ካማላ ሃሪስ የሕክምና ማስረጃቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ትራምፕ ጫና እየበረታባቸው ነው

ዕጩ ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ጤናቸው “በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ” ለመራጮች ለማረጋገጥ የሕክምና ማስረጃዎቻቸውን ይፋ ሲያደርጉ፤ ተፎካካሪያቸውን ዶናልድ ትራምፕም ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ ግፊት እየበረታባቸው ነው።

የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ የሕክምና ማስረጃዎቻቸውን ይፋ ባለማድረጋቸው “ግልጽነት ይጎድላቸዋል” ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ አክለውም የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጪ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ለፕሬዝዳንትነት ብቁ ይሁኑ አይሁኑ የአሜሪካ ሕዝብ እንዲያውቅ አይፈልጉም” ብለዋል።

ነገር ግን የትራምፕ ረዳቶች የሕክምና መዛግብቶቻቸውን ይፋ ሳያደርጉ የግል ዶክተራቸው ጤናቸው “ያለምንም እክል በጥሩ ሁኔታ ላይ” እንደሚገኝ በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል።

የትራም የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላት ዕጩው ፕሬዝዳንት “በጣሙን የተጨናነቀ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻን በብቃት እያካሄዱ” መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሃሪስ የዚያን ያህል “ጥንካሬን የሚጠይቅ ብቃት የላቸውም” ሲሉ ተችተዋል።

በሁለቱ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች መካከል የትችት ቃላት ልውውጥ የተጀመረው የምክትል ፕሬዝዳንቷ ጽህፈት ቤት ካማላ ሃሪስ ፕሬዝዳንት ሆነው አሜሪካንን ለማገልገል የሚያስፈልገው “አካላዊ እና አእምሯዊ ጥንካሬ” እንዳለቸው ያሳያል ያሉትን የሕክምና ምርመራ ውጤት ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

ለሦስት ዓመታት የሃሪስ ሐኪም ሆነው እያገለገሉ ያሉት የአሜሪካ ሠራዊት ኮሎኔል ዶ/ር ጆሽዋ ሳይመንስ በሕክምና ማስረጃው ላይ ምክትል ፕሬዝዳንቷ የተለያዩ ምርመራዎችን በማድግ ጤናማ እና ንቁ የሕይወት ዘይቤ እንዳለቸው አረጋግጠዋል።

የሃሪስ የሕክምና ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ የምርጫ ዘመቻ ቃል አቀባያቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ዶናልድ ትራምፕ፤ አሁን የእርሶ ተራ ነው” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዲሞክራቶች፤ ሪፐብሊካኖችን በመወከል የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪያቸው የሆኑት የ78 ዓመቱን ትራምፕ በዕድሜ መግፋት እና በአእምሮ ብቃታቸው ሲተቿቸው ቆይተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በሚካሄደው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት የሚያሸንፉ ከሆነ ከአራት ዓመት በኋላ የመሪነት ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ፣ በመጪው ጥር ሥልጣን ከሚያስረክቡት ጆ ባይደን ጋር በአሜሪካ ታሪክ በዕድሜ የገፉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ታሪክን ይጋራሉ።

ከተቀናቃኛቸው በኩል የሕክምና ማስረጃዎቻቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ግፊት የበረታባቸው ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ኃላፊ በሰጡት ምላሽ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የግል ዶክተራቸው እና በግድያ ሙከራ ከተካሄደባቸው በኋላ ሕክምና ያደረጉላቸው ሐኪሞች የጤንነታቸው ሁኔታ ተገልጿል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

“የሁለቱም ሐኪሞች ውጤት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ለመሆን በሚያስችል እጅግ በጣም ጥሩ በሚባል የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ደምድመዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በዕጩነት ቀርበዋል።

እስካሁን ያለውን የመራጮች ፍላጎትን በተመለከተ የተደረጉ አገር አቀፍ የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች ሃሪስ በጠባብ ነጥብ ትራምፕን እየመሩ መሆናቸውን ሲያመለክቱ፣ ከባድ ፉክክር በሚደረግባቸው ግዛቶች ውስጥ ሁለቱ ዕጩዎች በጣም ተቀራራቢ ውጤት አግኝተዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

 

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

 

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)