ኬንያዊቷ አትሌት በትዕግስት አሰፋ ተይዞ የነበረውን የማራቶን ክብረ ወሰን ሰበረች

ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ተይዞ የነበረውን የማራቶን ክብረ ወሰን ሰበረች።

አትሌቷ ይህንን ክብረ ወሰን ያሻሸለችው እሁድ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም በቺካጎ በተደረገ የማራቶን ውድድር ነው።

የ30 ዓመቷ ኬንያዊት አትሌት በትዕግስት አሰፋ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በሁለት ደቂቃ በማሻሻል 2፡09፡57 ሰዓት በማስመዝገብ ነው ውድድሩን ያጠናቀቀችው።

ቼፕንጌቲች የማራቶን ሩጫ ውድድርን ከሁለት ሰዓት ከ10 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመሮጥ የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።

ትዕግስት በ2፡11፡33 ሰኮንዶች ክብረ ወሰን ያስመዘገበችው ባለፈው ዓመት በርሊን በተካሄደው የማራቶን ውድድር ነበር።

የ29 ዓመቷ አትሌት ትዕግሥት በአውሮፓውያኑ 2019 በተካሄደው የችካጎ ማራቶን በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ ተመዝግቦ የነበረውን 2:14.04 ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል ነበር አዲስ ክብረ ወሰን የጨበጠችው።

“በጣም ጥሩ ስሜት ይሰማኛል። በራሴ ኮርቻለሁ። በድሉ ህልሜ ዕውን ሆኗል” ስትል በአውሮፓውያኑ 2019 የዓለም አቀፉ ማራቶን ሻምፒዮን የሆነችው ቼፕንጌቲች ተናግራለች።

“ስለ ዓለም ክብረ ወሰን በማሰብ ብዙ ታግያለሁ አሁን አሳክቸዋለሁ” ስትል ገልጻለች።

አትሌቷ በቺካጎ ማራቶን ድል ስታስመዘግብ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት የሃገሯ ልጅ በሆነችው ብሪጊድ ኮስጌይ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ለመስበር 14 ሰኮንዶች ብቻ ነበር የዘገየችው።

ከአምስቱ ፈጣን የሴቶች የማራቶን ሰዓት አራቱ የተገኙት በቺካጎ በባለፉት ስድስት ዓመታት ነው።

በወንዶች የማራቶን ውድድር ኬንያዊው ጆን ኮሪር አሸናፊ ሲሆን ኢትዮጵያዊው መሃመድ ኢሳ ሁለተኛ እንዲሁም ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ በሶስተኛነት አጠናቀዋል።

በዚህ ውድር ድል የቀናው ጆን ኮሪር ባለፈው ዓመት አሸናፊ የነበረው ኬልቪን ኪፕቱምን ዘክሮታል።

በባለፈው ዓመት በቺካጎ የወንዶች የማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን በሁለት ሰዓት አምስት ሰኮንዶች የጨበጠው ኪፕቱም ከውድድሩ ከአራት ወራት በኋላ በመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል።

ኪፕቱም ገና የ24 ዓመት ወጣት ነበር።

የዘንድሮው አሸናፊ ጆን ኮሪር የአገሩ ልጅ ኪፕቱም ድል እንዳነሳሳው ተናግሯል።

“ዛሬ ስለ ኪፕቱም እያሰብኩ ነበር እናም እሱ ከ2 ሰዓት ከአንድ ደቂቃ በመሮጥ ካሳካ፤ እኔስ ለምን ማሳካት አልችልም አልኩኝ? በራሴ ማመን እና የቻልኩትን ሁሉ ማድረግ ነበረብኝ” ሲል ከድሉ በኋላ ገልጿል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)