በወልዲያ ከተማ ትናንት እሁድ ምሽት የተከሰተው ምንድን ነው?

በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልዲያ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለሰዓታት የዘለቀ “ከባድ” የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

እሁድ ጥቅምት 03/ 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡30 ገደማ ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ የተካሄደው የተኩስ ልውውጥ በተለይ በተወሰኑ የከተማዋ ክፍሎች ላይ የነበረ ሲሆን፤ ለሰዓታት የቆየ እንደበረም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በከተማዋ ውስጥ በተካሄደው ውጊያ በሰው እና በንበረት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ቢቢሲ ከከተማዋ ባለሥልጣናት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂ ቡድን ጥቃት የፈጸመው የመንግሥት ኃይሎች “ወታደራዊ ማዘዣዎች” ላይ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በከተማዋ በዋናነት ጎንደር በር እና መቻሬ (ወልዲያ ዓለም አቀፍ ስታዲየም አካባቢ) በተባሉ ሁለት ስፍራዎች “ከባድ ውጊያ” እንደነበረ የተናገሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሦስት ነዋሪዎች፤ በአካባቢዎቹ የመንግሥት ኃይሎች የሚጠቀሙባቸው ካምፖች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እሁድ ቀን ላይ የመንግሥት ኃይሎች ከባድ መሳሪያ በወልዲያ ዙሪያ ባሉ (ተራራማ) አካባቢዎች ላይ ሲተኩሱ እንደነበር የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ምሽት ላይ ግን የፋኖ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ዘልቀው መግባታቸውን ተናግረዋል።

“ወልዲያ ዱቄት ፋብሪካ (ኬላ/ጎንደር በር) በሚባለው አካባቢ እና ስታዲየም አካባቢ ላይ ተኩስ ነበር። አዳሩን ከባድ መሳሪያ ይተኮስ ነበር። በሁለቱ አካባቢዎች ኃይለኛ ተኩስ ነበር” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

“[እሁድ] ማታ ባልተጠበቀ ሁኔታ እዚሁ ከተማ ውስጥ ጎንደር በር በኩል [የፋኖ ኃይሎች] ገብተው ከፍተኛ ተኩስ ተከፈተ። በተለያዩ አቅጣጫዎችም መጠነኛ ተኩሶች ነበሩ” ያሉ ሌላ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ፤ የተኩስ ልውውጡ እስከ ሌሊት 06፡00 ገደማ ድረስ መቆየቱን ተናግረዋል።

“ኬላና ጎንደር በር ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚባሉ አካባቢዎች አሉ። መቻሬ እስታዲየም ደግሞ መከላከያ ካምፕ ያደረገው አለ። የተኩሱን አቅጣጫ ሳየው እነዚህ ቦታዎችን ዒላማ ያደረገ ይመስላል” ሲሉ አንድ ነዋሪ የፋኖ ታጣቂዎች የመንግሥት ኃይሎች ‘በሰፈሩባቸው’ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የአማራ ፋኖ በወሎ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ፈንታው በአካባቢው ውጊያ እንደነበር አረጋግጠው፤ ታጣቂዎቹ በከተማዋ ባሉ “በወታደራዊ ስፍራዎች” ላይ ጥቃት ፈጽመው እኩለ ሌሊት ላይ ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ግጭቱ ከምሽት ጅሮ አስከ እኩለ ሌሊት የተካሄደ በመሆኑ ከተማዋን ለሰዓታት ካናወጠው ተኩስ ውጪ ነዋሪዎች ምን እንደተከሰተ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በወልዲያ ከተማ ጋብ ብሎ የተነበረው የተኩስ ልውውጥ ባገረሸበት የእሁዱ ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ሆኖም በግጭቱ ከሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ሳይኖሩ እንደማይቀሩ ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

በተለይም ብርቱ የተኩስ ልውውጥ በነበረበት ስታዲሙ አካባቢ ይገኛል በተባለ ‘አጣና ተራ’ በተባለ ስፍራ ከተፋላሚ ኃይሎች የተጎዱ ሰዎች አሉ ብለዋል።

“የተጎዳ፤ የተመታ ሰው እንዳለ በድምጽ እንሰማ ነበር። ነገር ግን ከየትኛው ወገን እንደሆነ፤ ምን ያህል እንደሆነ አላወቅንም” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና መቀመጫ ወልዲያ ባለፉት ቀናት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን (ባጃጅ) ጨምሮ በትራንስፖርት ገደብ፣ ወከባ እና በዘፈቀደ እስር “ከፍተኛ ቁዝምት” ላይ ናት ብለዋል።

የእሁዱን ጥቃት ተከትሎ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 04/2017 በከተማዋ መደበኛ እንቅስቃሴ መቀጠሉን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የንግድ መደበሮችን ጨምሮ በወልዲያ “እንቅስቃሴ አለ” ብለዋል።

“ቀድሞም እንቅስቃሴው ስለተናወጠ ምንም አዲስ የተጨመረ አይመስልም። [ሰሞኑን] የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ስለተገታ ሁኔታው የተለመደ ነው” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

“ባንኮችን ጨምሮ ሁሉም እንቅስቃሴ አለ፤ እየሠሩ ነው” ያሉ ሌላ ነዋሪ ደግሞ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተለመደ ነው ያሉትን እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ብለዋል።

“ከነጋ የፓትሮል እንቅስቃሴ አለ። መደበኛው የተለመደው ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ነዋሪዎች በስጋትም ቢሆን እንቅስቃሴዎች ስለመቀጠላቸው ተናግረዋል።

ሐምሌ መጨረሻ 2015 ዓ.ም. በመንግሥት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በተደጋጋሚ ውጊያ ከሚደረግባቸው ከተሞች ውስጥ ወልዲያ ትጠቀሳለች።

የፋኖ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ዘልቀው በመግባት ማረሚያ ቤቶችን ከመስበር ጀምሮ በአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠሩ የቦምብ ጥቃቶችን ተፈጽመዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)