የስክሪን ሱስ፡ ለአምስት ቀናት ከስልካቸው እንዲርቁ የተደረጉት ታዳጊዎች ምን ሆኑ?

ታዳጊ ልጆች ያሏቸው በርካታ ወላጆች የሚጨነቁበት አንድ ጉዳይ አለ። ይህም ልጆቻቸው ስማርት ስልኮች ላይ የሚያጠፉት ጊዜ ነው።

እርግጥ ዘመናዊ ስልኮች ለዘመናዊ ሕይወት ያላቸው አስተዋፅዖ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

ወጣቶች የሚገናኙት፣ ለጥያቄያቸው ምላሽ የሚያገኙት፣ የቤት ሥራቸውን የሚሠሩት፤ በአንዳንድ አገራት ደግሞ ለትራንስፖርት እና ለለስላሳ እና ለምግብ የሚከፍሉት ስልክ ተጠቅመው ነው።

ነገር ግን ሰዎች ቀላል የማይባል ጊዜያቸውን ስክሪን ላይ በማፍጠጥ በተለይ ደግሞ ማኅበራዊ ሚድያ በማሰስ ማሳለፋቸው ይህ ቴክኖሎጂ ሱስ እየሆነ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው።

የዘርፉ ሰዎች ይሀን ሱስ በእንግሊዝኛው ‘ፎሞ’ ይሉታል። “ፊር ኦፍ ሚሲንግ አውት” ለሚለው ትንታኔ የሚሆን ምሕፃረ-ቃል ነው። በአማርኛው “ምን አምልጦኝ ይሆን?” የሚለው ጥያቄ ይተካው ይሆናል።

በይነ-መረብ ላይ አንድ አስደናቂ አሊያም አስገራሚ ነገር እየተካሄደ ነው፤ እንዳያመልጠኝ የሚለውን ፍራቻ የሚወክል ፍቺ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያስጠናው ጥናት እንደሚያሳየው ማኅበራዊ ሚድያ እና የመሳሰሉ የበይነ መረብ ገጾችን ስናስስ የሚነቃቃው የአእምሯችን ክፍል ሱስ አምጪ ዕፆችን ስንወስድ ከሚነቃቃው ጋር ተመሳሳይ ነው።

ቢቢሲ ታዳጊዎች ከስማርት ስልክ ጋር ያላቸው ቁርኝት ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ አንድ ጥናት አካሂዷል።

በእንግሊዟ ሳልፈርድ የሚገኘው ሚድያ ሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች የሆኑ 10 ታዳጊዎች ስማርት ስልካቸውን አስረክበው ስልክ ለመደወል እና የፅሑፍ መልዕክት ለመለዋወጥ ብቻ የሚያገለግል ኖኪያ ስልክ ተሰጣቸው።

“ቴክ ዲቶክስ” በተባለው 5 ቀናት የወሰደ ጥናት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች ለውጡን እንደሚያስተውሉት መቼም የሚያጠራጥር አይደለም።

አዲሱ አሊያም ታዳጊ የሚባለው ትውልድ ከስማርት ስልኮች ጋር ያደረገ ነው። ለሁሉም ነገር በይነ-መረብን መጠቀም ይመርጣል። በማኅበራዊ ሚድያዎች ይደዋወላል፤ አቅጣጫ ፍለጋ ጉግል ማፕስ ይከፍታል፤ ያሻውን ሙዚቃ የሚሰማውም ስልኩን ተጠቅሞ ነው።

የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኛ ክሪስቲያን ጆንሰን በጥናቱ ከተሳተፉት ተማሪዎች መካከል የተወሰኑትን እንዲታዘብ አደራ ተብሎ የተመለከተውን እንዲህ ያጋራል።

ከተማሪዎቹ መካከል ዊል የተባለው ታዳጊ በቀን ቢያንስ ለ8 ሰዓታት ያክል ስልኩ ላይ ተተክሎ ይውላል። ልጅ ሳለ ብስክሌት መንዳት ይወድ ነበር። ነገር ግን አሁን ከትምህርት በኋላ ያለውን ጊዜ የሚያሳልፈው የቲክቶክ ቪድዮ በመመልከት ነው።

ከጥናቱ በፊት ባለው ሳምንት ዊል 31 ሰዓታትን ማኅበራዊ ሚድያ በመመልከት አሳልፏል። ትልቁ ጭንቀቱ የነበረው አምስት ቀናት ሙሉ እንዴት ከስማርት ስልክ ርቆ ማሳለፍ ይቻላል የሚለው ነው።

“ከቤተሰቦቹ ጋር መቀራረብ መጀመር አለብኝ ማለት ነው” ይላል።ስልኩን የሚያስቀምጥ ወጣትየምስሉ መግለጫ, ወጣቶቹ በስልካቸው ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ ለመቀነስ ከስማርት ስልኮቻቸው እንዲርቁ ተደርገው ነበር

አዎንታዊ ተፅዕኖ

ሩቢ ሕልሟ ተዋናይት መሆን ነበር። ስልኳ ላይ በርካታ ሰዓታት እንደምታሳልፍ አትክድም። አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቿን ረስታ ቲክቶክ ላይ ተጥዳ እንደምትውል ትናገራለች።

ክሪስቲያን የጥናቱ አጋማሽ ላይ ወደ ሩቢ ቤተሰብ ለጥየቃ ሄደ። የቤተሰቦቿ ጋር ሲደርስ የ15 ዓመቷ ሩቢ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እየተዘጋጃጀች ነበር።

አባቷ ታዳጊዋ ልጁ የሥራ ዩኒፎርሟን እንዳትረሳ ቦርሳዋ ውስጥ ማስገባቷን ያረጋግጣል፤ እናቷ ደግሞ ወደ ባቡር ጣቢያው ልታደርሳት እየተሰናዳች ነው።

ሩቢ ስማርት ስልኳን አሳልፋ መስጠቷ ከወላጆቿ ጋር “እንድታወጋ” ጊዜ እንደሰጣት አምናለች። እናቷ ኤማ እንደምትለው ሩቢ ከስማርት ስልክ መራቋ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው።

“ሩቢ የስማርት ስልክ ሱሰኛ ናት። አሁን ከስማርት ስልኳ መራቋ እኔ ታዳጊ ሳለሁ ነገሮች እንዴት እንደነበሩ ለማየት ዕድሉን ሰጥቷታል” ትላለች እናቷ ኤማ።

“ብዙ እናወጋለን። ወደ አልጋዋ የምትሄደው በጊዜ ነው። ደስ የሚል ለውጥ ነው።”

ሩቢ የባቡር ጣቢያ ስትደርስ አጋጣሚ ሆኖ ባቡሩ ሞልቶ ሄዷል። ቀጣዩ ባቡር ስንት ደቂቃ ቆይቶ ይመጣል የሚለው በስልኳ ማጣራት ልምድ የሆነባት ሩቢ ግድግዳው ላይ የተለጠፈውን ሰሌዳ መመልከት ነበረባት።

“ያለ ስልክ ምን እየሆነ እንዳለ የማጣራበት መንገድ የለኝም” ትላለች።

የሚቀጥለው ባቡር እስኪመጣ ሩቢ በትርፍ ጊዜዋ በሳምንት ጥቂት ቀናት ሥራ እንደምትሠራ ለክሪስቲያን ትነገረዋለች። ነገር ግን አሁን ስማርት ስልክ ስሌላት ፈረቃዋ መች እንደሆነ ማወቅ አትችልም።

ምንም እንኳ የሥራ አለቃዋ ፈረቃዋን ለማጣራት ደውላ የምትጠይቀበት ስልክ ቁጥር ቢሰጣትም መደወል ዳገት ይሆንባታል።

ለወትሮው በስልኳ የምትከፍለውን የባቡር ቲኬት አሁን በካርድ ለመክፈል ተገዳለች። ያለስማርት ስልክ አንድ ሰዓት ያክል የሚወስደውን የባቡር ጉዞ ጀመረች።ስልኳን የምትመለከት ታዳጊየምስሉ መግለጫ, ወጣቶች እና ታዳጊዎች በሁሉም ቦታዎች ላይ ትኩረታቸው በሙሉ በስልካቸው ላይ እየሆነ ነው

ፍራቻ

አንዳንድ ታዳጊዎች ስማርት ስልካቸውን መጠቀም ማቆም እጅግ ይከብዳቸዋል።

የ14 ዓመቱ ቻርሊ ጥናቱ በተጀመረ በ27ኛው ሰዓት እንደማይቀጥል ተናግሮ ስማርት ስልኩን ተቀብሎ ወጣ።

“ስልኬ እዚሁ [የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ] እያለ የሆነ ሰው ሊያገኘኝ ይፍልግ ይሆን? እንዴት ነው ቀኔን የምገፋው የሚለው ነገር ጭንቀት ሆነብኝ” ይላል።

ልክ እንደ ቻርሊ ሁሉ ሌሎች በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች “ፎሞ” የተሰኘው ፍራቻ እንደገጠማቸው ይናገራሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ስልክ ሳይዙ መዋል ያለው ነፃነት አስገርሟቸዋል።

አንዳንዶቹ ተሳታፊዎች የተሻለ እንቅልፍ እያገኙ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ስማርት ስልካቸውን መጠቀም ሲያቆሙ የበለጠ ምርታማ እንደሆኑ ያስረዳሉ።

“አዳዲስ ነገሮች እየተማርኩ እንደሆነና የበለጠ ተሳታፊ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ምን አምልጦኝ ይሆን? የሚለው ስሜት እየተሰማኝ አይደለም” ትላለች የ15 ዓመቷ ግሬስ።

ጥናቱ በተጀመረ በመጀመሪያው ቀን ነው ግሬስ እና ጓደኞቿ ከትምርህት በኋላ ለአዲስ ኖኪያ ስልካቸው የፕላስቲክ ጌጣጌጥ ለመግዛት የወጡት።

ግሬስ “ቤት እንደገባሁ ሥዕል መሳል ጀምሪያለሁ። ድሮ የምደሰትባቸውን ነገሮች እንደ አዲስ እንዳጥጣምቸው ሆኛለሁ” ትላለች።

ባለፈው የካቲት የብሪታኒያ መንግሥት ሕፃናት ትምህርት ያላቸው ቀን ስልክ እንዳይጠቀሙ የሚያበረታታ አዲስ ደንብ አውጥቷል።

ነገር ግን ከተለያዩ ፓርቲዎች የተውጣጡ የሕዝብ እንደራሴ አባላት ባለፈው ግንቦት ትምህርት ቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች ሙሉ በመሉ ስልክ እንዳይጠቀሙ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 20 ያሉ 2 ሺህ ታዳጊዎች በተሳተፉበት የቢቢሲ ጥናት ውጤት መሠረት 23 በመቶው የሚሆኑት ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ስልክ እንዳይጠቀሙ የሚለውን ሐሳብ ይደግፉታል።

35 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚድያ እንዳይጠቀሙ መታገድ አለበት ይላሉ።

50 በመቶዎቹ ደግሞ ስማርት ስልካቸው ከጎናቸው ከሌለ ጭንቀት እንደሚሰማቸው ይገልጻሉ። ባለፈው ዓመት የተሠራ ጥናት ይህን ቁጥር 56 በመቶ ያደርገዋል።

ከአምስት ቀናት በኋላ በጥናቱ የተሳተፉት ተማሪዎች መልሰው ስማርት ስልካቸውን እንዲጠቀሙ ተፈቀደላቸው። አብዛኞቹ በደስታ ፈነደቁ።

ስልካቸውን እንደከፈቱ ያመለጣቸውን ነገር ለማጣራት ስክሪናቸው ላይ አቀረቀሩ። የጽሑፍ መልዕክት እና ማኅበራዊ ሚድያን ማሰስ ያዙ።

ቢሆንም አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ስልካቸው ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ የሚቀንስላቸው መላ ቢኖር ይመርጣሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)