እና ሽያጭ መካከል ያለው ልዩነት ዓለም አቀፍ አሠራርን የተከተለ መሆን ስላለበት መመሪያውን ማውጣቱን አመልክቷል።

ይህ ቢሆንም ግን ባንኮች የምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ስምምነት መሠረት ማካሄድ እና ማሳወቅ የሚቀጥሉ ሲሆን፣ ከውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የሚጠይቋቸውን ኮሚሽኖች ከምንዛሪ መሸጫ ዋጋ በተናጠል ለደንበኞቻቸው እንዲያሳውቁም ብሔራዊ ባንክ አዟል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)